ሉቃስ 9:46-50
ሉቃስ 9:46-50 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እርስ በርሳቸውም ከእነርሱ ማን እንደሚበልጥ ዐሰቡ። ጌታችን ኢየሱስም በልቡናቸው የሚያስቡትን ዐወቀባቸውና አንድ ሕፃን ወስዶ በመካከላቸው አቆመው። እንዲህም አላቸው፥ “በስሜ እንደዚህ ያለውን ሕፃን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፤ ራሱን ከሁሉ ዝቅ የሚያደርግ እርሱ ታላቅ ይሆናል።” ዮሐንስም መልሶ፥ “መምህር ሆይ፥ በስምህ ጋኔን ሲያወጣ ያየነው አንድ ሰው አለ፤ ከእኛም ጋር አልተከተለህምና ከለከልነው፤” አለው። ጌታችን ኢየሱስም፥ “አትከልክሉት፤ ባለጋራችሁ ካልሆነ ባልንጀራችሁ ነውና” አላቸው።
ሉቃስ 9:46-50 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከእነርሱ ማን እንደሚበልጥ በደቀ መዛሙርቱ መካከል ክርክር ተነሣ። ኢየሱስም የልባቸውን ሐሳብ ተረድቶ፣ አንድ ሕፃን ይዞ በአጠገቡ አቆመ፤ እንዲህም አላቸው፤ “ይህን ሕፃን በስሜ የሚቀበል ማንም ቢኖር እኔን ይቀበላል፤ እኔን የሚቀበል ደግሞ የላከኝን ይቀበላል፤ ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ከሁሉ ይበልጣልና።” ዮሐንስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያወጣ አየን፤ ከእኛ ጋር ሆኖ ስለማይከተል ልንከለክለው ሞከርን” አለው። ኢየሱስም፣ “አትከልክሉት፤ የማይቃወማችሁ ሁሉ እርሱ ከእናንተ ጋር ነውና” አለው።
ሉቃስ 9:46-50 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከእነርሱም ማን እንዲበልጥ ክርክር ተነሣባቸው። ኢየሱስም የልባቸውን አሳብ አውቆ ሕፃንን ያዘ፤ በአጠገቡም አቁሞ፦ ማንም ይህን ሕፃን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ የሚቀበለኝም ሁሉ የላከኝን ይቀበላል፤ ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ታላቅ ነውና አላቸው። ዮሐንስም መልሶ፦ አቤቱ፥ አንድ ሰው በስምህ አጋንንትን ሲያወጣ አየነው፥ ከእኛ ጋርም ስለማይከተል ከለከልነው አለው። ኢየሱስ ግን፦ የማይቃወማችሁ ከእናንተ ጋር ነውና አትከልክሉት አለው።
ሉቃስ 9:46-50 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ደቀ መዛሙርቱ “ከእኛ ከሁላችን የሚበልጥ ማን ነው?” በማለት ክርክር አንሥተው ነበር። ኢየሱስ ግን የልባቸውን ሐሳብ ዐውቆ አንድ ሕፃን ልጅ አመጣና በአጠገቡ አቆመው፤ እርሱም “ይህን ሕፃን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል ሁሉ የላከኝን ይቀበላል። ከእናንተ መካከል ከሁላችሁም የሚያንስ እርሱ ከሁሉ የሚበልጥ ይሆናል፤” አላቸው። ከዚህም በኋላ ዮሐንስ ኢየሱስን፥ “መምህር ሆይ፥ አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያወጣ አየነው፤ ነገር ግን ከእኛ ጋር ስላልሆነ ከለከልነው፤” አለ። ኢየሱስም “የማይቃወማችሁ ሁሉ ከእናንተ ጋር ስለ ሆነ ተዉ፤ አትከልክሉት!” አለ።
ሉቃስ 9:46-50 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከእነርሱም መካከል ማን እንደሚበልጥ በእነርሱ ዘንድ ክርክር ተነሣ። ኢየሱስም የልባቸውን አሳብ አውቆ አንድ ሕፃን ወሰደና፥ በአጠገቡም አቁሞት፦ “ማንም ይህን ሕፃን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ የሚቀበለኝም ሁሉ የላከኝን ይቀበላል፤ በእናንተ መካከል ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ታላቅ ነውና፤” አላቸው። ዮሐንስም መልሶ፦ “አቤቱ! አንድ ሰው በስምህ አጋንንትን ሲያወጣ አየነው፤ ከእኛ ጋርም ስለማይከተል ከለከልነው” አለው። ኢየሱስ ግን፦ “የማይቃወማችሁ ከእናንተ ጋር ነውና አትከልክሉት፤” አለው።