የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 14

14
የመጥምቁ ዮሐንስ ሞት
(ማር. 6፥14-29ሉቃ. 9፥7-9)
1በዚያን ጊዜ የገሊላ ክፍለ ሀገር ገዢ የነበረው ሄሮድስ፥ የኢየሱስን ዝና ሰማ። 2አገልጋዮቹን፥ “ይህ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ እርሱ ከሞት ተነሥቶአል፤ እነዚህ ድንቅ ነገሮች በእርሱ አማካይነት የሚደረጉት ስለዚህ ነው” አላቸው።
3ሄሮድስ ዮሐንስን አስይዞ በወህኒ ቤት አሳስሮት ነበር፤ ይህንንም ያደረገው የወንድሙ የፊልጶስ ሚስት በነበረችው በሄሮዲያዳ ምክንያት ነው። #ሉቃ. 3፥19-20። 4ዮሐንስ ለሄሮድስ፦ “የወንድምህን ሚስት እንድታገባ ሕግ አይፈቅድልህም!” ብሎት ነበር። #ዘሌ. 18፥16፤ 20፥21። 5ስለዚህ ሄሮድስ ዮሐንስን ሊገድለው ይፈልግ ነበር፤ ነገር ግን የአይሁድ ሕዝብ እንደ ነቢይ ያዩት ስለ ነበር ሕዝቡን ፈራ። 6የሄሮድስ ልደት በሚከበርበት ቀን የሄሮድያዳ ልጅ መጥታ በተጋባዦች መካከል እየጨፈረች ሄሮድስን አስደሰተች። 7ስለዚህም ሄሮድስ፦ “የምትፈልጊውን ነገር ጠይቂኝ! እኔም እሰጥሻለሁ!” ሲል በመሐላ ቃል ገባላት።
8እርስዋም በእናቷ ተመክራ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ በሳሕን አሁኑኑ ስጠኝ!” አለችው።
9ንጉሡ በዚህ ነገር አዘነ፤ ይሁን እንጂ ስለ መሐላውና ከእርሱ ጋር በማእድ ተቀምጠው ስለ ነበሩት ሰዎች ይሉኝታ ብሎ የዮሐንስ ራስ እንዲሰጣት አዘዘ። 10ስለዚህ ወደ ወህኒ ቤት ሰው ልኮ የዮሐንስን ራስ በወህኒ ቤት አስቈረጠ። 11የተቈረጠውንም ራስ በሳሕን አምጥተው ለልጅቱ ሰጡአት፤ እርስዋም ለእናትዋ ወስዳ ሰጠች። 12የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም መጡና በድኑን ወስደው ቀበሩት፤ ሄደውም ይህን ነገር ለኢየሱስ ነገሩት።
ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን እንደ መገበ
(ማር. 6፥30-44ሉቃ. 9፥10-17ዮሐ. 6፥1-14)
13ኢየሱስ የዮሐንስን መሞት በሰማ ጊዜ በጀልባ ተሳፈረና ወደ አንድ ገለልተኛ ቦታ ብቻውን ለመሆን ሄደ። ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ ከየከተማው እየወጡ በእግር ተከተሉት። 14ኢየሱስ ከጀልባው በወረደ ጊዜ ብዙ ሕዝብን አይቶ ራራላቸው፤ በሽተኞቻቸውንም ፈወሰ።
15በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፥ “ይህ ቦታ ምድረ በዳ ነው፤ ቀኑም መሽቶአል፤ ስለዚህ ሕዝቡ በአቅራቢያ ወዳሉት መንደሮች ሄደው ምግባቸውን እንዲገዙ አሰናብታቸው” አሉት።
16ኢየሱስ ግን፦ “እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው እንጂ እነርሱ እንዲሁ ሊሄዱ አይገባም!” አላቸው።
17ደቀ መዛሙርቱም “እኛ እዚህ ያለን አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ ብቻ ነው” አሉት።
18ኢየሱስም “እነርሱኑ ወደ እኔ አምጡልኝ!” አላቸው። 19ከዚህ በኋላ ሕዝቡ በመስኩ ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ አንሥቶ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና የምስጋና ጸሎት አደረገ፤ እንጀራውንም ቈርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ ዐደሉ። 20ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውን ፍርፋሪ፥ ደቀ መዛሙርቱ በዐሥራ ሁለት መሶብ ሞልተው አነሡ። 21የበሉትም ሰዎች ከሴቶችና ከሕፃናት ሌላ አምስት ሺህ ያኽል ወንዶች ነበሩ።
ኢየሱስ በባሕር ላይ እየተራመደ እንደ ሄደ
(ማር. 6፥45-52ዮሐ. 6፥15-21)
22ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፥ “እኔ ሕዝቡን እስካሰናብት ድረስ በጀልባ ተሳፈሩና ቀድማችሁኝ ወደ ማዶ ተሻገሩ፤” ሲል አዘዛቸው። 23ሕዝቡንም ካሰናበተ በኋላ ለመጸለይ ብቻውን ወደ አንድ ተራራ ላይ ወጣ፤ በመሸም ጊዜ ኢየሱስ እዚያ ብቻውን ነበር። 24በዚያን ጊዜ ጀልባዋ በባሕሩ መካከል ሆና ከምትሄድበት አቅጣጫ በተቃራኒ በሚነፍሰው ነፋስ እየተመታች ማዕበሉ ወዲያና ወዲህ ያንገላታት ነበር። 25ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት በኋላ ኢየሱስ በባሕር ላይ እየተራመደ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣ። 26ደቀ መዛሙርቱም በባሕሩ ላይ እየተራመደ ሲሄድ ባዩት ጊዜ በጣም ፈርተው ደነገጡ፤ “ይህ ምትሐት ነው!” ብለውም በፍርሃት ጮኹ።
27ኢየሱስም ወዲያውኑ “አይዞአችሁ! እኔ ነኝ፤ አትፍሩ!” አላቸው።
28በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ፥ “ጌታ ሆይ! አንተስ ከሆንክ በባሕሩ ላይ እየተራመድኩ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ!” አለው።
29ኢየሱስም “ና!” አለው። ስለዚህ ጴጥሮስ ከጀልባው ወርዶ ወደ ኢየሱስ ለመሄድ በባሕሩ ላይ ተራመደ። 30ነገር ግን የነፋሱን ኀይል አይቶ ፈራ፤ ወደ ባሕሩ ውስጥ መስጠም በጀመረ ጊዜ “ጌታ ሆይ! አድነኝ!” ሲል ጮኸ።
31ኢየሱስ ወዲያውኑ እጁን ዘርግቶ ያዘውና፦ “አንተ እምነት የጐደለህ! ስለምን ተጠራጠርክ?” አለው።
32ኢየሱስና ጴጥሮስ ወደ ጀልባው በገቡ ጊዜ ነፋሱ ጸጥ አለ። 33በጀልባውም ውስጥ የነበሩት ሁሉ “በእርግጥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ!” ብለው ለኢየሱስ ሰገዱለት።
ኢየሱስ በጌንሳሬጥ ሕመምተኞችን መፈወሱ
(ማር. 6፥53-56)
34ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ባሕሩን ተሻግረው ወደ ጌንሳሬጥ ምድር ደረሱ። 35በዚያም አገር የነበሩ ሰዎች ኢየሱስ መሆኑን ባወቁ ጊዜ በአካባቢው ወዳሉት ስፍራዎች ተላልከው በሽተኞችን ወደ እርሱ አስመጡ። 36በሽተኞቹም የልብሱን ጫፍ ብቻ እንዲነኩ ለመኑት። የነኩትም ሁሉ ከበሽታቸው ተፈወሱ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮዎች ለየማቴዎስ ወንጌል 14