የሉቃስ ወንጌል 1:57-79

የሉቃስ ወንጌል 1:57-79 አማ05

ኤልሳቤጥ የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰና ወንድ ልጅ ወለደች። ጐረቤቶችዋና ዘመዶችዋ ሁሉ ጌታ ታላቅ ምሕረቱን እንዳደረገላት ሰምተው ከእርስዋ ጋር ተደሰቱ። ሕፃኑ በተወለደ በስምንተኛው ቀን፥ በግዝረቱ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት ጐረቤቶችዋና ዘመዶችዋ ተሰብስበው መጡ፤ ባባቱ ስም ዘካርያስ ብለው ሊጠሩት ፈልገው ነበር፤ እናቱ ግን “እንዲህ አይሆንም፤ ስሙ ዮሐንስ ነው” አለች። እነርሱም “ከዘመዶችሽ በዚህ ስም የተጠራ ማንም የለም?” አሉአት። ከዚህም በኋላ አባቱን፦ “ልጅህ ማን ተብሎ እንዲጠራ ትፈልጋለህ?” ብለው በምልክት ጠየቁት። ዘካርያስም መጻፊያ እንዲሰጡት ጠይቆ፦ “ስሙ ዮሐንስ ነው” ብሎ ጻፈ፤ ሁሉም በዚህ ነገር ተደነቁ። በዚያኑ ጊዜ ዘካርያስ አንደበቱ ተፈቶለት መናገር ቻለ፤ እግዚአብሔርንም ማመስገን ጀመረ። ከዚህም የተነሣ በጐረቤቶቻቸው ሁሉ ፍርሀት አደረባቸው፤ ዜናውም በተራራማው በይሁዳ ምድር ሁሉ ተሰማ። ይህን ነገር የሰሙ ሁሉ፥ “ይህ ሕፃን ምን ሊሆን ይሆን?” እያሉ ይጠያየቁ ነበር። ይህም የሆነው የእግዚአብሔር ረድኤት በእርግጥ ከእርሱ ጋር ስለ ነበር ነው። የሕፃኑ አባት ዘካርያስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናገረ፦ “ሕዝቡን በምሕረት ስለ ጐበኘና ስላዳነ፥ የእስራኤል አምላክ፥ ጌታ ይመስገን! ከአገልጋዩ ከዳዊት ዘር ኀያል አዳኝ አስነሥቶልናል፤ ከጥንት ዘመን ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረ፤ ከጠላቶቻችንና ከባላጋራዎቻችን እጅ አድኖናል፤ ይህንንም ማድረጉ ለአባቶቻችን ምሕረትን እንደሚያደርግና የተናገረውንም ቅዱስ ቃል ኪዳኑን እንደሚፈጽም በማሰብ ነው። ይህንንም ቃል ኪዳን፥ በመሐላ የሰጠው ለአባታችን ለአብርሃም ነበር፤ የተስፋውም ቃል ከጠላቶቻችን እጅ ነጻ ወጥተን፥ ያለ ፍርሀት እንድናገለግለው ነው፤ እንዲሁም በሕይወታችን ዘመን ሁሉ፥ በእግዚአብሔር ፊት በቅድስናና በጽድቅ መኖር እንድንችል ነው። ደግሞም አንተ ሕፃን፥ የልዑል እግዚአብሔር ነቢይ ትባላለህ። መንገዱን ለማዘጋጀት ቀድመህ በጌታ ፊት ትሄዳለህ። ጌታም ኃጢአታቸውን ይቅር በማለት የመዳንን ዕውቀት ይሰጣቸዋል። አምላካችን መሓሪና ርኅሩኅ በመሆኑ የደኅንነት ብርሃን ከወደላይ እንዲበራልን ያደርጋል። እርሱ በጨለማና በሞት ጥላ ሥር ላሉት ሁሉ ያበራል፤ እርምጃችንንም ወደ ሰላም መንገድ ይመራል።”