ሉቃስ 1:57-79

ሉቃስ 1:57-79 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

የኤ​ል​ሣ​ቤ​ጥም የመ​ው​ለ​ጃዋ ጊዜ ደረሰ፤ ወንድ ልጅም ወለ​ደች። ዘመ​ዶ​ች​ዋና ጎረ​ቤ​ቶ​ች​ዋም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቸር​ነ​ቱን እን​ዳ​በ​ዛ​ላት በሰሙ ጊዜ ከእ​ር​ስዋ ጋር ደስ አላ​ቸው። ከዚ​ህም በኋላ በስ​ም​ን​ተ​ኛው ቀን ሕፃ​ኑን ሊገ​ዝ​ሩት መጡ፤ በአ​ባ​ቱም ስም ዘካ​ር​ያስ ብለው ጠሩት። እናቱ ግን መልሳ፥ “አይ​ሆ​ንም፥ ዮሐ​ንስ ይባል እንጂ” አለች። እነ​ር​ሱም፥ “ከዘ​መ​ዶ​ችሽ ስሙ እን​ደ​ዚህ የሚ​ባል የለም” አሉ​አት። አባ​ቱ​ንም ጠቅ​ሰው፥ “ማን ሊሉት ትወ​ዳ​ለህ?” አሉት። ብራ​ናም ለመ​ነና “ስሙ ዮሐ​ንስ ይባል” ብሎ ጻፈ፤ ሁሉም አደ​ነቁ። ያን​ጊ​ዜም አፉ ተከ​ፈተ፤ አን​ደ​በ​ቱም ተና​ገረ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም አመ​ሰ​ገነ። በዚ​ያም ሀገር ሰው ሁሉ ላይ ፍር​ሀት ሆነ፤ ይህም ነገር ሁሉ በይ​ሁዳ በተ​ራ​ራ​ማው ሀገር ሁሉ ተወራ። የሰ​ሙ​ትም ሁሉ፥ “እን​ግ​ዲህ ይህ ሕፃን ምን ይሆን?” እያሉ በል​ባ​ቸው አኖ​ሩት፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እጅ በእ​ርሱ ላይ ነበ​ረ​ችና። በአ​ባቱ በዘ​ካ​ር​ያ​ስም መን​ፈስ ቅዱስ መላ​በት፤ እን​ዲ​ህም ብሎ ትን​ቢት ተና​ገረ፦ “ይቅር ያለን፥ ለወ​ገ​ኖ​ቹም ድኅ​ነ​ትን ያደ​ረገ የእ​ስ​ራ​ኤል አም​ላክ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይመ​ስ​ገን፤ ከባ​ር​ያው ከዳ​ዊት ቤት የም​ን​ድ​ን​በ​ትን ቀንድ አስ​ነ​ሣ​ልን፤ ከጥ​ንት ጀምሮ በነ​በሩ በቅ​ዱ​ሳን በነ​ቢ​ያት አፍ እንደ ተና​ገረ። ከጠ​ላ​ቶ​ቻ​ችን እጅ፥ ከሚ​ጠ​ሉ​ንም ሁሉ እጅ ያድ​ነን ዘንድ። ቸር​ነ​ቱን ከአ​ባ​ቶ​ቻ​ችን ጋር ያደ​ርግ ዘንድ፥ ቅዱስ ኪዳ​ኑ​ንም ያስብ ዘንድ። ለአ​ባ​ታ​ችን ለአ​ብ​ር​ሃም የማ​ለ​ውን መሐላ ያስብ ዘንድ። ከጠ​ላ​ቶ​ቻ​ችን እጅ ድነን ያለ ፍር​ሀት፥ በቅ​ድ​ስ​ናና በጽ​ድቅ በፊቱ በዘ​መ​ና​ችን ሁሉ እን​ድ​ና​መ​ል​ከው ይሰ​ጠን ዘንድ። አን​ተም ሕፃን፥ የል​ዑል ነቢይ ትባ​ላ​ለህ፤ መን​ገ​ዱን ትጠ​ርግ ዘንድ በፊቱ ትሄ​ዳ​ለ​ህና። ኀጢ​አ​ታ​ቸው ይሰ​ረ​ይ​ላ​ቸው ዘንድ መድ​ኀ​ኒ​ታ​ቸ​ውን እን​ዲ​ያ​ውቁ ለአ​ሕ​ዛብ ትሰ​ጣ​ቸው ዘንድ። ከአ​ር​ያም በጐ​በ​ኘን በአ​ም​ላ​ካ​ችን በይ​ቅ​ር​ታ​ውና በቸ​ር​ነቱ። በጨ​ለ​ማና በሞት ጥላ ለነ​በ​ሩት ብር​ሃ​ኑን ያሳ​ያ​ቸው ዘንድ፥ እግ​ሮ​ቻ​ች​ን​ንም ወደ ሰላም ጎዳና ያቀና ዘንድ ወጣ።”

ሉቃስ 1:57-79 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የኤልሳቤጥም የመውለጃዋ ቀን ደረሰ፤ ወንድ ልጅም ወለደች። ጎረቤቶቿና ዘመዶቿም ጌታ ታላቅ ምሕረት እንዳደረገላት ሰሙ፤ የደስታዋም ተካፋዮች ሆኑ። በስምንተኛውም ቀን ሕፃኑን ሊገርዙት መጡ፤ በአባቱም ስም ዘካርያስ ሊሉት ፈለጉ፤ እናቱ ግን፣ “አይሆንም፤ ዮሐንስ መባል አለበት” አለች። እነርሱም፣ “ከዘመዶችሽ በዚህ ስም የተጠራ ማንም የለም” አሏት። አባቱንም ምን ስም ሊያወጣለት እንደሚፈልግ በምልክት ጠየቁት። እርሱም መጻፊያ ሰሌዳ እንዲሰጡት ለምኖ፣ “ስሙ ዮሐንስ ነው” ብሎ ጻፈ፤ ሁሉም በነገሩ ተደነቁ። ወዲያውም አፉ ተከፈተ፤ አንደበቱ ተፈታ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ መናገር ጀመረ። ጎረቤቶቹም ሁሉ በፍርሀት ተሞሉ፤ ይህም ሁሉ ነገር በደጋማው የይሁዳ ምድር ሁሉ ተወራ። ይህንም የሰሙ ሁሉ፣ “ይህ ሕፃን ምን ሊሆን ይሆን?” እያሉ ነገሩን በልባቸው ያዙ፤ የጌታ እጅ በርግጥ ከርሱ ጋራ ነበርና። የሕፃኑም አባት ዘካርያስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናገረ፤ “የእስራኤል አምላክ፣ ጌታ ይመስገን፤ መጥቶ ሕዝቡን ተቤዥቷልና። በብላቴናው በዳዊት ቤት፣ የድነት ቀንድ አስነሥቶልናል፤ ይህም ጥንት በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረው፣ ማዳኑም ከጠላቶቻችንና፣ ከተፃራሪዎቻችን ሁሉ እጅ ነው፤ ይህንም ያደረገው ለአባቶቻችን ምሕረቱን ለማሳየት፣ ቅዱስ ኪዳኑን ለማስታወስ፣ ለአባታችን ለአብርሃም የማለውን መሐላ ለማሰብ፣ ከጠላቶቻችን እጅ አውጥቶ፣ ያለ ፍርሀት እንድናገለግለው፣ በዘመናችንም ሁሉ በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ ሊያቆመን ነው። “ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ፤ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ የጌታን መንገድ ለማዘጋጀት በፊቱ ትሄዳለህና፤ የኀጢአታቸውን ስርየት ከማግኘታቸው የተነሣ፤ ለሕዝቡ የመዳንን ዕውቀት ትሰጥ ዘንድ፣ ከአምላካችንም ጥልቅ ምሕረት የተነሣ፣ የንጋት ፀሓይ ከሰማይ ወጣችልን፤ ይኸውም በጨለማ ለሚኖሩት፣ በሞት ጥላ ውስጥም ላሉት እንዲያበራና፣ እግሮቻችንንም ወደ ሰላም መንገድ እንዲመራ ነው።”

ሉቃስ 1:57-79 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

የኤልሳቤጥም የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ፥ ወንድ ልጅም ወለደች። ጎረቤቶችዋም ዘመዶችዋም ጌታ ምሕረቱን እንዳገነነላት ሰምተው ከእርስዋ ጋር ደስ አላቸው። በስምንተኛውም ቀን ሕፃኑን ሊገርዙት መጡ፥ በአባቱም ስም ዘካርያስ ሊሉት ወደዱ። እናቱ ግን መልሳ፦ አይሆንም፥ ዮሐንስ ይባል እንጂ አለች። እነርሱም፦ ከወገንሽ ማንም በዚህ ስም የተጠራ የለም አሉአት። አባቱንም ማን ሊባል እንዲወድ ጠቀሱት። ብራናም ለምኖ፦ ስሙ ዮሐንስ ነው ብሎ ጻፈ። ሁሉም አደነቁ። ያንጊዜም አፉ ተከፈተ መላሱም ተፈታ እግዚአብሔርንም እየባረከ ተናገረ። ለጎረቤቶቻቸውም ሁሉ ፍርሃት ሆነ፤ ይህም ሁሉ ነገር በይሁዳ በተራራማው አገር ሁሉ ተወራ፤ የሰሙትም ሁሉ፦ እንኪያ ይህ ሕፃን ምን ይሆን? እያሉ በልባቸው አኖሩት፤ የጌታ እጅ ከእርሱ ጋር ነበረችና። አባቱ ዘካርያስም መንፈስ ቅዱስ ሞላበትና ትንቢት ተናገረ እንዲህም አለ፦ የእስራኤል ጌታ አምላክ ይባረክ፥ ጐብኝቶ ለሕዝቡ ቤዛ አድርጎአልና፤ ከጥንት ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያት አፍ እንደ ተናገረ፥ በብላቴናው በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድን አስነስቶልናል፤ ማዳኑም ከወደረኞቻችንና ከሚጠሉን ሁሉ እጅ ነው፤ እንደዚህ ለአባቶቻችን ምሕረት አደረገ፤ ለአባታችን ለአብርሃምም የማለውን መሐላውን ቅዱሱን ኪዳን አሰበ፤ በእርሱም ከጠላቶቻችን እጅ ድነን በዘመናችን ሁሉ ያለ ፍርሃት በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግለው ሰጠን። ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ፥ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፥ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሄዳለህና፤ እንደዚህም የኃጢአታቸው ስርየት የሆነውን የመዳን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፤ ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው፤ ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል።

ሉቃስ 1:57-79 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኤልሳቤጥ የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰና ወንድ ልጅ ወለደች። ጐረቤቶችዋና ዘመዶችዋ ሁሉ ጌታ ታላቅ ምሕረቱን እንዳደረገላት ሰምተው ከእርስዋ ጋር ተደሰቱ። ሕፃኑ በተወለደ በስምንተኛው ቀን፥ በግዝረቱ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት ጐረቤቶችዋና ዘመዶችዋ ተሰብስበው መጡ፤ ባባቱ ስም ዘካርያስ ብለው ሊጠሩት ፈልገው ነበር፤ እናቱ ግን “እንዲህ አይሆንም፤ ስሙ ዮሐንስ ነው” አለች። እነርሱም “ከዘመዶችሽ በዚህ ስም የተጠራ ማንም የለም?” አሉአት። ከዚህም በኋላ አባቱን፦ “ልጅህ ማን ተብሎ እንዲጠራ ትፈልጋለህ?” ብለው በምልክት ጠየቁት። ዘካርያስም መጻፊያ እንዲሰጡት ጠይቆ፦ “ስሙ ዮሐንስ ነው” ብሎ ጻፈ፤ ሁሉም በዚህ ነገር ተደነቁ። በዚያኑ ጊዜ ዘካርያስ አንደበቱ ተፈቶለት መናገር ቻለ፤ እግዚአብሔርንም ማመስገን ጀመረ። ከዚህም የተነሣ በጐረቤቶቻቸው ሁሉ ፍርሀት አደረባቸው፤ ዜናውም በተራራማው በይሁዳ ምድር ሁሉ ተሰማ። ይህን ነገር የሰሙ ሁሉ፥ “ይህ ሕፃን ምን ሊሆን ይሆን?” እያሉ ይጠያየቁ ነበር። ይህም የሆነው የእግዚአብሔር ረድኤት በእርግጥ ከእርሱ ጋር ስለ ነበር ነው። የሕፃኑ አባት ዘካርያስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናገረ፦ “ሕዝቡን በምሕረት ስለ ጐበኘና ስላዳነ፥ የእስራኤል አምላክ፥ ጌታ ይመስገን! ከአገልጋዩ ከዳዊት ዘር ኀያል አዳኝ አስነሥቶልናል፤ ከጥንት ዘመን ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረ፤ ከጠላቶቻችንና ከባላጋራዎቻችን እጅ አድኖናል፤ ይህንንም ማድረጉ ለአባቶቻችን ምሕረትን እንደሚያደርግና የተናገረውንም ቅዱስ ቃል ኪዳኑን እንደሚፈጽም በማሰብ ነው። ይህንንም ቃል ኪዳን፥ በመሐላ የሰጠው ለአባታችን ለአብርሃም ነበር፤ የተስፋውም ቃል ከጠላቶቻችን እጅ ነጻ ወጥተን፥ ያለ ፍርሀት እንድናገለግለው ነው፤ እንዲሁም በሕይወታችን ዘመን ሁሉ፥ በእግዚአብሔር ፊት በቅድስናና በጽድቅ መኖር እንድንችል ነው። ደግሞም አንተ ሕፃን፥ የልዑል እግዚአብሔር ነቢይ ትባላለህ። መንገዱን ለማዘጋጀት ቀድመህ በጌታ ፊት ትሄዳለህ። ጌታም ኃጢአታቸውን ይቅር በማለት የመዳንን ዕውቀት ይሰጣቸዋል። አምላካችን መሓሪና ርኅሩኅ በመሆኑ የደኅንነት ብርሃን ከወደላይ እንዲበራልን ያደርጋል። እርሱ በጨለማና በሞት ጥላ ሥር ላሉት ሁሉ ያበራል፤ እርምጃችንንም ወደ ሰላም መንገድ ይመራል።”

ሉቃስ 1:57-79 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

የኤልሳቤጥም የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ፤ ወንድ ልጅም ወለደች። ጎረቤቶችዋም ዘመዶችዋም ጌታ ታላቅ ምሕረቱን እንዳደረገላት ሰምተው ከእርሷ ጋር ደስ አላቸው። በስምንተኛውም ቀን ሕፃኑን ሊገርዙት መጡ፤ በአባቱም ስም ዘካርያስ ብለው ሊጠሩት ፈልገው ነበር። እናቱ ግን መልሳ፦ “እንዲህ አይሆንም፤ ዮሐንስ ተብሎ ይጠራ እንጂ፤” አለች። እነርሱም፦ “ከዘመዶችሽ ማንም በዚህ ስም የተጠራ የለም፤” አሉአት። ማን ተብሎ ቢጠራ እንደሚወድ አባቱንም በምልክት ጠየቁ። ሰሌዳም ጠይቆ፦ “ስሙ ዮሐንስ ነው፤” ብሎ ጻፈ። ሁሉም ተደነቁ። ያንጊዜም አፉ ተከፈተ፤ ምላሱም ተፈታ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ተናገረ። በጎረቤቶቻቸውም ሁሉ ላይ ፍርሃት ሆነ፤ ይህም ሁሉ ነገር በተራራማው በይሁዳ አገር ሁሉ ተወራ፤ የሰሙትም ሁሉ፥ “እንግዲህ ይህ ሕፃን ምን ሊሆን ይሆን?” እያሉ በልባቸው አኖሩት፤ በእርግጥ የጌታ እጅ ከእርሱ ጋር ነበረችና። አባቱ ዘካርያስም መንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ትንቢት ተናገረ፤ እንዲህም አለ፦ “የእስራኤል ጌታ አምላክ ይባረክ፤ ጐብኝቶ ለሕዝቡ ቤዛ አድርጎአልና፤ በአገልጋዩ በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድን አስነስቶልናል፥ ከጥንት ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረ፤ ማዳኑም ከጠላቶቻችንና ከሚጠሉን ሁሉ እጅ ነው፤ እንዲሁም ለአባቶቻችን ምሕረትን አደረገ፤ ቅዱስ ኪዳኑንም ለአባታችን ለአብርሃም በመሐላ እንደማለለት አስታወሰ፤ በእርሱም ከጠላቶቻችን እጅ ድነን ያለ ፍርሃት በዘመናችን ሁሉ በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግለው ሰጠን። ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ! የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ መንገዱን ለማዘጋጀት በጌታ ፊት ትሄዳለህና፤ እንዲሁም በኀጢአታቸው ስርየት የመዳንን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፤ በአምላካችን የርኅራኄ ምሕረት ከላይ የሚመጣው ብርሃን ይጐበኘናልና፤ እርሱም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል፤ እግሮቻችንንም ወደ ሰላም መንገድ ይመራል።”