መጽሐፈ ነህምያ 4:6-20

መጽሐፈ ነህምያ 4:6-20 አማ05

እኛም ቅጽሩን መልሶ የማነጹን ሥራ ቀጠልን፤ ሕዝቡ በትጋት በመሥራቱ ሥራው እየተፋጠነ ሄዶ ግማሽ ደረሰ። ሰንባላጥ፥ ጦቢያና የዐረብ፥ የዐሞን፥ የአሽዶድም ሕዝብ ጭምር የኢየሩሳሌምን ቅጽር ግንብ እንደገና መልሰን በመሥራት ረገድ ጥሩ የሥራ ውጤት ማስገኘታችንንና በቅጽሮቹ መካከል የነበሩት ክፍት ቦታዎች መዘጋታቸውን በሰሙ ጊዜ በብርቱ ተቈጡ፤ ስለዚህም በአንድነት ተባብረው ወደ ኢየሩሳሌም ለመምጣትና አደጋ ጥለው ሽብር ለመፍጠር በእኛ ላይ አድማ አደረጉ፤ እኛ ግን ወደ አምላካችን ጸለይን፤ እነርሱንም ለመቋቋም ሌሊትና ቀን ቆመው የሚጠብቁ ዘበኞችን መደብን። በዚህ ጊዜ የይሁዳ ሰዎች “የሸክም ሥራ እያደከመን ሄደ፤ ገና መነሣት ያለበት ፍርስራሽ ብዙ ነው፤ ቅጽሩን እንሠራ ዘንድ አንችልም” አሉ። “ጠላቶቻችን የምናደርገውን ከማወቃቸውና ከማየታቸው በፊት በመካከላቸው ተገኝተን እነርሱን ገድለን ሥራቸውንም እናቆመዋለን” አሉ። በጠላቶቻችን መካከል የሚኖሩ አይሁድ ወደ ከተማው እየመጡ ጠላቶቻችን እኛን ለማጥቃት ያቀዱ መሆናቸውን ደጋግመው በማስጠንቀቅ ነገሩን። ስለዚህም ከሕዝባችን መካከል ሰይፍ፥ ጦርና ቀስት የያዙ ሰዎችን በየጐሣቸው በማዘጋጀት፥ ሥራው ባልተጠናቀቀበት ቦታ ሁሉ በቅጽሩ ግንብ በስተጀርባ እንዲመሸጉ አደረግሁ። ሕዝቡ ተጨንቀው ስላየሁ፥ እነርሱንና መሪዎቻቸውን፥ ሌሎችንም ባለሥልጣኖች ሁሉ “ከጠላቶቻችን የተነሣ አትፍሩ፤ ምን ያኽል ታላቅና ግርማው የሚያስፈራ አምላክ እንዳለንና እርሱ ስለ ወገኖቻችሁ፥ ስለ ልጆቻችሁና ሚስቶቻችሁ ስለ ቤት ንብረታችሁም እንደሚዋጋላችሁ አስታውሱ” አልኳቸው። ጠላቶቻችንም የተማማሉበትን አድማ የደረስንበት መሆኑን ሰሙ፤ እግዚአብሔርም ዕቅዳቸውን እንዳከሸፈባቸው ተገነዘቡ፤ ከዚያ በኋላ ሁላችንም የቅጽሩን ግንብ መሥራታችንን ቀጠልን። ከዚህም ጊዜ ጀምሮ እኔ ያሰለፍኳቸው ሰዎች እኩሌቶቹ ሲሠሩ፥ እኩሌቶቹ ጥሩር ለብሰው፥ ጦር ይዘው፥ ጋሻ አንግበው፥ ቀስት ደግነው ዘብ በመቆም እንዲጠብቁ አደረግሁ፤ መሪዎቻችንም ለሕዝቡ ሙሉ ድጋፍ ይሰጡ ነበር፤ ቅጽሩን የሚሠሩትን ሁሉ ያበረታቱ ነበር፤ ሌላው ቀርቶ፥ ተሸካሚዎቹ ጭምር በአንድ እጃቸው ሲሠሩ፥ በሌላ እጃቸው የጦር መሣሪያ ይዘው ለመከላከል ዝግጁዎች ነበሩ። እያንዳንዱም ግንበኛ ሰይፉን በወገቡ ታጥቆ ይሠራ ነበር፤ እምቢልታ ነፊውም ከአጠገቤ አይለይም ነበር። ሕዝቡን፥ መሪዎቻቸውንና ሹማምንቱን “የቅጽሩ ሥራ ታላቅና እጅግ ሰፊ ስለ ሆነ፥ እርስ በርሳችን በመራራቃችን አንዱ ከሌላው ጋር ለመገናኘት አይችልም። የእምቢልታ ድምፅ በምትሰሙበት ጊዜ ወደ እኔ መጥታችሁ በዙሪያዬ ተሰብሰቡ፤ አምላካችን ስለ እኛ ይዋጋልናል” አልኳቸው፤