የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማ​ቴ​ዎስ ወን​ጌል 14

14
ስለ መጥምቁ ዮሐንስ መገደል
(ማር. 6፥14-29ሉቃ. 9፥7-9)
1በዚያ ዘመን የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስ የኢየሱስን ዝና ሰማ፤ 2ለሎሌዎቹም “ይህ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል፤ ስለዚህም ኃይል በእርሱ ይደረጋል፤” አለ። 3ሄሮድስ በወንድሙ በፊልጶስ ሚስት በሄሮድያዳ ምክንያት ዮሐንስን አስይዞ አሳስሮት በወህኒ አኑሮት ነበርና፤ 4ዮሐንስ “እርስዋ ለአንተ ትሆን ዘንድ አልተፈቀደም፤” ይለው ነበርና። 5ሊገድለውም ወዶ ሳለ፥ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስለ አዩት ፈራቸው። 6ነገር ግን ሄሮድስ የተወለደበት ቀን በሆነ ጊዜ፥ የሄሮድያዳ ልጅ በመካከላቸው ዘፈነች፤ ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው፤ 7ስለዚህም የምትለምነውን ሁሉ እንዲሰጣት በመሐላ ተስፋ አደረገላት። 8እርስዋም በእናትዋ ተመክራ “የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በዚህ በወጭት ስጠኝ፤” አለችው። 9ንጉሡም አዘነ፤ ነገር ግን ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ተቀምጠው ስላሉት ሰዎች እንዲሰጡአት፤ አዘዘ፤ 10ልኮም የዮሐንስን ራስ በወህኒ አስቆረጠው። 11ራሱንም በወጭት አምጥተው ለብላቴናይቱ ሰጡአት፤ ወደ እናትዋም ወሰደችው። 12ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው በድኑን ወሰዱና ቀበሩት፤ መጥተውም ለኢየሱስ አወሩለት።
ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን እንደመገበ
(ማር. 6፥30-44ሉቃ. 9፥10-17ዮሐ. 6፥1-12)
13ኢየሱስም በሰማ ጊዜ ከዚያ ብቻውን ወደ ምድረ በዳ በታንኳ ፈቀቅ አለ፤ ሕዝቡም ሰምተው ከከተማዎቹ በእግር ተከተሉት። 14ወጥቶም ብዙ ሕዝብ አየና አዘነላቸው፤ ድውዮቻቸውንም ፈወሰ። 15በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው “ቦታው ምድረ በዳ ነው፤ አሁንም ሰዓቱ አልፎአል፤ ወደ መንደሮች ሄደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ ሕዝቡን አሰናብት፤” አሉት። 16ኢየሱስም “እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው እንጂ ሊሄዱ አያስፈልግም፤” አላቸው። 17እነርሱም “ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ በቀር በዚህ የለንም፤” አሉት። 18እርሱም “እነዚያን ወደዚህ አምጡልኝ፤” አላቸው። 19ሕዝቡም በሣር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፤ እንጀራውንም ቆርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ። 20ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውንም ቁርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ አነሡ። 21ከሴቶችና ከልጆችም በቀር የበሉት አምስት ሺህ ወንዶች ያህሉ ነበር።
ኢየሱስ በባሕር ላይ እንደሔደ
(ማር. 6፥45-52ሉቃ. 6፥15-21)
22ወዲያውም ሕዝቡን ሲያሰናብት ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳይቱ ገብተው ወደ ማዶ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው። 23ሕዝቡንም አሰናብቶ ይጸልይ ዘንድ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ ብቻውን በዚያ ነበረ። 24ታንኳይቱም አሁን በባሕር መካከል ሳለች፥ ነፋስ ከወደ ፊት ነበርና በማዕበል ትጨነቅ ነበር። 25ከሌሊቱም በአራተኛው ክፍል ኢየሱስ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ። 26ደቀ መዛሙርቱም በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ “ምትሐት ነው” ብለው ታወኩ፤ በፍርሃትም ጮኹ። 27ወዲያውም ኢየሱስ ተናገራቸውና “አይዞአችሁ፤ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ፤” አላቸው።
28ጴጥሮስም መልሶ “ጌታ ሆይ! አንተስ ከሆንህ በውሃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ፤” አለው። 29እርሱም፦ ና አለው። ጴጥሮስም ከታንኳይቱ ወርዶ ወደ ኢየሱስ ሊደርስ በውሃው ላይ ሄደ። 30ነገር ግን የነፋሱን ኃይል አይቶ ፈራ፤ ሊሰጥምም በጀመረ ጊዜ “ጌታ ሆይ! አድነኝ፤” ብሎ ጮኸ። 31ወዲያውም ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና “አንተ እምነት የጎደለህ፤ ስለምን ተጠራጠርህ?” አለው። 32ወደ ታንኳይቱም በወጡ ጊዜ ነፋሱ ተወ። 33በታንኳይቱም የነበሩት “በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤” ብለው ሰገዱለት።
34ተሻግረውም ወደ ጌንሴሬጥ ምድር መጡ። 35የዚያ ቦታ ሰዎችም ባወቁት ጊዜ በዙርያው ወዳለ አገር ሁሉ ላኩ፤ ሕመምተኞችንም ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ 36የልብሱንም ጫፍ ብቻ ሊዳስሱ ይለምኑት ነበር፤ የዳሰሱትም ሁሉ ዳኑ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮዎች ለየማ​ቴ​ዎስ ወን​ጌል 14