ሉቃስ 9:51-62
ሉቃስ 9:51-62 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የመውጣቱ ወራትም በቀረበ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፊቱን አቀና። በፊቱም መልእክተኞችን ላከ፤ ሄደውም ያዘጋጁለት ዘንድ ወደ ሰማርያ ከተማ ገቡ። ነገር ግን አልተቀበሉትም፤ ፊቱን ወደ ኢየሩሳሌም አቅንቶ ነበርና። ደቀ መዛሙርቱ ያዕቆብና ዮሐንስም ይህን ባዩ ጊዜ፥ “አቤቱ፥ ኤልያስ እንደ አደረገ እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጥፋቸው እንድንል ትፈቅዳለህን?” አሉት። እርሱ ግን ዘወር ብሎ፥ “ከምን መንፈስ እንደ ሆናችሁ አታውቁም” ብሎ ገሠጻቸው። የሰው ልጅ የሰውን ነፍስ ሊያድን እንጂ ሊያጠፋ አልመጣም። ወደ ሌላም መንደር ሄዱ። ከዚህ በኋላ በመንገድ ሲሄዱ አንድ ሰው፥ “መምህር፥ ወደምትሄድበት ልከተልህን?” አለው። ጌታችን ኢየሱስም “ለቀበሮዎች ጕድጓድ አላቸው፤ ለሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም” አለው። ሌላውንም፥ “ተከተለኝ” አለው፤ እርሱ ግን፥ “አቤቱ፥ በፊት ሄጄ አባቴን እንድቀብረው ፍቀድልኝ” አለው። ጌታችን ኢየሱስም፥ “ሙታኖቻቸውን ይቀብሩ ዘንድ ሙታንን ተዉአቸው፤ አንተ ግን ሂድና የእግዚአብሔርን መንግሥት ስበክ” አለው። ሦስተኛውም፥ “አቤቱ፥ ልከተልህን? ነገር ግን ሄጄ ቤተ ሰቦችን ሁሉ እንድሰናበት ፍቀድልኝ” አለው። ጌታችን ኢየሱስም፥ “ማንም ዕርፍ ይዞ እያረሰ ወደ ኋላው የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይሆንም” አለው።
ሉቃስ 9:51-62 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሚያርግበት ጊዜ በመቃረቡ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ቈርጦ ተነሣ፤ አስቀድሞም መልእክተኞችን ወደዚያ ላከ። እነርሱም ሁኔታዎችን አስቀድመው ሊያመቻቹለት ወደ አንድ የሳምራውያን መንደር ገቡ። ሕዝቡ ግን ወደ ኢየሩሳሌም እያመራ መሆኑን ስላወቁ አልተቀበሉትም። ደቀ መዛሙርቱም ያዕቆብና ዮሐንስ ይህን ሲያዩ፣ “ጌታ ሆይ፤ ኤልያስ እንዳደረገው ሁሉ እሳት ከሰማይ ወርዶ እንዲያጠፋቸው እንድናዝዝ ትፈቅዳለህን?” አሉት። ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ገሠጻቸውና፣ እርሱና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ሌላ መንደርም ሄዱ። በመንገድ ሲሄዱም አንድ ሰው ቀርቦ፣ “ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” አለው። ኢየሱስም፣ “ቀበሮዎች ጕድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጐጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ዐንገቱን እንኳ የሚያስገባበት የለውም” አለው። ሌላውን ሰው ግን፣ “ተከተለኝ” አለው። ሰውየውም፣ “ጌታ ሆይ፤ አስቀድሜ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ” አለው። ኢየሱስም፣ “ሙታን ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ተዋቸው፤ አንተ ግን ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት ስበክ” አለው። ሌላ ሰው ደግሞ፣ “ጌታ ሆይ፤ መከተልስ እከተልሃለሁ፤ ነገር ግን ልመለስና መጀመሪያ የቤቴን ሰዎች እንድሰናበት ፍቀድልኝ” አለ። ኢየሱስ ግን፣ “ዕርፍ ጨብጦ ወደ ኋላ የሚመለከት ሰው ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም” አለው።
ሉቃስ 9:51-62 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የሚወጣበትም ወራት በቀረበ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፊቱን አቀና፥ በፊቱም መልክተኞችን ሰደደ። ሄደውም ሊያሰናዱለት ወደ አንድ ወደ ሳምራውያን መንደር ገቡ፤ ፊቱም ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድ ስለ ነበረ አልተቀበሉትም። ደቀ መዛሙርቱም ያዕቆብና ዮሐንስ አይተው፦ ጌታ ሆይ፥ ኤልያስ ደግሞ እንዳደረገ እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጥፋቸው እንል ዘንድ ትወዳለህን? አሉት። እርሱ ግን ዘወር ብሎ ገሠጻቸውና፦ ምን ዓይነት መንፈስ እንደ ሆነላችሁ አታውቁም፤ የሰው ልጅ የሰውን ነፍስ ሊያድን እንጂ ሊያጠፋ አልመጣም አለ። ወደ ሌላ መንደርም ሄዱ። እነርሱም በመንገድ ሲሄዱ አንድ ሰው፦ ጌታ ሆይ፥ ወደ ምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ አለው። ኢየሱስም፦ ለቀበሮዎች ጕድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም አለው። ሌላውንም፦ ተከተለኝ አለው። እርሱ ግን፦ ጌታ ሆይ አስቀድሜ ልሂድና አባቴን እቀብር ዘንድ ፍቀድልኝ አለ። ኢየሱስም፦ ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው፤ አንተስ ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት ስበክ አለው። ደግሞ ሌላው፦ ጌታ ሆይ እከተልሃለሁ፤ ነገር ግን አስቀድሜ ከቤቴ ሰዎች እንድሰናበት ፍቀድልኝ አለ። ኢየሱስ ግን፦ ማንም ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም አለው።
ሉቃስ 9:51-62 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ የሚያርግበት ቀን በተቃረበ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ቈርጦ ተነሣ። ከእርሱ በፊት ቀድመው የሚሄዱትንም መልእክተኞች ላከ፤ እነርሱም ሁሉን ነገር ለማዘጋጀት በሰማርያ ወደምትገኘው ወደ አንዲት መንደር ሄዱ። ነገር ግን እርሱ በዚያ አልፎ ወደ ኢየሩሳሌም የሚሄድ መሆኑን ዐውቀው ስለ ነበር የዚያች መንደር ሰዎች ሊቀበሉት አልፈለጉም። ደቀ መዛሙርቱ ያዕቆብና ዮሐንስ ይህን ባዩ ጊዜ፥ “ጌታ ሆይ! ከሰማይ እሳት ወርዶ እነዚህን ሰዎች ያቃጥላቸው ዘንድ እንድናዝዝ ትፈቅዳለህን?” አሉት። ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ መለስ ብሎ ገሠጻቸው። [እናንተ ከምን ዐይነት መንፈስ እንደ ሆናችሁ አታውቁም፤ የሰው ልጅ የመጣው የሰውን ሕይወት ለማዳን ነው እንጂ፥ ለማጥፋት አይደለም።] ከዚያም ተነሥተው ወደ ሌላ መንደር ሄዱ። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ጒዞ ቀጥለው በመንገድ ላይ ሳሉ አንድ ሰው ኢየሱስን “እኔ ወደምትሄድበት ሁሉ ልከተልህ እፈልጋለሁ፤” አለው። ኢየሱስም “ቀበሮዎች ጒድጓድ አላቸው፤ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን እንኳ አስጠግቶ የሚያሳርፍበት ስፍራ የለውም፤” ሲል መለሰለት። ሌላውንም ሰው “ተከተለኝ!” አለው። ሰውየው ግን “ጌታ ሆይ! መጀመሪያ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ፤” አለው። ኢየሱስም “ሙታንን ተዋቸው፤ ሙታኖቻቸውን ይቅበሩ፤ አንተ ግን ሂድና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት አስተምር!” ሲል መለሰለት። አንድ ሌላ ሰው ደግሞ “ጌታ ሆይ፥ እኔ ልከተልህ እፈልጋለሁ፤ ነገር ግን መጀመሪያ ሄጄ ቤተሰቤን እንድሰናበት ፍቀድልኝ፤” አለው። ኢየሱስም “ለማረስ በእጁ ዕርፍ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ሰው ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም፤” ሲል መለሰለት።
ሉቃስ 9:51-62 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስ የሚያርግበት ወራት በቀረበ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፊቱን አቀና፤ እርሱም አስቀድሞ መልክተኞችን ላከ። ሄደውም ሊያሰናዱለት ወደ አንዲት የሳምራውያን መንደር ገቡ፤ ነገር ግን ወደ ኢየሩሳሌም ሊሄድ ፊቱን አቅንቶ ስለ ነበረ የመንደሩ ሰዎች አልተቀበሉትም። ደቀመዛሙርቱ ያዕቆብና ዮሐንስ አይተው፦ “ጌታ ሆይ! ከሰማይ እሳት ወርዶ እንዲበላቸው እንድናዝዝ ትወዳለህን?” አሉት። እርሱ ግን ዘወር ብሎ ገሠጻቸው። ወደ ሌላ መንደርም ሄዱ። እነርሱም በመንገድ ሲሄዱ ሳሉ አንድ ሰው ኢየሱስን፦ “አንተ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ፤” አለው። ኢየሱስም፦ “ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች ጎጆ አላቸው፤ ለሰው ልጅ ግን ራሱን እንኳ የሚያሳርፍበት ምንም ስፍራ የለውም፤” አለው። ሌላውንም፦ “ተከተለኝ፤” አለው። እርሱ ግን፦ “ጌታ ሆይ! መጀመሪያ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ፤” አለ። ኢየሱስም፦ “ሙታኖቻቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው፤ አንተስ ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት አስተምር፤” አለው። እንዲሁም ሌላው፦ “ጌታ ሆይ! እከተልሃለሁ፤ ነገር ግን መጀመሪያ ሄጄ በቤቴ ያሉትን እንድሰናበት ፍቀድልኝ፥” አለ። ኢየሱስ ግን፦ “የሞፈሩን ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ማንም ሰው ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም፤” አለው።