የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 22:39-71

የሉቃስ ወንጌል 22:39-71 አማ05

ኢየሱስ ከከተማ ወጥቶ እንደ ልማዱ ወደ ደብረ ዘይት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም አብረውት ሄዱ። እዚያም በደረሱ ጊዜ ኢየሱስ፦ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ” አላቸው። 41 ከዚህ በኋላ የድንጋይ ውርወራ ያኽል ከእነርሱ ራቅ ብሎ ሄደ፤ ተንበርክኮም እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “አባት ሆይ! ፈቃድህ ቢሆን ይህን የመከራ ጽዋ ከእኔ አርቅልኝ፤ ግን የአንተ ፈቃድ ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ አይሁን።” በዚያን ጊዜ የሚያበረታታው መልአክ ከሰማይ መጥቶ ታየው። ልቡም በጣም ተጨንቆ በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ ላቡም እንደ ደም ሆኖ ወደ መሬት ይንጠባጠብ ነበር። ከጸሎቱ ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣ፤ ከሐዘን ብዛት የተነሣ ተኝተው አገኛቸውና እንዲህ አላቸው፤ “ስለምን ትተኛላችሁ? ይልቅስ ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሡና ጸልዩ።” ኢየሱስ ይህን ሲናገር ሳለ እነሆ፥ ብዙ ሰዎች መጡ፤ መሪያቸው ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው ይሁዳ ነበር፤ ይሁዳ ሊስመው ወደ ኢየሱስ ቀረበ። ኢየሱስ ግን “ይሁዳ ሆይ! የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው። ከኢየሱስ ጋር የነበሩት ደቀ መዛሙርት የነገሩን ሁኔታ ባዩ ጊዜ “ጌታ ሆይ! በሰይፍ እንምታቸውን?” አሉ። ከእነርሱም አንዱ የካህናት አለቃውን አገልጋይ በሰይፍ መታና ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ። ኢየሱስ ግን “ተው! እንደዚህ ያለ ነገር ደግመህ አታድርግ!” አለ፤ የሰውዬውንም ጆሮ ዳስሶ አዳነው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሊይዙት የመጡትን የካህናት አለቆች፥ የቤተ መቅደስ የዘብ አዛዦችንና የሕዝብ ሽማግሌዎችንም እንዲህ አላቸው፦ “እኔን እንደ ወንበዴ ልትይዙ ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ መጣችሁን? በየቀኑ በቤተ መቅደስ ከእናንተ ጋር ስገኝ አልያዛችሁኝም ነበር፤ አሁን ግን የእናንተ ጊዜና የጨለማው ሥልጣን ጊዜ ነው።” ከዚህ በኋላ ሰዎቹ ኢየሱስን ይዘው ወሰዱትና ወደ ካህናት አለቃው ቤት አመጡት፤ ጴጥሮስም ራቅ ብሎ ይከተለው ነበር። ሰዎቹ በግቢው ውስጥ እሳት አቀጣጥለው በአንድነት ተቀምጠው ነበር። ጴጥሮስም መጥቶ አብሮ ተቀመጠ። ጴጥሮስ በእሳቱ አጠገብ ተቀምጦ ሳለ አንዲት ገረድ በእሳቱ ብርሃን አየችው፤ ወደ እርሱ ትኲር ብላ ተመልክታም “ይህም ከኢየሱስ ጋር ነበር!” አለች። ጴጥሮስ ግን፥ “አንቺ ሴት! እኔ አላውቀውም!” ሲል ካደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ ሌላ ሰው ጴጥሮስን አየውና “አንተም ከእነርሱ አንዱ ነህ!” አለው። ጴጥሮስ ግን “አንተ ሰው! አይደለሁም!” አለ። አንድ ሰዓት ያኽል ቈይቶም አንድ ሌላ ሰው ጴጥሮስን “ይህ ሰው ገሊላዊ ነውና በእርግጥ ከእርሱ ጋር ነበረ!” በማለት አጥብቆ ተናገረ። ጴጥሮስ ግን፥ “አንተ ሰው! የምትለውን አላውቅም!” አለ። ይህን ሲናገር ሳለ ወዲያውኑ ዶሮ ጮኸ። በዚህ ጊዜ ጌታ ኢየሱስ ዞር ብሎ ጴጥሮስን አየው፤ ጴጥሮስም “ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” በማለት ጌታ ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አስታወሰ። ወደ ውጪ ወጥቶም ምርር ብሎ አለቀሰ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስን ይዘውት የነበሩ ሰዎች በእርሱ ላይ ያፌዙበትና ይደበድቡትም ነበር። ፊቱንም እየሸፈኑ፥ “ማን ነው የመታህ? ነቢይ ከሆንክ እስቲ ዕወቅ!” ይሉት ነበር። በእርሱም ላይ ብዙ ነገር እየተናገሩ ይሰድቡት ነበር። በነጋ ጊዜም የሕዝብ ሽማግሌዎች፥ የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን በአንድነት ተሰበሰቡ፤ ኢየሱስንም ወደ ሸንጎአቸው አመጡት። እንዲህም አሉት፦ “እስቲ አንተ መሲሕ ከሆንክ ንገረን፤” እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ “ብነግራችሁ አታምኑኝም፤ ጥያቄም ባቀርብላችሁ አትመልሱልኝም፤ ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በኀያሉ እግዚአብሔር ቀኝ ይቀመጣል።” ሁሉም በአንድነት “ታዲያ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም “አዎ፥ እናንተ እንዳላችሁት ነው” አላቸው። እነርሱም “እንግዲህ ምን ምስክር ያስፈልገናል? እነሆ፥ ከአፉ የወጣውን ቃል እኛ ራሳችን ሰምተናል!” አሉ።