ነፍሴ ሆይ! እግዚአብሔርን አመስግኚ! እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! እንዴት ታላቅ ነህ! ግርማንና ክብርን ለብሰሃል። ብርሃንንም እንደ ልብስ ተጐናጽፈሃል፤ ሰማይን እንደ ድንኳን ዘርግተሃል። በጠፈር ላይ ካለው ውሃ በላይ ቤትህን ሠርተሃል፤ ደመና ሠረገላህ ነው፤ በነፋስ ክንፎችም ትሄዳለህ። ነፋስ መልእክተኛህ ነው፤ የእሳት ነበልባልም አገልጋይህ ነው። ምድርን በመሠረትዋ ላይ አጽንተህ አቆምሃት፤ ከቶም አትናወጥም። ውቅያኖስን እንደ ልብስ አለበስካት፤ ውሃውም ተራራዎችን ሸፈነ። ውሃውን በገሠጽከው ጊዜ ከፊትህ ሸሸ፤ የትእዛዝህን ድምፅ በሰማ ጊዜ በፍጥነት ሮጠ። አንተ ወዳዘጋጀህለት ስፍራ፥ ወደ ተራራዎች ላይና ወደ ሸለቆዎች ውስጥ ፈሰሰ። ዳግመኛ ምድርን እንዳይሸፍንም የማይጥሰውን ወሰን አበጀህለት። ምንጮች በሸለቆ ውስጥ እንዲፈስሱ፥ ወንዞችም በተራራዎች መካከል እንዲወርዱ አደረግህ። በዚህ ዐይነት የዱር አውሬዎች የሚጠጡት ውሃ ያገኛሉ፤ የሜዳ አህዮችም ጠጥተው ጥማቸውን ያረካሉ። በነዚህም ምንጮችና ወንዞች አጠገብ ባሉት ዛፎች ላይ፥ ወፎች ጎጆአቸውን ሠርተው ያዜማሉ። ከሰማይ ዝናብን በተራሮች ላይ ታወርዳለህ፤ ምድርም በምትሰጣት በረከት ትሞላለች። ሣርን ለእንስሶች ታበቅላለህ፤ አትክልትንም ለሰው ልጆች ጥቅም እንዲውል ታደርጋለህ፤ በዚህ ዐይነት ሰው ምግብ የሚሆነውን ዘርቶ ይሰበስባል። ስለዚህ ልቡን ደስ የሚያሰኝ የወይን ጠጅ፥ ፊቱን የሚያበራ ዘይትና ብርታት የሚሰጠውን ምግብ ያዘጋጃል። እግዚአብሔር የተከላቸው የሊባኖስ ዛፎች በቂ ዝናብ ያገኛሉ፤ በላያቸውም ወፎች ጎጆዎቻቸውን ይሠራሉ፤ ሸመላዎችም በእነዚያ ዛፎች ላይ መኖሪያቸውን ያበጃሉ።
መጽሐፈ መዝሙር 104 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መዝሙር 104:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች