የማቴዎስ ወንጌል 14
14
ስለ መጥምቁ ዮሐንስ መገደል
(ማር. 6፥14-29፤ ሉቃ. 9፥7-9)
1በዚያ ዘመን የአራተኛው ክፍል ገዢ የነበረው ሄሮድስ የኢየሱስን ዝና ሰማ፤ 2አገልጋዮቹንም “ይህ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ እርሱ ከሞት ተነሥቶአል፤ ኃይል በእርሱ የሚደረገውም ለዚህ ነው፤” አለ። 3#ሉቃ. 3፥19፤20።ሄሮድስ በወንድሙ በፊልጶስ ሚስት በሄሮድያዳ ምክንያት ዮሐንስን አስይዞ አሳስሮትና እስር ቤት አስገብቶት ነበርና፤ 4#ዘሌ. 18፥16፤ 20፥21።ዮሐንስ “እርሷ ለአንተ ትሆን ዘንድ ተገቢ አይደለም” ይለው ነበርና። 5ሊገድለው ይፈልግ ነበር፥ ነገር ግን ሕዝቡ እንደ ነቢይ ያዩት ስለ ነበር ፈራቸው። 6ነገር ግን ሄሮድስ የልደት ቀን በሆነ ጊዜ፥ የሄሮድያዳ ልጅ በመካከላቸው ጨፈረች፥ ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው፤ 7የምትለምነውን ሁሉ እንደሚሰጣት በመሐላ ቃል ገባላት። 8እርሷም በእናትዋ ተመክራ “የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በዚህ ሳሕን አሁን ስጠኝ” አለችው። 9ንጉሡም አዘነ፤ ነገር ግን ስለ መሐላውና ከእርሱ ጋር ተቀምጠው ስለ ነበሩት ሰዎች ሲል እንዲሰጡአት አዘዘ፤ 10ልኮም የዮሐንስን ራስ በእስር ቤት አስቆረጠው። 11ራሱን በሳሕን መጥቶ ለልጅቱ ተሰጣት፤ እርሷም ወደ እናትዋ ወሰደችው። 12ደቀ መዛሙርቱም መጥተው በድኑን ወሰደው ቀበሩት፤ መጥተውም ለኢየሱስ ነገሩት።
ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን እንደመገበ
(ማር. 6፥30-44፤ ሉቃ. 9፥10-17፤ ዮሐ. 6፥1-12)
13ኢየሱስም ይህን በሰማ ጊዜ ብቻውን ገለል ወዳለ ቦታ በታንኳ ከዚያ ፈቀቅ አለ፤ ሕዝቡም ሰምተው ከየከተማው በእግር ተከተሉት። 14በወረደም ጊዜ ብዙ ሕዝብ አየና አዘነላቸው፤ በሽተኞቻቸውንም ፈወሰ። 15በመሸም ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው “ቦታው ምድረ በዳ ነው፤ ሰዓቱም አልፎአል፤ ወደ መንደሮች ሄደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ ሕዝቡን አሰናብታቸው” አሉት። 16ኢየሱስም “መሄድ አያስፈልጋቸውም፤ እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው” አላቸው። 17እነርሱም “ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ በቀር በዚህ ምንም የለንም” አሉት። 18እርሱም “እነዚያን ወደዚህ ወደ እኔ አምጡልኝ” አላቸው። 19ሕዝቡን በሣር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፤ እንጀራውንም ቆርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ ሰጡ። 20ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውንም ቁርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ አነሡ። 21የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች ውጪ አምስት ሺህ ወንዶች ነበሩ።
ኢየሱስ በባሕር ላይ እንደሔደ
(ማር. 6፥45-52፤ ሉቃ. 6፥15-21)
22ወዲያውም ሕዝቡን እስኪያሰናብት ድረስ ደቀመዛሙርቱ ወደ ጀልባ ገብተው ወደ ማዶ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው። 23ሕዝቡንም ካሰናበተ በኋላ ለመጸለይ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ ብቻውን በዚያው ነበር። 24በዚህ ጊዜ ጀልባዋ ከምድር በጣም ርቃ ሳለች፥ ነፋስ በተቃራኒው አቅጣጫ ነበርና በማዕበል ትንገላታ ጀመር። 25ከሌሊቱም በአራተኛው ክፍል ኢየሱስ በባሕር ላይ እየተራመደ ወደ እነርሱ መጣ። 26ደቀመዛሙርቱ በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ “ምትሐት ነው” ብለው ደነገጡ፤ ከፍርሃትም የተነሣ ጮኹ። 27ወዲያው ኢየሱስ ተናገራቸው፥ “አይዞአችሁ፥ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ፤” አላቸው።
28ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! አንተስ ከሆንህ በውሃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” ሲል መለሰለት። 29እርሱም “ና” አለው። ጴጥሮስም ከጀልባዋ ወርዶ ወደ ኢየሱስ ለመሄድ በውሃው ላይ ተራመደ። 30ነገር ግን የነፋሱን ብርታት አይቶ ፈራ፤ መስጠም በጀመረም ጊዜ “ጌታ ሆይ! አድነኝ” ብሎ ጮኸ። 31ኢየሱስም ወዲያው እጁን ዘርግቶ ያዘውና “አንተ እምነት የጎደለህ፥ ለምን ተጠራጠርህ?” አለው። 32ወደ ጀልባዋ በወጡ ጊዜ ነፋሱ ፀጥ አለ። 33በጀልባዋ የነበሩትም “በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብለው ሰገዱለት።
34ተሻግረውም ወደ ጌንሴሬጥ ምድር መጡ። 35የዚያ ቦታ ሰዎችም ባወቁት ጊዜ በዙርያው ወዳለ አገር ሁሉ ላኩ፤ ሕመምተኞችንም ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ 36የልብሱን ጫፍ ብቻ ለመንካት ለመኑት፤ የነኩትም ሁሉ ተፈወሱ።
Currently Selected:
የማቴዎስ ወንጌል 14: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ