ምሳሌ 11:1-16
ምሳሌ 11:1-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አባይ ሚዛን በእግዚአብሔር ፊት አስጸያፊ ነው፤ እውነተኛ ሚዛን ግን በእርሱ ዘንድ የተመረጠ ነው። ትዕቢት ባለበት በዚያ ውርደት አለ፤ የየዋሃን አፍ ግን ጥበብን ይማራል። ጻድቃንን ፍጻሜያቸው ትመራቸዋለች፤ ኃጥኣንን ግን መሰነካከላቸው ትማርካቸዋለች። በቍጣ ቀን ገንዘብ አይጠቅምም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ታድናለች። ጻድቅ በሞተ ጊዜ ጸጸትን ይተዋል፥ የኀጢአተኛ ሞት ግን በእጅ የተያዘና ሣቅ ይሆናል። የፍጹም ሰው ጽድቁ መንገዱን ያቀናለታል፤ ኀጢአት ግን በክፉዎች ላይ ትወርዳለች። ቅኖች ሰዎችን ጽድቃቸው ይታደጋቸዋል፤ ኃጥኣን ግን ባለማወቃቸው ይጠመዳሉ። ጻድቅ ሰው በሞተ ጊዜ ተስፋውን አያጣም፥ የክፉዎች ትምክሕታቸው ግን ትጠፋለች። ጻድቅ ከወጥመድ ያመልጣል፥ ኀጢአተኛ ግን በእርሱ ፋንታ ይሰጣል። በክፉዎች አፍ የሀገር ወጥመድ አለ፥ የጻድቃን ዕውቀት ግን መልካም ጎዳና ናት። በጻድቃን ደግነት ከተማ ትቀናለች፥ በክፉዎችም ጥፋት ደስ ይላታል። በቅኖች በረከት ከተማ ከፍ ከፍ ትላለች፤ በኃጥኣን አፍ ግን ትገለበጣለች። ጥበብ የጐደለው የሀገሩን ሰው ይንቃል። ብልህ ሰው ግን ጸጥታን ያመጣል። ሁለት ምላስ የሆነ ሰው የጉባኤን ምሥጢር ይገልጣል፤ በአንደበቱ የታመነ ግን ነገርን ይሰውራል። መምህር የሌላቸው እንደ ቅጠል ይወድቃሉ። በምክር ብዛት ግን ደኅንነት ይኖራል። ክፉ ሰው ከጻድቅ ጋር በተቀላቀለ ጊዜ ይከፋል፥ የሰላም ድምፅንም ይጠላል። ደግ ሴት ለባሏ ክብርን ታስገኛለች፥ ጽድቅን የምትጠላ ሴት ግን የውርደት ወንበር ናት። ሐኬተኞች ከብልጽግና ይደኸያሉ፥ ብርቱዎች ግን ብልጽግናን ይከተላሉ።
ምሳሌ 11:1-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር የተጭበረበረ ሚዛንን ይጸየፋል፤ ትክክለኛ መለኪያ ግን ደስ ያሠኘዋል። ትዕቢት ስትመጣ ውርደትም ትከተላለች፤ በትሑት ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች። ቅኖችን ትክክለኛነታቸው ትመራቸዋለች፤ ወስላቶች ግን በገዛ አታላይነታቸው ይጠፋሉ። በቍጣ ቀን ሀብት ፋይዳ የለውም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ትታደጋለች። ለፍጹማን ሰዎች ጽድቃቸው መንገዳቸውን ታቃናላቸዋለች፤ ክፉዎች ግን በገዛ ክፋታቸው ይወድቃሉ። ቅኖችን ጽድቃቸው ትታደጋቸዋለች፤ ወስላቶች ግን በክፉ ምኞታቸው ይጠመዳሉ። ክፉ ሰው ሲሞት ተስፋው ከንቱ ትሆናለች፤ በኀይሉ የተመካበትም ሁሉ እንዳልነበረ ይሆናል። ጻድቅ ከመከራ ይድናል፤ ይልቁን መከራው በክፉው ላይ ይደርሳል። ክፉ ሰው ባልንጀራውን በአፉ ያጠፋል፤ ጻድቃን ግን በዕውቀት ያመልጣሉ። ጻድቃን ሲሳካላቸው ከተማ ደስ ይላታል፤ ክፉዎች ሲጠፉ እልልታ ይሆናል። በቅኖች በረከት ከተማ ከፍ ከፍ ትላለች፤ በክፉዎች አንደበት ግን ትጠፋለች። ልበ ቢስ ባልንጀራውን ያንኳስሳል፤ አስተዋይ ግን አንደበቱን ይገዛል። ሐሜተኛ ምስጢር አይጠብቅም፤ ታማኝ ሰው ግን ምስጢር ይጠብቃል። በአመራር ጕድለት መንግሥት ይወድቃል፤ የመካሮች ብዛት ግን ድልን ርግጠኛ ያደርጋል። ለማይታወቅ ሰው ዋስ የሚሆን መከራ ያገኘዋል፤ ዋስትና ለመስጠት እጅ የማይመታ ግን ምንም አይደርስበትም። ርኅሩኅ ሴት ክብር ታገኛለች፤ ጨካኝ ሰዎች ግን ብልጽግናን ብቻ ያገኛሉ።
ምሳሌ 11:1-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር በሐሰተኛ ሚዛን የሚያታልሉትን ሰዎች ይጠላል፤ በትክክለኛ ሚዛን በሚመዝኑት ሰዎች ግን ይደሰታል። ትዕቢት ውርደትን ያስከትላል፤ ትሕትና ግን ጥበብን ያስገኛል። ቀጥተኞች ሰዎች ቅንነታቸው ይመራቸዋል። እምነት የማይጣልባቸው ሰዎች ግን ጠማማነታቸው ያጠፋቸዋል። ለመሞት በምትቃረብበት ቀን ሀብትህ አይጠቅምህም፤ ደግነት ግን የሕይወት ዋስትና ይሆንልሃል። ደግነት የመልካሙን ሰው ኑሮ ያቃናለታል፤ ክፉ ሰው ግን በገዛ ክፋቱ ይወድቃል። ቅን ሰው በደግነቱ ይድናል፤ እምነት የማይጣልበት ሰው ግን የራሱ ክፉ ምኞት ወጥመድ ሆኖ ይይዘዋል። ክፉ ሰው ሲሞት ተስፋውም አብሮት ይሞታል፤ በኀይሉ መመካቱም አብሮት ይጠፋል። ጻድቅ ከመከራ ይድናል። መከራው ግን በክፉ ሰው ላይ ይደርሳል። እግዚአብሔርን የማያመልኩ በንግግራቸው ሰውን ያጠፋሉ፤ ጻድቃን ግን በዕውቀት ይድናሉ። ለጻድቃን፥ ሁሉ ነገር ሲሳካላቸው በከተማው ውስጥ ደስታ ይሆናል። ክፉዎች ሲጠፉ ደግሞ እልልታ ይሆናል። በእውነተኞች ሰዎች በረከት ምክንያት ከተማ እያደገች ትሄዳለች፤ የክፉ ሰዎች መጥፎ ንግግር ግን ወደ ውድቀት ያደርሳታል። በንቀት ተናግሮ ሰውን የሚያዋርድ፥ ማስተዋል የጐደለው ነው፤ አስተዋይ ሰው ግን ዝም ይላል። ሐሜተኛ ሰው ምሥጢር አይጠብቅም፤ ታማኝ ሰው ግን ምሥጢርን ሰውሮ ይይዛል። አማካሪ የሌለው መንግሥት ይወድቃል፤ ብዙ አማካሪዎች ሲኖሩ ግን ዋስትና ይገኛል። የማታውቀውን ሰው ዕዳ ለመክፈል ዋስ ብትሆን፥ በችግር ላይ ትወድቃለህ፤ ዋስ መሆን ቢቀርብህ ግን የተሻለ ነው። ሞገስ ያላት ሴት ትከበራለች፤ መልካም ጠባይ የሌላት ሴት ግን ውርደት ያገኛታል። ሰነፍ ሰው ሀብት ማግኘት አይችልም፤ ታታሪ ሰው ግን ሀብታም ይሆናል።
ምሳሌ 11:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የሐሰት ሚዛን በጌታ ፊት አስጸያፊ ነው፥ እውነተኛ ሚዛን ግን ደስ ያሰኘዋል። ትዕቢት ከመጣች ውርደት ትመጣለች፥ በትሑታን ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች። ቅኖች ቅንነታቸው ትመራቸዋለች፥ ወስላቶችን ግን ጠማማነታቸው ታጠፋቸዋለች። በቁጣ ቀን ሀብት አትረባም፥ ጽድቅ ግን ከሞት ታድናለች። የፍጹም ሰው ጽድቁ መንገዱን ያቀናለታል፥ ክፉ ግን በክፋቱ ይወድቃል። ቅኖችን ጽድቃቸው ይታደጋቸዋል፥ ወስላቶች ግን በምኞታቸው ይጠመዳሉ። ክፉ ሰው በሞተ ጊዜ ተስፋው ይቈረጣል፥ የኃያል አለኝታም ይጠፋል። ጻድቅ ከጭንቀት ይድናል፥ ክፉ ግን የእርሱን ቦታ ይወስዳል። እኩይ ሰው በአፉ ባልንጀራውን ያጠፋል፥ ጻድቃን ግን በእውቀት ይድናሉ። በጻድቃን ልማት ከተማ ደስ ይላታል፥ በክፉዎችም ጥፋት እልል ትላለች። በቅኖች በረከት ከተማ ከፍ ከፍ ትላለች፥ በክፉዎች አፍ ግን ትገለበጣለች። ወዳጁን የሚንቅ ልበ ጐደሎ ነው፥ አስተዋይ ሰው ግን ዝም ይላል። ለሐሜት የሚሄድ ምሥጢሩን ይገልጣል፥ በመንፈስ የታመነ ግን ነገሩን ይሰውራል። መልካም ምክር በሌለበት ሕዝብ ይወድቃል፥ በአማካሪዎች ብዛት ግን ዋስትና ይገኛል። ለእንግዳ ሰው የሚዋስ ክፉ መከራን ይቀበላል፥ ዋስ መሆንን የሚጠላ ግን ይድናል። ሞገስ ያላት ሴት ክብርን ታገኛለች፥ ኃያላንም ሀብትን ያገኛሉ።።