የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሉቃስ 22:39-71

ሉቃስ 22:39-71 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢየሱስ እንደ ልማዱ ወጥቶ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። እዚያም በደረሱ ጊዜ፣ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ” አላቸው። ከእነርሱም የድንጋይ ውርወራ ያህል ርቆ ተንበርክኮ ጸለየ፤ እንዲህም አለ፤ “አባት ሆይ፤ ፈቃድህ ከሆነ፣ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም።” መልአክም ከሰማይ ተገልጦለት አበረታታው። እጅግ ተጨንቆም በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ ላቡም እንደ ደም ነጠብጣብ ወደ ምድር ይፈስስ ነበር። ከጸሎትም ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣ፤ እነርሱም ከሐዘን የተነሣ ተኝተው አገኛቸው፣ “ለምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሥታችሁ ጸልዩ” አላቸው። እርሱም ገና እየተነጋገረ ሳለ፣ ብዙ ሰዎች መጡ፤ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ የተባለውም ሰው ይመራቸው ነበር፤ ሊስመውም ወደ ኢየሱስ ተጠጋ። ኢየሱስ ግን፣ “ይሁዳ ሆይ፤ የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው። በኢየሱስ ዙሪያ የነበሩ ሰዎችም ሁኔታውን ተመልክተው “ጌታ ሆይ፤ በሰይፍ እንምታቸውን?” አሉት። ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው። ኢየሱስ ግን፣ “ተው! እዚህ ድረስም ፍቀዱ” አለ፤ የሰውየውንም ጆሮ ዳስሶ ፈወሰው። ከዚያም ኢየሱስ ሊይዙት የመጡትን የካህናት አለቆች፣ የቤተ መቅደስ ሹሞችና ሽማግሌዎችን እንዲህ አላቸው፤ “ወንበዴ እንደሚይዝ ሰው፣ ሰይፍና ቈመጥ ይዛችሁ ወጣችሁን? በየዕለቱ በቤተ መቅደስ ከእናንተ ጋራ በነበርሁ ጊዜ እጃችሁን አላነሣችሁብኝም፤ ይህ ግን ጨለማ የነገሠበት ጊዜያችሁ ነው።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስን ይዘው ወሰዱት፤ ወደ ሊቀ ካህናቱም ግቢ አስገቡት፤ ጴጥሮስም በርቀት ይከተለው ነበር። ሰዎቹ በሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ እሳት አንድደው በአንድነት ተቀምጠው ሳለ፣ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋራ ተቀምጦ ነበር። አንዲት የቤት ሠራተኛም ጴጥሮስ እሳቱ አጠገብ ተቀምጦ አየችውና ትኵር ብላ በመመልከት፣ “ይህ ሰው ደግሞ ከርሱ ጋራ ነበረ” አለች። እርሱ ግን፣ “አንቺ ሴት፤ እኔ ዐላውቀውም” ብሎ ካደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላም አንድ ሌላ ሰው አይቶት፣ “አንተም ደግሞ ከእነርሱ አንዱ ነህ” አለው። ጴጥሮስ ግን፣ “አንተ ሰው፤ እኔ አይደለሁም” አለ። አንድ ሰዓት ያህል ቈይቶም፣ ሌላ ሰው በርግጠኛነት፣ “ይህ ሰው የገሊላ ሰው ስለ ሆነ በእውነት ከርሱ ጋራ ነበረ” አለ። ጴጥሮስ ግን፣ “አንተ ሰው፤ የምትለውን እኔ አላውቅም” አለ፤ ይህንም ተናግሮ ገና ሳይጨርስ ዶሮ ጮኸ። ጌታም መለስ ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው፤ ጴጥሮስም፣ “ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ብሎ ጌታ የተናገረው ቃል ትዝ አለው። ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ። ኢየሱስን አስረው ይጠብቁት የነበሩት ሰዎችም ያፌዙበትና ይመቱት ጀመር፤ ዐይኑንም ሸፍነው፣ “ትንቢት ተናገር! ማነው የመታህ?” እያሉ ይጠይቁት ነበር። ሌላም ብዙ የስድብ ቃል እየተናገሩ ያቃልሉት ነበር። በነጋም ጊዜ፣ የሕዝብ ሽማግሌዎች፣ የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ተሰበሰቡ፤ ኢየሱስንም በሸንጓቸው ፊት አቀረቡት። እነርሱም፣ “አንተ ክርስቶስ ነህን? እስኪ ንገረን” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ብነግራችሁ አታምኑኝም፤ ብጠይቃችሁም አትመልሱም። ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኀይል ቀኝ ይቀመጣል።” በዚህ ጊዜ ሁሉም፣ “ታዲያ፣ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን?” አሉት። እርሱም፣ “መሆኔን እኮ እናንተው ተናገራችሁት” አላቸው። እነርሱም፣ “ከእንግዲህ ሌላ ምስክር ምን ያስፈልገናል? ራሳችን ከገዛ አንደበቱ ሰምተናልና” አሉ።

ሉቃስ 22:39-71 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ወጥ​ቶም እን​ዳ​ስ​ለ​መ​ደው ይጸ​ልይ ዘንድ ወደ ደብረ ዘይት ሄደ፤ ደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱም ተከ​ተ​ሉት። ከዚ​ያም ደርሶ፥ “ወደ መከራ እን​ዳ​ት​ገቡ ጸልዩ” አላ​ቸው። የድ​ን​ጋይ ውር​ወራ ያህ​ልም ከእ​ነ​ርሱ ፈቀቅ ብሎ እየ​ሰ​ገደ ጸለየ። እን​ዲ​ህም አለ፥ “አባት ሆይ፥ ብት​ፈ​ቅ​ድስ ይህን ጽዋ ከእኔ አሳ​ል​ፈው፤ ነገር ግን የአ​ንተ ፈቃድ ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ አይ​ሁን።” የሚ​ያ​በ​ረ​ታ​ታው የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መል​አ​ክም ከሰ​ማይ ታየው። ፈራ፤ መላ​ል​ሶም ጸለየ፤ ላቡም በም​ድር ላይ እን​ደ​ሚ​ወ​ርድ እንደ ደም ነጠ​ብ​ጣብ ሆነ። ከሚ​ጸ​ል​ይ​በ​ትም ተነ​ሥቶ ወደ ደቀ መዛ​ሙ​ርቱ ሄደ፤ ከኀ​ዘ​ንም የተ​ነሣ ተኝ​ተው አገ​ኛ​ቸው። “ስለ ምን ትተ​ኛ​ላ​ችሁ? ወደ ፈተና እን​ዳ​ት​ገቡ ተነ​ሡና ጸልዩ” አላ​ቸው። ይህ​ንም ሲነ​ግ​ራ​ቸው ሕዝቡ ደረሱ፤ ከዐ​ሥራ ሁለቱ ደቀ መዛ​ሙ​ርቱ አንዱ ይሁ​ዳም ይመ​ራ​ቸው ነበር፤ ወደ ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ቀርቦ ሳመው፤ የሰ​ጣ​ቸ​ውም ምል​ክት ይህ ነበር፤ “የም​ስ​መው እርሱ ነውና እር​ሱን አጽ​ን​ታ​ችሁ ያዙት” አላ​ቸው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ይሁ​ዳን፥ “በመ​ሳም የሰ​ውን ልጅ አሳ​ል​ፈህ ትሰ​ጠ​ዋ​ለ​ህን?” አለው። አብ​ረ​ውት የነ​በ​ሩ​ትም የሆ​ነ​ውን ባዩ ጊዜ፥ ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስን፥ “አቤቱ፥ በሰ​ይፍ ልን​መ​ታ​ቸው ትፈ​ቅ​ዳ​ለ​ህን?” አሉት። ከእ​ነ​ር​ሱም አንዱ የሊቀ ካህ​ና​ቱን አገ​ል​ጋይ መታው፤ ቀኝ ጆሮ​ው​ንም ቈረ​ጠው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም መልሶ፥ “ይህ​ንስ ተው” አለ፤ ወዲ​ያ​ውም ጆሮ​ውን ዳስሶ አዳ​ነው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ሊይ​ዙት ወደ እርሱ የመ​ጡ​ትን የካ​ህ​ናት አለ​ቆ​ችን፥ የቤተ መቅ​ደስ ሹሞ​ች​ንና ሽማ​ግ​ሌ​ዎ​ችን እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “ሌባን እን​ደ​ም​ት​ይዙ በሰ​ይ​ፍና በጎ​መድ ልት​ይ​ዙኝ መጣ​ች​ሁን? ዘወ​ት​ርም ከእ​ና​ንተ ጋር በቤተ መቅ​ደስ ስኖር እጃ​ች​ሁን እንኳ አል​ዘ​ረ​ጋ​ች​ሁ​ብ​ኝም፤ ነገር ግን ጊዜ​ያ​ችሁ ይህ ነው፤ የጨ​ለ​ማው አበ​ጋ​ዝም ሥል​ጣኑ ይህ ነው።” ይዘ​ውም ወደ ሊቀ ካህ​ናቱ ቤት ወሰ​ዱት፤ ጴጥ​ሮ​ስም ከሩቅ ይከ​ተ​ለው ነበር። በግ​ቢ​ውም ውስጥ እሳት አን​ድ​ደው ተቀ​መጡ፤ ጴጥ​ሮ​ስም አብ​ሮ​አ​ቸው በመ​ካ​ከ​ላ​ቸው ተቀ​መጠ። በእ​ሳ​ቱም ብር​ሃን በኩል ተቀ​ምጦ ሳለ አን​ዲት ብላ​ቴና አየ​ችው፤ እርሱ መሆ​ኑ​ንም ለየ​ች​ውና፥ “ይህም ከእ​ርሱ ጋር ነበር” አለች። እርሱ ግን፥ “ሴትዮ! የም​ት​ዪ​ውን አላ​ው​ቅም” ብሎ ካደ። ከጥ​ቂት ጊዜም በኋላ ሌላ ሰው አየ​ውና፥ “አን​ተም ከእ​ነ​ርሱ ወገን ነህ” አለው፤ ጴጥ​ሮስ ግን፥ “አንተ ሰው! እኔ አይ​ደ​ለ​ሁም” አለው። አን​ዲት ሰዓት ያህ​ልም ቈይቶ አንድ ሌላ ሰው፥ “ይህም በእ​ው​ነት ከእ​ርሱ ጋር ነበረ፤ ሰው​የ​ውም የገ​ሊላ ሰው ነው” ብሎ አስ​ጨ​ነ​ቀው። ጴጥ​ሮስ ግን፥ “አንተ ሰው! የም​ት​ለ​ውን አላ​ው​ቅም” አለው፤ እር​ሱም ይህን ሲና​ገር ያን​ጊዜ ዶሮ ጮኸ። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ዘወር ብሎ ጴጥ​ሮ​ስን አየው፤ ጴጥ​ሮ​ስም፥ “ዛሬ ዶሮ ሳይ​ጮኽ ሦስት ጊዜ ትክ​ደ​ኛ​ለህ” ያለ​ውን የጌ​ታ​ች​ንን ቃል ዐሰበ። ጴጥ​ሮ​ስም ወደ ውጭ ወጥቶ መራራ ልቅ​ሶን አለ​ቀሰ። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስን ይዘ​ውት የነ​በ​ሩት ሰዎ​ችም ይዘ​ባ​በ​ቱ​በ​ትና ይደ​በ​ድ​ቡት ነበር። ሸፍ​ነ​ውም ፊቱን በጥፊ ይመ​ቱት ነበር፤ “ፊት​ህን በጥፊ የመ​ታህ ማነው? ንገ​ረን” እያ​ሉም ይጠ​ይ​ቁት ነበር። ሌላም ብዙ ነገር እየ​ተ​ሳ​ደቡ በእ​ርሱ ላይ ይና​ገሩ ነበር። በነ​ጋም ጊዜ፥ የካ​ህ​ናት አለ​ቆች፥ ጻፎ​ችና የሕ​ዝቡ ሽማ​ግ​ሌ​ዎች ተሰ​ብ​ስ​በው ወደ ሸን​ጎ​አ​ቸው ወሰ​ዱት። “አንተ ክር​ስ​ቶስ እንደ ሆንህ በግ​ልጥ ንገ​ረን” አሉት፤ እር​ሱም እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “ብነ​ግ​ራ​ች​ሁም አታ​ም​ኑ​ኝም። ብጠ​ይ​ቃ​ች​ሁም አት​መ​ል​ሱ​ል​ኝም፤ ወይም አት​ተ​ዉ​ኝም። ነገር ግን ከእ​ን​ግ​ዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ኀይል ቀኝ ይቀ​መ​ጣል።” ሁሉም፥ “እን​ግ​ዲ​ያስ አንተ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልጅ ነህን?” አሉት፤ እር​ሱም፥ “እኔ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልጅ እንደ ሆንሁ እና​ንተ ትላ​ላ​ችሁ” አላ​ቸው። እነ​ር​ሱም፥ “ስለ እርሱ ምን ምስ​ክር እን​ሻ​ለን? እኛ ራሳ​ችን ሲና​ገር ሰም​ተ​ናል” አሉ።

ሉቃስ 22:39-71 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ወጥቶም እንደ ልማዱ ወደ ደብረ ዘይት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ደግሞ ተከተሉት። ወደ ስፍራውም ደርሶ፦ ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ አላቸው። ከእነርሱም የድንጋይ ውርወራ የሚያህል ራቀ፥ ተንበርክኮም፦ አባት ሆይ፥ ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ እያለ ይጸልይ ነበር። ከሰማይም መጥቶ የሚያበረታ መልአክ ታየው። በፍርሃትም ሲጣጣር አጽንቶ ይጸልይ ነበር፤ ወዙም በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ ነበረ። ከጸሎትም ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣና ከኀዘን የተነሣ ተኝተው ሲያገኛቸው፦ ስለ ምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሥታችሁ ጸልዩ አላቸው። ገናም ሲናገር እነሆ፥ ሰዎች መጡ፤ ከአሥራ ሁለቱ አንዱም ይሁዳ የሚባለው ይቀድማቸው ነበር፥ ሊስመውም ወደ ኢየሱስ ቀረበ። ኢየሱስ ግን፦ ይሁዳ ሆይ፥ በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጣለህን? አለው። በዙሪያውም የነበሩት የሚሆነውን ባዩ ጊዜ፦ ጌታ ሆይ፥ በሰይፍ እንምታቸውን? አሉት። ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው። ኢየሱስ ግን መልሶ፦ ይህንስ ፍቀዱ አለ፤ ጆሮውንም ዳስሶ ፈወሰው። ኢየሱስም ወደ እርሱ ለመጡበት ለካህናት አለቆችና ለመቅደስ አዛዦች ለሽማግሌዎችም፦ ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ወጣችሁን? በመቅደስ ዕለት ዕለት ከእናንተ ጋር ስሆን እጆቻችሁን አልዘረጋችሁብኝም፤ ይህ ግን ጊዜያችሁና የጨለማው ሥልጣን ነው አላቸው። ይዘውም ወሰዱት ወደ ሊቀ ካህናት ቤትም አገቡት፤ ጴጥሮስም ርቆ ይከተለው ነበር። በግቢ መካከልም እሳት አንድደው በአንድነት ተቀምጠው ሳሉ ጴጥሮስ በመካከላቸው ተቀመጠ። በብርሃኑም በኩል ተቀምጦ ሳለ አንዲት ገረድ አየችውና ትኵር ብላ፦ ይህ ደግሞ ከእርሱ ጋር ነበረ አለች። እርሱ ግን፦ አንቺ ሴት፥ አላውቀውም ብሎ ካደ። ከጥቂት ጊዜም በኋላ ሌላው አይቶት፦ አንተ ደግሞ ከእነርሱ ወገን ነህ አለው። ጴጥሮስ ግን፦ አንተ ሰው፥ እኔ አይደለሁም አለ። አንድ ሰዓትም የሚያህል ቆይቶ ሌላው አስረግጦ፦ እርሱ የገሊላ ሰው ነውና በእውነት ይህ ደግሞ ከእርሱ ጋር ነበረ አለ። ጴጥሮስ ግን፦ አንተ ሰው፥ የምትለውን አላውቅም አለ። ያን ጊዜም ገና ሲናገር ዶሮ ጮኸ። ጌታም ዘወር ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው፤ ጴጥሮስም፦ ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ እንዳለው የጌታ ቃል ትዝ አለው። ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ። ኢየሱስንም የያዙት ሰዎች ይዘብቱበትና ይደበድቡት ነበር፤ ሸፍነውም ፊቱን ይመቱት ነበርና፦ በጥፊ የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገር እያሉ ይጠይቁት ነበር። ሌላም ብዙ ነገር እየተሳደቡ በእርሱ ላይ ይናገሩ ነበር። በነጋም ጊዜ የሕዝቡ ሽማግሌዎችና የካህናት አለቆች ጻፎችም ተሰብስበው ወደ ሸንጎአቸው ወሰዱትና ክርስቶስ አንተ ነህን? ንገረን አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ ብነግራችሁ አታምኑም፤ ብጠይቅም አትመልሱልኝም አትፈቱኝምም። ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኃይል ቀኝ ይቀመጣል። ሁላቸውም፦ እንግዲያስ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን? አሉት። እርሱም፦ እኔ እንደ ሆንሁ እናንተ ትላላችሁ አላቸው። እነርሱም፦ ራሳችን ከአፉ ሰምተናልና ከእንግዲህ ወዲህ ምን ምስክር ያስፈልገናል? አሉ።

ሉቃስ 22:39-71 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስ ከከተማ ወጥቶ እንደ ልማዱ ወደ ደብረ ዘይት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም አብረውት ሄዱ። እዚያም በደረሱ ጊዜ ኢየሱስ፦ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ” አላቸው። 41 ከዚህ በኋላ የድንጋይ ውርወራ ያኽል ከእነርሱ ራቅ ብሎ ሄደ፤ ተንበርክኮም እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “አባት ሆይ! ፈቃድህ ቢሆን ይህን የመከራ ጽዋ ከእኔ አርቅልኝ፤ ግን የአንተ ፈቃድ ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ አይሁን።” በዚያን ጊዜ የሚያበረታታው መልአክ ከሰማይ መጥቶ ታየው። ልቡም በጣም ተጨንቆ በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ ላቡም እንደ ደም ሆኖ ወደ መሬት ይንጠባጠብ ነበር። ከጸሎቱ ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣ፤ ከሐዘን ብዛት የተነሣ ተኝተው አገኛቸውና እንዲህ አላቸው፤ “ስለምን ትተኛላችሁ? ይልቅስ ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሡና ጸልዩ።” ኢየሱስ ይህን ሲናገር ሳለ እነሆ፥ ብዙ ሰዎች መጡ፤ መሪያቸው ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው ይሁዳ ነበር፤ ይሁዳ ሊስመው ወደ ኢየሱስ ቀረበ። ኢየሱስ ግን “ይሁዳ ሆይ! የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው። ከኢየሱስ ጋር የነበሩት ደቀ መዛሙርት የነገሩን ሁኔታ ባዩ ጊዜ “ጌታ ሆይ! በሰይፍ እንምታቸውን?” አሉ። ከእነርሱም አንዱ የካህናት አለቃውን አገልጋይ በሰይፍ መታና ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ። ኢየሱስ ግን “ተው! እንደዚህ ያለ ነገር ደግመህ አታድርግ!” አለ፤ የሰውዬውንም ጆሮ ዳስሶ አዳነው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሊይዙት የመጡትን የካህናት አለቆች፥ የቤተ መቅደስ የዘብ አዛዦችንና የሕዝብ ሽማግሌዎችንም እንዲህ አላቸው፦ “እኔን እንደ ወንበዴ ልትይዙ ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ መጣችሁን? በየቀኑ በቤተ መቅደስ ከእናንተ ጋር ስገኝ አልያዛችሁኝም ነበር፤ አሁን ግን የእናንተ ጊዜና የጨለማው ሥልጣን ጊዜ ነው።” ከዚህ በኋላ ሰዎቹ ኢየሱስን ይዘው ወሰዱትና ወደ ካህናት አለቃው ቤት አመጡት፤ ጴጥሮስም ራቅ ብሎ ይከተለው ነበር። ሰዎቹ በግቢው ውስጥ እሳት አቀጣጥለው በአንድነት ተቀምጠው ነበር። ጴጥሮስም መጥቶ አብሮ ተቀመጠ። ጴጥሮስ በእሳቱ አጠገብ ተቀምጦ ሳለ አንዲት ገረድ በእሳቱ ብርሃን አየችው፤ ወደ እርሱ ትኲር ብላ ተመልክታም “ይህም ከኢየሱስ ጋር ነበር!” አለች። ጴጥሮስ ግን፥ “አንቺ ሴት! እኔ አላውቀውም!” ሲል ካደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ ሌላ ሰው ጴጥሮስን አየውና “አንተም ከእነርሱ አንዱ ነህ!” አለው። ጴጥሮስ ግን “አንተ ሰው! አይደለሁም!” አለ። አንድ ሰዓት ያኽል ቈይቶም አንድ ሌላ ሰው ጴጥሮስን “ይህ ሰው ገሊላዊ ነውና በእርግጥ ከእርሱ ጋር ነበረ!” በማለት አጥብቆ ተናገረ። ጴጥሮስ ግን፥ “አንተ ሰው! የምትለውን አላውቅም!” አለ። ይህን ሲናገር ሳለ ወዲያውኑ ዶሮ ጮኸ። በዚህ ጊዜ ጌታ ኢየሱስ ዞር ብሎ ጴጥሮስን አየው፤ ጴጥሮስም “ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” በማለት ጌታ ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አስታወሰ። ወደ ውጪ ወጥቶም ምርር ብሎ አለቀሰ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስን ይዘውት የነበሩ ሰዎች በእርሱ ላይ ያፌዙበትና ይደበድቡትም ነበር። ፊቱንም እየሸፈኑ፥ “ማን ነው የመታህ? ነቢይ ከሆንክ እስቲ ዕወቅ!” ይሉት ነበር። በእርሱም ላይ ብዙ ነገር እየተናገሩ ይሰድቡት ነበር። በነጋ ጊዜም የሕዝብ ሽማግሌዎች፥ የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን በአንድነት ተሰበሰቡ፤ ኢየሱስንም ወደ ሸንጎአቸው አመጡት። እንዲህም አሉት፦ “እስቲ አንተ መሲሕ ከሆንክ ንገረን፤” እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ “ብነግራችሁ አታምኑኝም፤ ጥያቄም ባቀርብላችሁ አትመልሱልኝም፤ ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በኀያሉ እግዚአብሔር ቀኝ ይቀመጣል።” ሁሉም በአንድነት “ታዲያ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም “አዎ፥ እናንተ እንዳላችሁት ነው” አላቸው። እነርሱም “እንግዲህ ምን ምስክር ያስፈልገናል? እነሆ፥ ከአፉ የወጣውን ቃል እኛ ራሳችን ሰምተናል!” አሉ።

ሉቃስ 22:39-71 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እንደ ለመደው ወጥቶም ወደ ደብረዘይት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም እንዲሁ ተከተሉት። ወደ ስፍራውም ደርሶ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ፤” አላቸው። ከእነርሱም የድንጋይ ውርወራ የሚያህል ራቀ፤ ተንበርክኮም፦ “አባት ሆይ! ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ አርቅ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን፤ የአንተ ፈቃድ ይሁን እንጂ፤” እያለ ይጸልይ ነበር። ከሰማይም የሚያበረታው መልአክ ታየው። በስቃይ ጣር ውስጥ ሆኖ በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ ላቡም ወደ መሬት እንደሚንጠባጠቡ የደም ጠብታዎች ሆኑ። ከጸሎትም ተነሥቶ ወደ ደቀመዛሙርቱ መጣና ከኀዘን የተነሣ ተኝተው ሲያገኛቸው “ለምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሡና ጸልዩ፤” አላቸው። ይህንን እየተናገረ እያለ፥ እነሆ ሰዎች መጡ፤ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ ይመራቸው ነበር፤ ሊስመውም ወደ ኢየሱስ ቀረበ። ኢየሱስ ግን “ይሁዳ ሆይ! በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው። በዙሪያውም የነበሩት የሚሆነውን ባዩ ጊዜ “ጌታ ሆይ! በሰይፍ እንምታቸውን?” አሉት። ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው። ኢየሱስ ግን፦ “ይህንስ ተው” አለ፤ ጆሮውንም ዳስሶ ፈወሰው። ኢየሱስም ወደ እርሱ ለመጡበት ለካህናት አለቆችና ለቤተ መቅደስ አዛዦች ለሽማግሌዎችም “ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ መጣችሁን? ዕለት ዕለት ከእናንተ ጋር በመቅደስ ስሆን እጆቻችሁን አልዘረጋችሁብኝም፤ ሆኖም ይህ የእናንተ ጊዜና ጨለማው የሚሰፍንበት ወቅት ነው፤” አላቸው። ይዘውም ወሰዱት፤ ወደ ሊቀ ካህናት ቤትም አስገቡት፤ ጴጥሮስም በርቀት ይከተለው ነበር። በግቢው መካከልም እሳት አንድደው፥ በአንድነት ተቀምጠው ሳሉ ጴጥሮስ በመካከላቸው ተቀመጠ። በብርሃኑም በኩል ተቀምጦ ሳለ አንዲት አገልጋይ አየችውና ትኩር ብላ “ይህም እኮ ከእርሱ ጋር ነበረ፤” አለች። እርሱ ግን “አንቺ ሴት! እኔ አላውቀውም፤” ሲል ካደ። ከጥቂት ጊዜም በኋላ ሌላ ሰው አይቶት “አንተም እኮ ከእነርሱ አንዱ ነህ፤” አለው። ጴጥሮስ ግን “አንተ ሰው! አይደለሁም፤” አለ። አንድ ሰዓትም የሚያህል ቆይቶ ሌላ ሰው “እርሱ የገሊላ ሰው ነውና በእርግጥ ከእርሱ ጋር ነበረ!” ሲል አጥብቆ ተናገረ። ጴጥሮስ ግን “አንተ ሰው! የምትለውን አላውቅም፤” አለ። ያን ጊዜም፥ ገና እየተናገረ ሳለ ዶሮ ጮኸ። ጌታም ዘወር ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው፤ ጴጥሮስም “ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤” ያለው የጌታ ቃል ትዝ አለው። ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ። ኢየሱስንም የያዙት ሰዎች ይቀልዱበትና ይደበድቡት ነበር፤ ፊቱንም እየሸፈኑ “በጥፊ የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገር፤” እያሉ ይጠይቁት ነበር። ሌላም ብዙ የስድብ ቃል በእርሱ ላይ ይናገሩ ነበር። ሲነጋም የሕዝቡ ሽማግሌዎችና የካህናት አለቆች፥ ጻፎችም ተሰብስበው ወደ ሸንጎአቸው ወሰዱትና “አንተ መሢሕ ነህን? እስቲ ንገረን፤” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው “ብነግራችሁ አታምኑም፤ ብጠይቅም አትመልሱልኝም፤ አትፈቱኝምም። ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኃይል ቀኝ ይቀመጣል።” ሁላቸውም “እንግዲያስ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን?” አሉት። እርሱም “እኔ እንደሆንሁ እናንተ እየተናገራችሁ ነው” አላቸው። እነርሱም “ራሳችን ከአፉ ሰምተናልና ከእንግዲህ ወዲህ ምን ምስክር ያስፈልገናል?” አሉ።