የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ነህምያ 4

4
1ሰንባላጥም ቅጥሩን እንደ ሠራን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፥ ተበሳጨም፥ በአይሁድም አላገጠ። 2በወንድሞቹና በሰማርያ ሠራዊትም ፊት፦ እነዚህ ደካሞች አይሁድ የሚሠሩት ምንድር ነው? ይተዉላቸዋልን? ይሠዋሉን? በአንድ ቀንስ ይጨርሳሉን? የተቃጠለውንስ ድንጋይ ከፍርስራሹ መልሰው ያድኑታልን? ብሎ ተናገረ። 3አሞንዊውም ጦብያ በአጠገቡ ቆሞ፦ በድንጋይ በሚሠሩት ቅጥራቸው ላይ ቀበሮ ቢመጣበት ያፈርሰዋል አለ። 4አምላካችን ሆይ፥ ተንቀናልና ስማ፥ ስድባቸውን በራሳቸው ላይ መልስባቸው፥ በምርኮ አገር ለብዝበዛ አሳልፈህ ስጣቸው። 5በደላቸውንም አትክደን፥ ኃጢአታቸውም ከፊትህ አይደምሰስ፥ በሠራተኞች ፊት አስቆጥተውሃልና። 6ቅጥሩንም ሠራን፥ ቅጥሩም ሁሉ እስከ እኩሌታው ድረስ ተጋጠመ፥ የሕዝቡም ልብ ለሥራው ጨከነ።
7ሰንበላጥና ጦብያም ዓረባውያንም አሞናውያንም አሽዶዳውያንም የኢየሩሳሌም ቅጥር እየታደሰ እንደ ሄደ፥ የፈረሰውም ሊጠገን እንደ ተጀመረ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቈጡ። 8መጥተውም ኢየሩሳሌምን ይወጉና ያሸብሩ ዘንድ ሁሉም በአንድነት ተማማሉ። 9ወደ አምላካችንም ጸለይን፥ ከእነርሱም የተነሣ በአንጻራቸው ተጠባባቂዎች በሌሊትና በቀን አደረግን። 10ይሁዳም፦ የተሸካሚዎች ኃይል ደከመ፥ ፍርስራሹም ብዙ ነው፥ ቅጥሩንም እንሠራ ዘንድ አንችልም አሉ። 11ጠላቶቻችንም፦ ወደ መካከላቸው እስክንመጣና እስክንገድላቸው ድረስ ሥራቸውንም እስክናስተጓጉል ድረስ አያውቁምና አያዩም አሉ። 12በአጠገባቸውም የተቀመጡት አይሁድ መጥተው፦ ከስፍራው ሁሉ ይመጡብናል ብለው አሥር ጊዜ ነገሩን። 13ከቅጥሩም በስተ ኋላ በኩል ባለው በታችኛው ስፍራ ሰይፋቸውን ጦራቸውንም ቀስታቸውንም አስይዤ ሕዝቡን በየወገናቸው አቆምኋቸው። 14አይቼም ተነሣሁ፥ ታላላቆቹንና ሹማምቱንም የቀሩትንም ሕዝብ፦ አትፍሩአቸው፥ ታላቁንና የተፈራውን ጌታ አስቡ፥ ስለ ወንድሞቻችሁም ስለ ወንዶችና ስለ ሴቶች ልጆቻችሁም ስለ ሚስቶቻችሁም ስለ ቤቶቻችሁም ተዋጉ አልኋቸው።
15ጠላቶቻችንም ይህ ነገር እንደ ደረሰልን፥ እግዚአብሔርም ምክራቸውን ከንቱ እንዳደረገው ሰሙ፥ እኛም ሁላችን ወደ ቅጥሩ እያንዳንዳችን ወደ ሥራችን ተመለስን። 16ከዚያም ቀን ጀምሮ እኩሌቶቹ ብላቴኖቼ ሥራ ይሠሩ ነበር፥ እኩሌቶቹም ጋሻና ጦር ቀስትና ጥሩርም ይዘው ነበር፥ አለቆቹም ከይሁዳ ቤት ሁሉ በኋላ ይቆሙ ነበር። 17ቅጥሩንም የሚሠሩትና ተሸካሚዎቹ በአንድ እጃቸው ይሠሩ ነበር፥ በአንድ እጃቸውም የጦር መሣሪያቸውን ይይዙ ነበር። 18አናጢዎቹም ሁሉ እያንዳንዱ ሰይፉን በወገቡ ታጥቆ ይሠራ ነበር፥ ቀንደ መለከትም የሚነፋ በአጠገቤ ነበረ። 19ታላላቆቹንና ሹማምቱን የቀሩትንም ሕዝብ፦ ሥራው ታላቅና ሰፊ ነው፥ እኛም በቅጥሩ ላይ ተበታትነናል፥ አንዱም ከሁለተኛው ርቆአል፥ 20የቀንደ መለከቱን ድምፅ ወደምትሰሙበት ስፍራ ወደዚያ ወደ እኛ ተሰብሰቡ፥ አምላካችን ስለ እኛ ይዋጋል አልኋቸው።
21ሥራውንም ሠራን ከማለዳ ወገግታም ጀምሮ ከዋክብት እስኪወጡ ድረስ እኩሌቶቹ ጦር ይይዙ ነበር። 22ደግሞም በዚያ ጊዜ ሕዝቡን፦ ሁላችሁ ከብላቴኖቻችሁ ጋር በኢየሩሳሌም ውስጥ እደሩ፥ በሌሊትም ጠባቂዎች ሁኑልን፥ በቀንም ሥሩ አልኋቸው። 23እኔና ወንድሞቼም ብላቴኖቼም በኋላዬም የነበሩት ጠባቂዎች ልብሳችንን አናወልቅም ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ