ኢየሱስ እንደ ልማዱ ወጥቶ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። እዚያም በደረሱ ጊዜ፣ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ” አላቸው። ከእነርሱም የድንጋይ ውርወራ ያህል ርቆ ተንበርክኮ ጸለየ፤ እንዲህም አለ፤ “አባት ሆይ፤ ፈቃድህ ከሆነ፣ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም።” መልአክም ከሰማይ ተገልጦለት አበረታታው። እጅግ ተጨንቆም በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ ላቡም እንደ ደም ነጠብጣብ ወደ ምድር ይፈስስ ነበር። ከጸሎትም ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣ፤ እነርሱም ከሐዘን የተነሣ ተኝተው አገኛቸው፣ “ለምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሥታችሁ ጸልዩ” አላቸው። እርሱም ገና እየተነጋገረ ሳለ፣ ብዙ ሰዎች መጡ፤ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ የተባለውም ሰው ይመራቸው ነበር፤ ሊስመውም ወደ ኢየሱስ ተጠጋ። ኢየሱስ ግን፣ “ይሁዳ ሆይ፤ የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው። በኢየሱስ ዙሪያ የነበሩ ሰዎችም ሁኔታውን ተመልክተው “ጌታ ሆይ፤ በሰይፍ እንምታቸውን?” አሉት። ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው። ኢየሱስ ግን፣ “ተው! እዚህ ድረስም ፍቀዱ” አለ፤ የሰውየውንም ጆሮ ዳስሶ ፈወሰው። ከዚያም ኢየሱስ ሊይዙት የመጡትን የካህናት አለቆች፣ የቤተ መቅደስ ሹሞችና ሽማግሌዎችን እንዲህ አላቸው፤ “ወንበዴ እንደሚይዝ ሰው፣ ሰይፍና ቈመጥ ይዛችሁ ወጣችሁን? በየዕለቱ በቤተ መቅደስ ከእናንተ ጋራ በነበርሁ ጊዜ እጃችሁን አላነሣችሁብኝም፤ ይህ ግን ጨለማ የነገሠበት ጊዜያችሁ ነው።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስን ይዘው ወሰዱት፤ ወደ ሊቀ ካህናቱም ግቢ አስገቡት፤ ጴጥሮስም በርቀት ይከተለው ነበር። ሰዎቹ በሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ እሳት አንድደው በአንድነት ተቀምጠው ሳለ፣ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋራ ተቀምጦ ነበር። አንዲት የቤት ሠራተኛም ጴጥሮስ እሳቱ አጠገብ ተቀምጦ አየችውና ትኵር ብላ በመመልከት፣ “ይህ ሰው ደግሞ ከርሱ ጋራ ነበረ” አለች። እርሱ ግን፣ “አንቺ ሴት፤ እኔ ዐላውቀውም” ብሎ ካደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላም አንድ ሌላ ሰው አይቶት፣ “አንተም ደግሞ ከእነርሱ አንዱ ነህ” አለው። ጴጥሮስ ግን፣ “አንተ ሰው፤ እኔ አይደለሁም” አለ። አንድ ሰዓት ያህል ቈይቶም፣ ሌላ ሰው በርግጠኛነት፣ “ይህ ሰው የገሊላ ሰው ስለ ሆነ በእውነት ከርሱ ጋራ ነበረ” አለ። ጴጥሮስ ግን፣ “አንተ ሰው፤ የምትለውን እኔ አላውቅም” አለ፤ ይህንም ተናግሮ ገና ሳይጨርስ ዶሮ ጮኸ። ጌታም መለስ ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው፤ ጴጥሮስም፣ “ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ብሎ ጌታ የተናገረው ቃል ትዝ አለው። ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ። ኢየሱስን አስረው ይጠብቁት የነበሩት ሰዎችም ያፌዙበትና ይመቱት ጀመር፤ ዐይኑንም ሸፍነው፣ “ትንቢት ተናገር! ማነው የመታህ?” እያሉ ይጠይቁት ነበር። ሌላም ብዙ የስድብ ቃል እየተናገሩ ያቃልሉት ነበር። በነጋም ጊዜ፣ የሕዝብ ሽማግሌዎች፣ የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ተሰበሰቡ፤ ኢየሱስንም በሸንጓቸው ፊት አቀረቡት። እነርሱም፣ “አንተ ክርስቶስ ነህን? እስኪ ንገረን” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ብነግራችሁ አታምኑኝም፤ ብጠይቃችሁም አትመልሱም። ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኀይል ቀኝ ይቀመጣል።” በዚህ ጊዜ ሁሉም፣ “ታዲያ፣ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን?” አሉት። እርሱም፣ “መሆኔን እኮ እናንተው ተናገራችሁት” አላቸው። እነርሱም፣ “ከእንግዲህ ሌላ ምስክር ምን ያስፈልገናል? ራሳችን ከገዛ አንደበቱ ሰምተናልና” አሉ።
ሉቃስ 22 ያንብቡ
ያዳምጡ ሉቃስ 22
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሉቃስ 22:39-71
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos