ቅጥሩንም ሠራን፤ ቅጥሩም ሁሉ እስከ እኩሌታው ድረስ ተጋጠመ፤ ሕዝቡ ከልብ ይሠራ ነበርና። ሰንባላጥና ጦብያም፥ ዓረባውያንም፥ አሞናውያንም፥ አዛጦናውያንም የኢየሩሳሌም ቅጥር እየታደሰ እንደ ሄደ፥ የፈረሰውም ሊጠገን እንደ ተጀመረ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቈጡ። መጥተውም ኢየሩሳሌምን ይወጉና ያፈርሷት ዘንድ ሁሉም በአንድነት ተሰበሰቡ። እኛም ወደ አምላካችን ጸለይን፤ ከእነርሱም የተነሣ በአንጻራቸው ተጠባባቂዎችን በሌሊትና በቀን አደረግን። ይሁዳም፥ “የተሸካሚዎች ኀይል ደከመ፤ ፍርስራሹም ብዙ ነው፤ ቅጥሩንም እንሠራ ዘንድ አንችልም” አሉ። ጠላቶቻችንም፥ “ወደ መካከላቸው እስክንመጣና እስክንገድላቸው ድረስ፥ ሥራቸውንም እስክናስተጓጕል ድረስ አያውቁም፤ አያዩም” አሉ። በአጠገባቸውም የተቀመጡት አይሁድ መጥተው፥ “ከስፍራው ሁሉ ይመጡብናል ብለው ዐሥር ጊዜ ነገሩን።” ከቅጥሩም በስተኋላ በኩል ባለው በታችኛው ክፍል በሰዋራ ስፍራ ሰይፋቸውንና ጦራቸውን፥ ቀስታቸውንም አስይዤ ሕዝቡን በየወገናቸው አቆምኋቸው፤ አይችም ተነሣሁ፤ ታላላቆቹንና ሹሞቹንም፥ የቀሩትንም ሕዝብ፥ “አትፍሩአቸው፤ ታላቁንና የተፈራውን አምላካችንን አስቡ፤ ስለ ወንድሞቻችሁም፥ ስለ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም፥ ስለ ሚስቶቻችሁም፥ ስለ ቤቶቻችሁም ተዋጉ” አልኋቸው። ጠላቶቻችንም እንደ ዐወቅንባቸው፥ እግዚአብሔርም ምክራቸውን ከንቱ እንዳደረገው ሰሙ፤ እኛም ሁላችን ወደ ቅጥሩ እያንዳንዳችን ወደ ሥራችን ተመለስን። ከዚያም ቀን ጀምሮ እኩሌቶቹ ብላቴኖች ሥራ ይሠሩ ነበር፤ እኩሌቶቹም ጋሻና ጦር፥ ቀስትና ጥሩርም ይዘው በፊትና በኋላ ይጠብቁ ነበር፤ አለቆቹም ከይሁዳ ቤት ሁሉ በኋላ ይቆሙ ነበር። ቅጥሩንም የሚሠሩትና ሸክም ተሸካሚዎቹ በአንድ እጃቸው ይሠሩ ነበር፤ በአንድ እጃቸውም የጦር መሣሪያቸውን ይይዙ ነበር። አናጢዎቹም ሁሉ እያንዳንዱ ሰይፉን በወገቡ ታጥቆ ይሠራ ነበር፤ ቀንደ መለከትም የሚነፋ በአጠገቤ ነበረ። ታላላቆቹንና ሹሞቹን፥ የቀሩትንም ሕዝብ፥ “ሥራው ታላቅና ሰፊ ነው፤ እኛም በቅጥሩ ላይ ተበታትነናል፤ አንዱም ከሁለተኛው ርቆአል፤ የቀንደ መለከቱን ድምፅ ወደምትሰሙበት ስፍራ ወደዚያ ወደ እኛ ተሰብሰቡ፤ አምላካችን ስለ እኛ ይዋጋል” አልኋቸው።
መጽሐፈ ነህምያ 4 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ነህምያ 4:6-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች