የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ምሳሌ 12

12
1ተግሣጽን የሚወድድ ዕውቀትን ይወድዳል፤
መታረምን የሚጠላ ግን ደነዝ ነው።
2መልካም ሰው ከእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ ያገኛል፤
ተንኰለኛውን ግን እግዚአብሔር ይፈርድበታል።
3ሰው በክፋት ላይ ተመሥርቶ ሊጸና አይችልም፤
ጻድቃን ግን ከቦታቸው አይነቃነቁም።
4መልካም ሴት ለባሏ ዘውድ ናት፤
አሳፋሪ ሚስት ግን ዐጥንቱ ውስጥ እንዳለ ንቅዘት ናት።
5የጻድቃን ሐሳብ ቀና ነው፤
የክፉዎች ምክር ግን ሸር አለበት።
6የክፉዎች ቃል ደም ለማፍሰስ ታደባለች፤
የቅኖች ንግግር ግን ይታደጋቸዋል።
7ክፉ ሰዎች ይገለበጣሉ፤ ድራሻቸውም ይጠፋል፤
የጻድቃን ቤት ግን ጸንቶ ይኖራል።
8ሰው በጥበቡ ይመሰገናል፤
ጠማማ ልብ ያላቸው ግን የተናቁ ናቸው።
9የሚበላው ሳይኖረው ከሚኵራራ ይልቅ፣
ራሱን ዝቅ አድርጎ ሠራተኛ የሚያሳድር ይሻላል።
10ጻድቅ ሰው ለእንስሳቱ ይራራል፤
ክፉዎች ራሩ ቢባል እንኳ ዞሮ ዞሮ ሥራቸው ጭካኔ ነው።
11መሬቱን የሚያርስ የተትረፈረፈ ምግብ ያገኛል፤
ከንቱ ተስፋን የሚያሳድድ ግን ማመዛዘን ይጐድለዋል።
12ኀጥኣን የክፉዎችን ምርኮ ይመኛሉ፤
የጻድቅ ሥር ግን ይንሰራፋል።
13ክፉ ሰው በእኩይ ንግግሩ ይጠመዳል፤
ጻድቅ ሰው ግን ከመከራ ያመልጣል።
14ሰው ከከንፈሩ ፍሬ የተነሣ በበጎ ነገር ይሞላል፤
እንደ እጁ ሥራም ተገቢውን ዋጋ ያገኛል።
15ተላላ ሰው መንገዱ ትክክል መስሎ ይታየዋል፤
ጠቢብ ሰው ግን ምክር ይሰማል።
16ተላላ ሰው ቍጣው ወዲያውኑ ይታወቅበታል፤
አስተዋይ ሰው ግን ስድብን ንቆ ይተዋል።
17ሐቀኛ ምስክር በእውነት ይመሰክራል፤
ሐሰተኛ ምስክር ግን ውሸት ይናገራል።
18ግድ የለሽ ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤
የጠቢብ አንደበት ግን ፈውስን ያመጣል።
19እውነት የሚናገሩ ከንፈሮች ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ፤
ሐሰተኛ አንደበት ግን ለቅጽበት ያህል ብቻ ነው።
20ክፋትን በሚያውጠነጥኑ ሰዎች ልብ አታላይነት አለ፤
ሰላምን የሚያራምዱ ግን ደስታ አላቸው።
21ጻድቃን ጕዳት አያገኛቸውም፤
ክፉዎች ግን በመከራ የተሞሉ ናቸው።
22 እግዚአብሔር ሐሰተኛ ከንፈርን ይጸየፋል፤
በእውነተኞች ሰዎች ግን ደስ ይለዋል።
23አስተዋይ ሰው ዕውቀቱን ይሰውራል፤
የተላሎች ልብ ግን ድንቍርናን ይነዛል።
24ትጉህ እጆች ለገዥነት ሲያበቁ፣
የስንፍና ፍጻሜ ግን የባርነት ሥራ ነው።
25ሥጉ ልብ ሰውን በሐዘን ይወጥራል፤
መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል።
26ጻድቅ ሰው ለወዳጁ መልካም ምክር ይሰጣል፤#12፥26 ወይም ለወዳጁ መሪ ሆኖም የዕብራይስጡ ፍች በውል አይታወቅም።
የክፉዎች መንገድ ግን ወደ ስሕተት ይመራቸዋል።
27ሰነፍ ዐድኖ ያመጣውን እንኳ አይጠብስም፤#12፥27 ለዚህ ቃል የዕብራይስጡ ትርጓሜ በርግጠኝነት አይታወቅም።
ትጉህ ሰው ግን ለንብረቱ ዋጋ ይሰጣል።
28በጽድቅ መንገድ ላይ ሕይወት አለ፤
በዚያ ጐዳና ላይ ሞት የለም።

Currently Selected:

ምሳሌ 12: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ