የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 22:39-71

የሉቃስ ወንጌል 22:39-71 መቅካእኤ

እንደ ለመደው ወጥቶም ወደ ደብረዘይት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም እንዲሁ ተከተሉት። ወደ ስፍራውም ደርሶ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ፤” አላቸው። ከእነርሱም የድንጋይ ውርወራ የሚያህል ራቀ፤ ተንበርክኮም፦ “አባት ሆይ! ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ አርቅ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን፤ የአንተ ፈቃድ ይሁን እንጂ፤” እያለ ይጸልይ ነበር። ከሰማይም የሚያበረታው መልአክ ታየው። በስቃይ ጣር ውስጥ ሆኖ በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ ላቡም ወደ መሬት እንደሚንጠባጠቡ የደም ጠብታዎች ሆኑ። ከጸሎትም ተነሥቶ ወደ ደቀመዛሙርቱ መጣና ከኀዘን የተነሣ ተኝተው ሲያገኛቸው “ለምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሡና ጸልዩ፤” አላቸው። ይህንን እየተናገረ እያለ፥ እነሆ ሰዎች መጡ፤ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ ይመራቸው ነበር፤ ሊስመውም ወደ ኢየሱስ ቀረበ። ኢየሱስ ግን “ይሁዳ ሆይ! በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው። በዙሪያውም የነበሩት የሚሆነውን ባዩ ጊዜ “ጌታ ሆይ! በሰይፍ እንምታቸውን?” አሉት። ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው። ኢየሱስ ግን፦ “ይህንስ ተው” አለ፤ ጆሮውንም ዳስሶ ፈወሰው። ኢየሱስም ወደ እርሱ ለመጡበት ለካህናት አለቆችና ለቤተ መቅደስ አዛዦች ለሽማግሌዎችም “ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ መጣችሁን? ዕለት ዕለት ከእናንተ ጋር በመቅደስ ስሆን እጆቻችሁን አልዘረጋችሁብኝም፤ ሆኖም ይህ የእናንተ ጊዜና ጨለማው የሚሰፍንበት ወቅት ነው፤” አላቸው። ይዘውም ወሰዱት፤ ወደ ሊቀ ካህናት ቤትም አስገቡት፤ ጴጥሮስም በርቀት ይከተለው ነበር። በግቢው መካከልም እሳት አንድደው፥ በአንድነት ተቀምጠው ሳሉ ጴጥሮስ በመካከላቸው ተቀመጠ። በብርሃኑም በኩል ተቀምጦ ሳለ አንዲት አገልጋይ አየችውና ትኩር ብላ “ይህም እኮ ከእርሱ ጋር ነበረ፤” አለች። እርሱ ግን “አንቺ ሴት! እኔ አላውቀውም፤” ሲል ካደ። ከጥቂት ጊዜም በኋላ ሌላ ሰው አይቶት “አንተም እኮ ከእነርሱ አንዱ ነህ፤” አለው። ጴጥሮስ ግን “አንተ ሰው! አይደለሁም፤” አለ። አንድ ሰዓትም የሚያህል ቆይቶ ሌላ ሰው “እርሱ የገሊላ ሰው ነውና በእርግጥ ከእርሱ ጋር ነበረ!” ሲል አጥብቆ ተናገረ። ጴጥሮስ ግን “አንተ ሰው! የምትለውን አላውቅም፤” አለ። ያን ጊዜም፥ ገና እየተናገረ ሳለ ዶሮ ጮኸ። ጌታም ዘወር ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው፤ ጴጥሮስም “ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤” ያለው የጌታ ቃል ትዝ አለው። ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ። ኢየሱስንም የያዙት ሰዎች ይቀልዱበትና ይደበድቡት ነበር፤ ፊቱንም እየሸፈኑ “በጥፊ የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገር፤” እያሉ ይጠይቁት ነበር። ሌላም ብዙ የስድብ ቃል በእርሱ ላይ ይናገሩ ነበር። ሲነጋም የሕዝቡ ሽማግሌዎችና የካህናት አለቆች፥ ጻፎችም ተሰብስበው ወደ ሸንጎአቸው ወሰዱትና “አንተ መሢሕ ነህን? እስቲ ንገረን፤” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው “ብነግራችሁ አታምኑም፤ ብጠይቅም አትመልሱልኝም፤ አትፈቱኝምም። ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኃይል ቀኝ ይቀመጣል።” ሁላቸውም “እንግዲያስ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን?” አሉት። እርሱም “እኔ እንደሆንሁ እናንተ እየተናገራችሁ ነው” አላቸው። እነርሱም “ራሳችን ከአፉ ሰምተናልና ከእንግዲህ ወዲህ ምን ምስክር ያስፈልገናል?” አሉ።