ማቴዎስ 14:12-23
ማቴዎስ 14:12-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው በድኑን ወሰዱና ቀበሩት፤ መጥተውም ለኢየሱስ አወሩለት። ኢየሱስም በሰማ ጊዜ ከዚያ ብቻውን ወደ ምድረ በዳ በታንኳ ፈቀቅ አለ፤ ሕዝቡም ሰምተው ከከተማዎቹ በእግር ተከተሉት። ወጥቶም ብዙ ሕዝብ አየና አዘነላቸው፤ ድውዮቻቸውንም ፈወሰ። በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው “ቦታው ምድረ በዳ ነው፤ አሁንም ሰዓቱ አልፎአል፤ ወደ መንደሮች ሄደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ ሕዝቡን አሰናብት፤” አሉት። ኢየሱስም “እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው እንጂ ሊሄዱ አያስፈልግም፤” አላቸው። እነርሱም “ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ በቀር በዚህ የለንም፤” አሉት። እርሱም “እነዚያን ወደዚህ አምጡልኝ፤” አላቸው። ሕዝቡም በሣር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፤ እንጀራውንም ቆርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውንም ቁርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ አነሡ። ከሴቶችና ከልጆችም በቀር የበሉት አምስት ሺህ ወንዶች ያህሉ ነበር። ወዲያውም ሕዝቡን ሲያሰናብት ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳይቱ ገብተው ወደ ማዶ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው። ሕዝቡንም አሰናብቶ ይጸልይ ዘንድ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ ብቻውን በዚያ ነበረ።
ማቴዎስ 14:12-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም አስከሬኑን ወስደው ቀበሩት፤ ከዚያም ሄደው ለኢየሱስ ነገሩት። ኢየሱስ የሆነውን ነገር በሰማ ጊዜ፣ ከነበረበት ተነሥቶ ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ በጀልባ ሄደ። ሕዝቡም ይህን ሰምተው፣ ከየከተማው በእግር ተከተሉት። ኢየሱስም ከጀልባው ሲወርድ ብዙ ሕዝብ አይቶ ራራላቸው፤ ሕመምተኞቻቸውንም ፈወሰላቸው። ሊመሽ ሲል ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ይህ ስፍራ ምንም የማይገኝበት ምድረ በዳ ነው፤ ጊዜው እየመሸ ስለ ሆነ፣ ወደ መንደሮች ሄደው የሚበሉት ምግብ እንዲገዙ ሕዝቡን አሰናብት” አሉት። ኢየሱስ ግን፣ “መሄድ አያስፈልጋቸውም፤ የሚበሉትን እናንተ ስጧቸው” አላቸው። እነርሱም፣ “በዚህ ያለን ዐምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ ብቻ ነው” አሉት። እርሱም፣ “እስኪ ያለውን ወደ እኔ አምጡት” አላቸው። ከዚያም ሕዝቡ በሣሩ ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ ዐምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ዐይኑን ወደ ሰማይ በማቅናት አመስግኖና ባርኮ እንጀራውን ቈረሰ፤ ለደቀ መዛሙርቱም ሰጠ፤ እነርሱም ለሕዝቡ ሰጡ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ የተረፈውን ቍርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ አነሡ። የበሉትም ከሴቶችና ከሕፃናት ሌላ፣ ዐምስት ሺሕ ወንዶች ያህሉ ነበር። ወዲያውኑ ደቀ መዛሙርቱ በጀልባ ተሳፍረው ወደ ማዶ እንዲቀድሙት አዘዛቸውና እርሱ ሕዝቡን ለማሰናበት ወደ ኋላ ቀረት አለ። ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላም ለመጸለይ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ፤ በጨለመም ጊዜ ብቻውን በዚያው ነበር፤
ማቴዎስ 14:12-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው በድኑን ወሰዱና ቀበሩት፥ መጥተውም ለኢየሱስ አወሩለት። ኢየሱስም በሰማ ጊዜ ከዚያ ብቻውን ወደ ምድረ በዳ በታንኳ ፈቀቅ አለ፤ ሕዝቡም ሰምተው ከከተማዎቹ በእግር ተከተሉት። ወጥቶም ብዙ ሕዝብ አየና አዘነላቸው ድውዮቻቸውንም ፈወሰ። በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፦ ቦታው ምድረ በዳ ነው አሁንም ሰዓቱ አልፎአል፤ ወደ መንደሮች ሄደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ ሕዝቡን አሰናብት አሉት። ኢየሱስም፦ እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው እንጂ ሊሄዱ አያስፈልግም አላቸው። እነርሱም፦ ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ በቀር በዚህ የለንም አሉት። እርሱም፦ እነዚያን ወደዚህ አምጡልኝ አላቸው። ሕዝቡም በሣር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፥ አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፥ እንጀራውንም ቆርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፥ የተረፈውንም ቁርስራሽ አሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ አነሡ። ከሴቶችና ከልጆችም በቀር የበሉት አምስት ሺህ ወንዶች ያህሉ ነበር። ወዲያውም ሕዝቡን ሲያሰናብት ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳይቱ ገብተው ወደ ማዶ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው። ሕዝቡንም አሰናብቶ ይጸልይ ዘንድ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ ብቻውን በዚያ ነበረ።
ማቴዎስ 14:12-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም መጡና በድኑን ወስደው ቀበሩት፤ ሄደውም ይህን ነገር ለኢየሱስ ነገሩት። ኢየሱስ የዮሐንስን መሞት በሰማ ጊዜ በጀልባ ተሳፈረና ወደ አንድ ገለልተኛ ቦታ ብቻውን ለመሆን ሄደ። ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ ከየከተማው እየወጡ በእግር ተከተሉት። ኢየሱስ ከጀልባው በወረደ ጊዜ ብዙ ሕዝብን አይቶ ራራላቸው፤ በሽተኞቻቸውንም ፈወሰ። በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፥ “ይህ ቦታ ምድረ በዳ ነው፤ ቀኑም መሽቶአል፤ ስለዚህ ሕዝቡ በአቅራቢያ ወዳሉት መንደሮች ሄደው ምግባቸውን እንዲገዙ አሰናብታቸው” አሉት። ኢየሱስ ግን፦ “እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው እንጂ እነርሱ እንዲሁ ሊሄዱ አይገባም!” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም “እኛ እዚህ ያለን አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ ብቻ ነው” አሉት። ኢየሱስም “እነርሱኑ ወደ እኔ አምጡልኝ!” አላቸው። ከዚህ በኋላ ሕዝቡ በመስኩ ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ አንሥቶ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና የምስጋና ጸሎት አደረገ፤ እንጀራውንም ቈርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ ዐደሉ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውን ፍርፋሪ፥ ደቀ መዛሙርቱ በዐሥራ ሁለት መሶብ ሞልተው አነሡ። የበሉትም ሰዎች ከሴቶችና ከሕፃናት ሌላ አምስት ሺህ ያኽል ወንዶች ነበሩ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፥ “እኔ ሕዝቡን እስካሰናብት ድረስ በጀልባ ተሳፈሩና ቀድማችሁኝ ወደ ማዶ ተሻገሩ፤” ሲል አዘዛቸው። ሕዝቡንም ካሰናበተ በኋላ ለመጸለይ ብቻውን ወደ አንድ ተራራ ላይ ወጣ፤ በመሸም ጊዜ ኢየሱስ እዚያ ብቻውን ነበር።
ማቴዎስ 14:12-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ደቀ መዛሙርቱም መጥተው በድኑን ወሰደው ቀበሩት፤ መጥተውም ለኢየሱስ ነገሩት። ኢየሱስም ይህን በሰማ ጊዜ ብቻውን ገለል ወዳለ ቦታ በታንኳ ከዚያ ፈቀቅ አለ፤ ሕዝቡም ሰምተው ከየከተማው በእግር ተከተሉት። በወረደም ጊዜ ብዙ ሕዝብ አየና አዘነላቸው፤ በሽተኞቻቸውንም ፈወሰ። በመሸም ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው “ቦታው ምድረ በዳ ነው፤ ሰዓቱም አልፎአል፤ ወደ መንደሮች ሄደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ ሕዝቡን አሰናብታቸው” አሉት። ኢየሱስም “መሄድ አያስፈልጋቸውም፤ እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው” አላቸው። እነርሱም “ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ በቀር በዚህ ምንም የለንም” አሉት። እርሱም “እነዚያን ወደዚህ ወደ እኔ አምጡልኝ” አላቸው። ሕዝቡን በሣር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፤ እንጀራውንም ቆርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ ሰጡ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውንም ቁርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ አነሡ። የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች ውጪ አምስት ሺህ ወንዶች ነበሩ። ወዲያውም ሕዝቡን እስኪያሰናብት ድረስ ደቀመዛሙርቱ ወደ ጀልባ ገብተው ወደ ማዶ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው። ሕዝቡንም ካሰናበተ በኋላ ለመጸለይ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ ብቻውን በዚያው ነበር።