ምሳሌ 11
11
1 እግዚአብሔር የተጭበረበረ ሚዛንን ይጸየፋል፤
ትክክለኛ መለኪያ ግን ደስ ያሰኘዋል።
2ትዕቢት ስትመጣ ውርደትም ትከተላለች፤
በትሑት ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች።
3ቅኖችን ትክክለኛነታቸው ትመራቸዋለች፤
ወስላቶች ግን በገዛ አታላይነታቸው ይጠፋሉ።
4በቍጣ ቀን ሀብት ፋይዳ የለውም፤
ጽድቅ ግን ከሞት ትታደጋለች።
5ለፍጹማን ሰዎች ጽድቃቸው መንገዳቸውን ታቃናላቸዋለች፤
ክፉዎች ግን በገዛ ክፋታቸው ይወድቃሉ።
6ቅኖችን ጽድቃቸው ትታደጋቸዋለች፤
ወስላቶች ግን በክፉ ምኞታቸው ይጠመዳሉ።
7ክፉ ሰው ሲሞት ተስፋው ከንቱ ትሆናለች፤
በኀይሉ የተመካበትም ሁሉ እንዳልነበረ ይሆናል።
8ጻድቅ ከመከራ ይድናል፤
ይልቁን መከራው በክፉው ላይ ይደርሳል።
9ክፉ ሰው ባልንጀራውን በአፉ ያጠፋል፤
ጻድቃን ግን በዕውቀት ያመልጣሉ።
10ጻድቃን ሲሳካላቸው ከተማ ደስ ይላታል፤
ክፉዎች ሲጠፉ እልልታ ይሆናል።
11በቅኖች በረከት ከተማ ከፍ ከፍ ትላለች፤
በክፉዎች አንደበት ግን ትጠፋለች።
12ማመዛዘን የጐደለው ሰው ባልንጀራውን ያንኳስሳል፤
አስተዋይ ግን አንደበቱን ይገዛል።
13ሐሜተኛ ምስጢር አይጠብቅም፤
ታማኝ ሰው ግን ምስጢር ይጠብቃል።
14በአመራር ጕድለት መንግሥት ይወድቃል፤
የመካሮች ብዛት ግን ድልን ርግጠኛ ያደርጋል።
15ለማይታወቅ ሰው ዋስ የሚሆን መከራ ያገኘዋል፤
ዋስትና ለመስጠት እጅ የማይመታ ግን ምንም አይደርስበትም።
16ርኅሩኅ ሴት ክብር ታገኛለች፤
ጕልበተኛ ሰዎች ግን ብልጽግናን ብቻ ያገኛሉ።
17ደግ ሰው ራሱን ይጠቅማል፤
ጨካኝ ግን በራሱ ላይ መከራ ያመጣል።
18ክፉ ሰው የሚያገኘው ትርፍ መቅኖ የለውም፤
ጽድቅን የሚዘራ ግን አስተማማኝ ዋጋ ያገኛል።
19እውነተኛ ጻድቅ ሕይወትን ያገኛል፤
ክፋትን የሚከተል ግን ወደ ሞቱ ይጓዛል።
20 እግዚአብሔር ልበ ጠማሞችን ይጸየፋል፤
በመንገዳቸው ነቀፋ በሌለባቸው ሰዎች ግን ደስ ይሰኛል።
21ክፉ ሳይቀጣ እንደማይቀር ዕወቅ፣
ጻድቃን ግን በነጻ ይሄዳሉ።
22በእርያ አፍንጫ ላይ እንደ ተሰካ የወርቅ ቀለበት፣
ማስተዋል የጐደላት ቈንጆ ሴት እንዲሁ ናት።
23የጻድቃን ምኞት ምንጊዜም ፍጻሜው ያማረ ነው፤
የክፉዎች ተስፋ ግን በቍጣ ያከትማል።
24አንዱ በለጋስነት ይሰጣል፤ ሆኖም ይበልጥ ያገኛል፤
ሌላው ያለ መጠን ይሰስታል፤ ግን ይደኸያል።
25ለጋስ ይበለጽጋል፤
ሌሎችን የሚያረካም ራሱ ይረካል።
26በድብቅ እህል የሚያከማቸውን ሕዝብ ይረግመዋል፤
አውጥቶ የሚሸጥ ግን በረከት ይጐናጸፋል።
27በጎ ነገርን ተግቶ የሚሻ በጎ ነገር ይጠብቀዋል፤
ክፉ ነገር የሚፈልገውን ግን ክፉ ያገኘዋል።
28በሀብቱ የሚታመን ሁሉ ይወድቃል፤
ጻድቃን ግን እንደ አረንጓዴ ቅጠል ይለመልማሉ።
29ቤተ ሰቡን የሚያውክ ሰው ነፋስን ይወርሳል፤
ተላላም ሰው የጠቢብ ሎሌ ይሆናል።
30የጻድቅ ፍሬ የሕይወት ዛፍ ናት፤
ነፍሳትን የሚማርክም ጠቢብ ነው።
31ጻድቃን ለሠሩት ሥራ በምድር የእጃቸውን የሚያገኙ ከሆነ፣
የክፉዎችና የኀጢአተኞችማ የቱን ያህል የባሰ ይሆን?
Currently Selected:
ምሳሌ 11: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.