ነህምያ 4:6-20

ነህምያ 4:6-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ቅጥ​ሩ​ንም ሠራን፤ ቅጥ​ሩም ሁሉ እስከ እኩ​ሌ​ታው ድረስ ተጋ​ጠመ፤ ሕዝቡ ከልብ ይሠራ ነበ​ርና። ሰን​ባ​ላ​ጥና ጦብ​ያም፥ ዓረ​ባ​ው​ያ​ንም፥ አሞ​ና​ው​ያ​ንም፥ አዛ​ጦ​ና​ው​ያ​ንም የኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ቅጥር እየ​ታ​ደሰ እንደ ሄደ፥ የፈ​ረ​ሰ​ውም ሊጠ​ገን እንደ ተጀ​መረ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቈጡ። መጥ​ተ​ውም ኢየ​ሩ​ሳ​ሌ​ምን ይወ​ጉና ያፈ​ር​ሷት ዘንድ ሁሉም በአ​ን​ድ​ነት ተሰ​በ​ሰቡ። እኛም ወደ አም​ላ​ካ​ችን ጸለ​ይን፤ ከእ​ነ​ር​ሱም የተ​ነሣ በአ​ን​ጻ​ራ​ቸው ተጠ​ባ​ባ​ቂ​ዎ​ችን በሌ​ሊ​ትና በቀን አደ​ረ​ግን። ይሁ​ዳም፥ “የተ​ሸ​ካ​ሚ​ዎች ኀይል ደከመ፤ ፍር​ስ​ራ​ሹም ብዙ ነው፤ ቅጥ​ሩ​ንም እን​ሠራ ዘንድ አን​ች​ልም” አሉ። ጠላ​ቶ​ቻ​ች​ንም፥ “ወደ መካ​ከ​ላ​ቸው እስ​ክ​ን​መ​ጣና እስ​ክ​ን​ገ​ድ​ላ​ቸው ድረስ፥ ሥራ​ቸ​ው​ንም እስ​ክ​ና​ስ​ተ​ጓ​ጕል ድረስ አያ​ው​ቁም፤ አያ​ዩም” አሉ። በአ​ጠ​ገ​ባ​ቸ​ውም የተ​ቀ​መ​ጡት አይ​ሁድ መጥ​ተው፥ “ከስ​ፍ​ራው ሁሉ ይመ​ጡ​ብ​ናል ብለው ዐሥር ጊዜ ነገ​ሩን።” ከቅ​ጥ​ሩም በስ​ተ​ኋላ በኩል ባለው በታ​ች​ኛው ክፍል በሰ​ዋራ ስፍራ ሰይ​ፋ​ቸ​ው​ንና ጦራ​ቸ​ውን፥ ቀስ​ታ​ቸ​ው​ንም አስ​ይዤ ሕዝ​ቡን በየ​ወ​ገ​ና​ቸው አቆ​ም​ኋ​ቸው፤ አይ​ችም ተነ​ሣሁ፤ ታላ​ላ​ቆ​ቹ​ንና ሹሞ​ቹ​ንም፥ የቀ​ሩ​ት​ንም ሕዝብ፥ “አት​ፍ​ሩ​አ​ቸው፤ ታላ​ቁ​ንና የተ​ፈ​ራ​ውን አም​ላ​ካ​ች​ንን አስቡ፤ ስለ ወን​ድ​ሞ​ቻ​ች​ሁም፥ ስለ ወን​ዶ​ችና ሴቶች ልጆ​ቻ​ች​ሁም፥ ስለ ሚስ​ቶ​ቻ​ች​ሁም፥ ስለ ቤቶ​ቻ​ች​ሁም ተዋጉ” አል​ኋ​ቸው። ጠላ​ቶ​ቻ​ች​ንም እንደ ዐወ​ቅ​ን​ባ​ቸው፥ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ምክ​ራ​ቸ​ውን ከንቱ እን​ዳ​ደ​ረ​ገው ሰሙ፤ እኛም ሁላ​ችን ወደ ቅጥሩ እያ​ን​ዳ​ን​ዳ​ችን ወደ ሥራ​ችን ተመ​ለ​ስን። ከዚ​ያም ቀን ጀምሮ እኩ​ሌ​ቶቹ ብላ​ቴ​ኖች ሥራ ይሠሩ ነበር፤ እኩ​ሌ​ቶ​ቹም ጋሻና ጦር፥ ቀስ​ትና ጥሩ​ርም ይዘው በፊ​ትና በኋላ ይጠ​ብቁ ነበር፤ አለ​ቆ​ቹም ከይ​ሁዳ ቤት ሁሉ በኋላ ይቆሙ ነበር። ቅጥ​ሩ​ንም የሚ​ሠ​ሩ​ትና ሸክም ተሸ​ካ​ሚ​ዎቹ በአ​ንድ እጃ​ቸው ይሠሩ ነበር፤ በአ​ንድ እጃ​ቸ​ውም የጦር መሣ​ሪ​ያ​ቸ​ውን ይይዙ ነበር። አና​ጢ​ዎ​ቹም ሁሉ እያ​ን​ዳ​ንዱ ሰይ​ፉን በወ​ገቡ ታጥቆ ይሠራ ነበር፤ ቀንደ መለ​ከ​ትም የሚ​ነፋ በአ​ጠ​ገቤ ነበረ። ታላ​ላ​ቆ​ቹ​ንና ሹሞ​ቹን፥ የቀ​ሩ​ት​ንም ሕዝብ፥ “ሥራው ታላ​ቅና ሰፊ ነው፤ እኛም በቅ​ጥሩ ላይ ተበ​ታ​ት​ነ​ናል፤ አን​ዱም ከሁ​ለ​ተ​ኛው ርቆ​አል፤ የቀ​ንደ መለ​ከ​ቱን ድምፅ ወደ​ም​ት​ሰ​ሙ​በት ስፍራ ወደ​ዚያ ወደ እኛ ተሰ​ብ​ሰቡ፤ አም​ላ​ካ​ችን ስለ እኛ ይዋ​ጋል” አል​ኋ​ቸው።

ነህምያ 4:6-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ሕዝቡ ከልቡ ስለሚሠራ፣ ቅጥሩን እኩሌታው ድረስ መልሰን ሠራነው። ሰንባላጥ፣ ጦቢያ፣ ዐረቦች፣ የአሞንና የአሽዶድ ሰዎች፣ የኢየሩሳሌም ቅጥር ሥራ እየተፋጠነና ክፍት ቦታዎቹም ሁሉ እየተሞሉ መሆናቸውን በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቈጡ። መጥተውም ኢየሩሳሌምን ይወጉ ዘንድ፣ ሽብርንም ይፈጥሩ ዘንድ ሁሉም በአንድነት አደሙ። እኛ ግን ወደ አምላካችን ጸለይን፤ ዛቻቸውንም ለመቋቋም ቀንና ሌሊት የሚጠብቁ ዘቦችን መደብን። በዚህ ጊዜ የይሁዳ ሕዝብ፣ “የሠራተኞቹ ጕልበት እየደከመ ነው፤ ከፍርስራሹም ብዛት የተነሣ ቅጥሩን መልሰን ለመሥራት አንችልም” አሉ። ጠላቶቻችን ደግሞ፣ “በመካከላቸው ገብተን እስክንገድላቸውና ሥራውን እስክናስቆም ድረስ አያውቁም ወይም አያዩም” አሉ። ከዚያም በአጠገባቸው የሚኖሩ አይሁድ መጥተው፣ “እናንተ የትም ቦታ ብትሆኑ፣ እኛን ማጥቃታቸው አይቀርም!” በማለት ዐሥር ጊዜ ደጋግመው ነገሩን። ስለዚህ ከቅጥሩ በስተኋላ በሚገኙ ግልጽ ቦታዎች ላይ ከሕዝቡ አንዳንዶቹ ሰይፋቸውን፣ ጦራቸውንና ቀስታቸውን እንደ ያዙ በየቤተ ሰባቸው በመመደብ ቦታቸውን እንዲይዙ አደረግሁ። ነገሩን በጥሞና ከተመለከትሁ በኋላ መኳንንቱን፣ ሹማምቱንና የቀረውን ሕዝብ፣ “አትፍሯቸው፤ ታላቁንና የተፈራውን ጌታ አስቡ፤ ስለ ወንድሞቻችሁ፣ ስለ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ፣ ስለ ሚስቶቻችሁና ስለ ቤት ንብረታችሁ ተዋጉ” አልኋቸው። አድማቸውን እንዳወቅንባቸውና እግዚአብሔርም ዕቅዳቸውን ከንቱ እንዳደረገባቸው ጠላቶቻችን በሰሙ ጊዜ፣ ሁላችን ወደ ቅጥሩ፣ እያንዳንዳችንም ወደየሥራችን ተመለስን። ከዚያ ቀን ጀምሮ ከሰዎቼ እኩሌቶቹ ሥራውን ሠሩ፤ የቀሩት ደግሞ ጋሻና ጦር፣ ቀስትና ጥሩር ይዘው ነበር። የጦር አለቆች ከመላው የይሁዳ ሕዝብ በስተኋላ ቆሙ፤ እነርሱም ቅጥሩን ይገነቡ ነበር፤ ዕቃ የሚሸከሙት በአንድ እጃቸው ሥራቸውን ሲሠሩ፣ በሌላው እጃቸው የጦር መሣሪያቸውን ይዘው ነበር፤ እያንዳንዱም ግንበኛ ቅጥሩን በሚሠራበት ጊዜ ሰይፉን በወገቡ ላይ ታጥቆ ነበር፤ መለከት የሚነፋው ሰው ግን ከእኔ አይለይም ነበር። ከዚያም ለመኳንንቱ፣ ለሹማምቱና ለቀረው ሕዝብ እንዲህ አልሁ፤ “ሥራው ታላቅ ነው፤ ብዙም ነው፤ እርስ በርሳችን በቅጥሩ ላይ እጅግ ተራርቀናል፤ የመለከት ድምፅ በምትሰሙበት ጊዜ፣ ወደ እኛ ተሰብሰቡ። አምላካችን ስለ እኛ ይዋጋል።”

ነህምያ 4:6-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ቅጥሩንም ሠራን፥ ቅጥሩም ሁሉ እስከ እኩሌታው ድረስ ተጋጠመ፥ የሕዝቡም ልብ ለሥራው ጨከነ። ሰንበላጥና ጦብያም ዓረባውያንም አሞናውያንም አሽዶዳውያንም የኢየሩሳሌም ቅጥር እየታደሰ እንደ ሄደ፥ የፈረሰውም ሊጠገን እንደ ተጀመረ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቈጡ። መጥተውም ኢየሩሳሌምን ይወጉና ያሸብሩ ዘንድ ሁሉም በአንድነት ተማማሉ። ወደ አምላካችንም ጸለይን፥ ከእነርሱም የተነሣ በአንጻራቸው ተጠባባቂዎች በሌሊትና በቀን አደረግን። ይሁዳም፦ የተሸካሚዎች ኃይል ደከመ፥ ፍርስራሹም ብዙ ነው፥ ቅጥሩንም እንሠራ ዘንድ አንችልም አሉ። ጠላቶቻችንም፦ ወደ መካከላቸው እስክንመጣና እስክንገድላቸው ድረስ ሥራቸውንም እስክናስተጓጉል ድረስ አያውቁምና አያዩም አሉ። በአጠገባቸውም የተቀመጡት አይሁድ መጥተው፦ ከስፍራው ሁሉ ይመጡብናል ብለው አሥር ጊዜ ነገሩን። ከቅጥሩም በስተ ኋላ በኩል ባለው በታችኛው ስፍራ ሰይፋቸውን ጦራቸውንም ቀስታቸውንም አስይዤ ሕዝቡን በየወገናቸው አቆምኋቸው። አይቼም ተነሣሁ፥ ታላላቆቹንና ሹማምቱንም የቀሩትንም ሕዝብ፦ አትፍሩአቸው፥ ታላቁንና የተፈራውን ጌታ አስቡ፥ ስለ ወንድሞቻችሁም ስለ ወንዶችና ስለ ሴቶች ልጆቻችሁም ስለ ሚስቶቻችሁም ስለ ቤቶቻችሁም ተዋጉ አልኋቸው። ጠላቶቻችንም ይህ ነገር እንደ ደረሰልን፥ እግዚአብሔርም ምክራቸውን ከንቱ እንዳደረገው ሰሙ፥ እኛም ሁላችን ወደ ቅጥሩ እያንዳንዳችን ወደ ሥራችን ተመለስን። ከዚያም ቀን ጀምሮ እኩሌቶቹ ብላቴኖቼ ሥራ ይሠሩ ነበር፥ እኩሌቶቹም ጋሻና ጦር ቀስትና ጥሩርም ይዘው ነበር፥ አለቆቹም ከይሁዳ ቤት ሁሉ በኋላ ይቆሙ ነበር። ቅጥሩንም የሚሠሩትና ተሸካሚዎቹ በአንድ እጃቸው ይሠሩ ነበር፥ በአንድ እጃቸውም የጦር መሣሪያቸውን ይይዙ ነበር። አናጢዎቹም ሁሉ እያንዳንዱ ሰይፉን በወገቡ ታጥቆ ይሠራ ነበር፥ ቀንደ መለከትም የሚነፋ በአጠገቤ ነበረ። ታላላቆቹንና ሹማምቱን የቀሩትንም ሕዝብ፦ ሥራው ታላቅና ሰፊ ነው፥ እኛም በቅጥሩ ላይ ተበታትነናል፥ አንዱም ከሁለተኛው ርቆአል፥ የቀንደ መለከቱን ድምፅ ወደምትሰሙበት ስፍራ ወደዚያ ወደ እኛ ተሰብሰቡ፥ አምላካችን ስለ እኛ ይዋጋል አልኋቸው።

ነህምያ 4:6-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እኛም ቅጽሩን መልሶ የማነጹን ሥራ ቀጠልን፤ ሕዝቡ በትጋት በመሥራቱ ሥራው እየተፋጠነ ሄዶ ግማሽ ደረሰ። ሰንባላጥ፥ ጦቢያና የዐረብ፥ የዐሞን፥ የአሽዶድም ሕዝብ ጭምር የኢየሩሳሌምን ቅጽር ግንብ እንደገና መልሰን በመሥራት ረገድ ጥሩ የሥራ ውጤት ማስገኘታችንንና በቅጽሮቹ መካከል የነበሩት ክፍት ቦታዎች መዘጋታቸውን በሰሙ ጊዜ በብርቱ ተቈጡ፤ ስለዚህም በአንድነት ተባብረው ወደ ኢየሩሳሌም ለመምጣትና አደጋ ጥለው ሽብር ለመፍጠር በእኛ ላይ አድማ አደረጉ፤ እኛ ግን ወደ አምላካችን ጸለይን፤ እነርሱንም ለመቋቋም ሌሊትና ቀን ቆመው የሚጠብቁ ዘበኞችን መደብን። በዚህ ጊዜ የይሁዳ ሰዎች “የሸክም ሥራ እያደከመን ሄደ፤ ገና መነሣት ያለበት ፍርስራሽ ብዙ ነው፤ ቅጽሩን እንሠራ ዘንድ አንችልም” አሉ። “ጠላቶቻችን የምናደርገውን ከማወቃቸውና ከማየታቸው በፊት በመካከላቸው ተገኝተን እነርሱን ገድለን ሥራቸውንም እናቆመዋለን” አሉ። በጠላቶቻችን መካከል የሚኖሩ አይሁድ ወደ ከተማው እየመጡ ጠላቶቻችን እኛን ለማጥቃት ያቀዱ መሆናቸውን ደጋግመው በማስጠንቀቅ ነገሩን። ስለዚህም ከሕዝባችን መካከል ሰይፍ፥ ጦርና ቀስት የያዙ ሰዎችን በየጐሣቸው በማዘጋጀት፥ ሥራው ባልተጠናቀቀበት ቦታ ሁሉ በቅጽሩ ግንብ በስተጀርባ እንዲመሸጉ አደረግሁ። ሕዝቡ ተጨንቀው ስላየሁ፥ እነርሱንና መሪዎቻቸውን፥ ሌሎችንም ባለሥልጣኖች ሁሉ “ከጠላቶቻችን የተነሣ አትፍሩ፤ ምን ያኽል ታላቅና ግርማው የሚያስፈራ አምላክ እንዳለንና እርሱ ስለ ወገኖቻችሁ፥ ስለ ልጆቻችሁና ሚስቶቻችሁ ስለ ቤት ንብረታችሁም እንደሚዋጋላችሁ አስታውሱ” አልኳቸው። ጠላቶቻችንም የተማማሉበትን አድማ የደረስንበት መሆኑን ሰሙ፤ እግዚአብሔርም ዕቅዳቸውን እንዳከሸፈባቸው ተገነዘቡ፤ ከዚያ በኋላ ሁላችንም የቅጽሩን ግንብ መሥራታችንን ቀጠልን። ከዚህም ጊዜ ጀምሮ እኔ ያሰለፍኳቸው ሰዎች እኩሌቶቹ ሲሠሩ፥ እኩሌቶቹ ጥሩር ለብሰው፥ ጦር ይዘው፥ ጋሻ አንግበው፥ ቀስት ደግነው ዘብ በመቆም እንዲጠብቁ አደረግሁ፤ መሪዎቻችንም ለሕዝቡ ሙሉ ድጋፍ ይሰጡ ነበር፤ ቅጽሩን የሚሠሩትን ሁሉ ያበረታቱ ነበር፤ ሌላው ቀርቶ፥ ተሸካሚዎቹ ጭምር በአንድ እጃቸው ሲሠሩ፥ በሌላ እጃቸው የጦር መሣሪያ ይዘው ለመከላከል ዝግጁዎች ነበሩ። እያንዳንዱም ግንበኛ ሰይፉን በወገቡ ታጥቆ ይሠራ ነበር፤ እምቢልታ ነፊውም ከአጠገቤ አይለይም ነበር። ሕዝቡን፥ መሪዎቻቸውንና ሹማምንቱን “የቅጽሩ ሥራ ታላቅና እጅግ ሰፊ ስለ ሆነ፥ እርስ በርሳችን በመራራቃችን አንዱ ከሌላው ጋር ለመገናኘት አይችልም። የእምቢልታ ድምፅ በምትሰሙበት ጊዜ ወደ እኔ መጥታችሁ በዙሪያዬ ተሰብሰቡ፤ አምላካችን ስለ እኛ ይዋጋልናል” አልኳቸው፤