ሉቃስ 9:23-29
ሉቃስ 9:23-29 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም ለሁሉም እንዲህ አላቸው፤ “በኋላዬ ሊመጣ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም በየዕለቱ ተሸክሞ ይከተለኝ፤ ምክንያቱም ነፍሱን ሊያድናት የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፤ ነፍሱን ስለ እኔ ብሎ የሚያጠፋት ግን ያድናታል። ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ወይም ቢያጐድል ጥቅሙ ምንድን ነው? ማንም በእኔና በቃሌ ቢያፍር፣ የሰው ልጅ በራሱ ክብር እንዲሁም በአብና በቅዱሳን መላእክት ክብር ሲመጣ ያፍርበታል። እውነት እላችኋለሁ፤ እዚህ ከቆሙት መካከል የእግዚአብሔርን መንግሥት ሳያዩ ሞትን የማይቀምሱ ሰዎች አሉ።” ኢየሱስ ይህን ከተናገረ ከስምንት ቀን ያህል በኋላ ጴጥሮስን፣ ዮሐንስንና ያዕቆብን ይዞ ሊጸልይ ወደ አንድ ተራራ ወጣ። በመጸለይ ላይ እንዳለም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም እንደ መብረቅ የሚያንጸባርቅ ነጭ ሆነ።
ሉቃስ 9:23-29 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሁሉንም እንዲህ አላቸው፥ “ሊከተለኝ የሚወድ ሰው ራሱን ይካድ፤ ጨክኖም የሞቱን መስቀል ይሸከም፤ ዕለት ዕለትም ይከተለኝ። ሰውነቱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ይጥላታል፤ ስለ እኔ ሰውነቱን የጣለ ግን ያድናታል። ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ነፍሱንም ካጣ ምን ይረባዋል? በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ የሰው ልጅ በክብሩ፥ በአባቱም ክብር፥ ቅዱሳንመላእክትን አስከትሎ ሲመጣ ያፍርበታል። እውነት እላችኋለሁ፤ በዚህ ከቆሙት የእግዚአብሔርን መንግሥት እስኪያዩአት ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አሉ።” ከዚህም ነገር በኋላ በስምንተኛው ቀን ጌታችን ኢየሱስ ጴጥሮስን፥ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞአቸው ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም ነጭ ሆነ፤ እንደ መብረቅም አብለጨለጨ።
ሉቃስ 9:23-29 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ለሁሉም እንዲህ አላቸው፦ በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፤ ስለ እኔ ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን እርሱ ያድናታል። ሰው ዓለሙን ሁሉ አትርፎ ራሱን ቢያጠፋ ወይም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ በክብሩ በአባቱና በቅዱሳን መላእክቱ ክብርም ሲመጣ በእርሱ ያፍርበታል። እውነት እላችኋለሁ፥ በዚህ ከሚቆሙት ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት እስኪያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ። ከዚህም ቃል በኋላ ስምንት ቀን ያህል ቈይቶ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ያዕቆብንም ይዞ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም ተብለጭልጮ ነጭ ሆነ።
ሉቃስ 9:23-29 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ለሁሉም ደግሞ እንዲህ አላቸው፦ “ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ በየቀኑም መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ፤ ከእኔ ይልቅ ለሕይወቱ የሚሳሳ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ግን ያድናታል። ሰው የዓለምን ሀብት ሁሉ ቢያገኝ፥ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ምን ይጠቅመዋል? በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ የሰው ልጅም በራሱ ክብርና በአባቱ ክብር፥ እንዲሁም በቅዱሳን መላእክቱ ክብር በሚመጣበት ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል። በእውነት እላችኋለሁ፤ አሁን እዚህ ካሉት መካከል የእግዚአብሔር መንግሥት ስትመጣ እስኪያዩ ድረስ የማይሞቱ አንዳንዶች አሉ።” ኢየሱስ ይህን ከተናገረ ከስምንት ቀን በኋላ ጴጥሮስን፥ ዮሐንስንና ያዕቆብን አስከትሎ ለመጸለይ ወደ አንድ ተራራ ላይ ወጣ። በሚጸልይበትም ጊዜ መልኩ ተለወጠ፤ ልብሱም ነጭ ሆኖ አንጸባረቀ፤
ሉቃስ 9:23-29 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ለሁሉም እንዲህ አላቸው፦ “ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር፥ ራሱን ይካድ፤ በየዕለቱም መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፤ ስለ እኔ ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን እርሱ ያድናታል። ሰው ዓለሙን ሁሉ አትርፎ ራሱን ግን ቢያጠፋ ወይም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? በእኔና በቃሎቼ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ በክብሩና በአባቱ ክብር እንዲሁም በቅዱሳን መላእክቱ ክብር በሚመጣበት ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል። እውነት እላችኋለሁ፤ በዚህ ከቆሙት አንዳንዶች የእግዚአብሔርን መንግሥት እስኪያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አሉ።” ኢየሱስም እነዚህን ቃላት ከተናገረ በኋላ፥ ስምንት ቀን ያህል ቈይቶ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ያዕቆብንም ይዞ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም እንደ መብረቅ ፀዳል አብረቅርቆ ነጭ ሆነ።