የኤልሳቤጥም የመውለጃዋ ቀን ደረሰ፤ ወንድ ልጅም ወለደች። ጎረቤቶቿና ዘመዶቿም ጌታ ታላቅ ምሕረት እንዳደረገላት ሰሙ፤ የደስታዋም ተካፋዮች ሆኑ። በስምንተኛውም ቀን ሕፃኑን ሊገርዙት መጡ፤ በአባቱም ስም ዘካርያስ ሊሉት ፈለጉ፤ እናቱ ግን፣ “አይሆንም፤ ዮሐንስ መባል አለበት” አለች። እነርሱም፣ “ከዘመዶችሽ በዚህ ስም የተጠራ ማንም የለም” አሏት። አባቱንም ምን ስም ሊያወጣለት እንደሚፈልግ በምልክት ጠየቁት። እርሱም መጻፊያ ሰሌዳ እንዲሰጡት ለምኖ፣ “ስሙ ዮሐንስ ነው” ብሎ ጻፈ፤ ሁሉም በነገሩ ተደነቁ። ወዲያውም አፉ ተከፈተ፤ አንደበቱ ተፈታ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ መናገር ጀመረ። ጎረቤቶቹም ሁሉ በፍርሀት ተሞሉ፤ ይህም ሁሉ ነገር በደጋማው የይሁዳ ምድር ሁሉ ተወራ። ይህንም የሰሙ ሁሉ፣ “ይህ ሕፃን ምን ሊሆን ይሆን?” እያሉ ነገሩን በልባቸው ያዙ፤ የጌታ እጅ በርግጥ ከርሱ ጋራ ነበርና። የሕፃኑም አባት ዘካርያስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናገረ፤ “የእስራኤል አምላክ፣ ጌታ ይመስገን፤ መጥቶ ሕዝቡን ተቤዥቷልና። በብላቴናው በዳዊት ቤት፣ የድነት ቀንድ አስነሥቶልናል፤ ይህም ጥንት በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረው፣ ማዳኑም ከጠላቶቻችንና፣ ከተፃራሪዎቻችን ሁሉ እጅ ነው፤ ይህንም ያደረገው ለአባቶቻችን ምሕረቱን ለማሳየት፣ ቅዱስ ኪዳኑን ለማስታወስ፣ ለአባታችን ለአብርሃም የማለውን መሐላ ለማሰብ፣ ከጠላቶቻችን እጅ አውጥቶ፣ ያለ ፍርሀት እንድናገለግለው፣ በዘመናችንም ሁሉ በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ ሊያቆመን ነው። “ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ፤ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ የጌታን መንገድ ለማዘጋጀት በፊቱ ትሄዳለህና፤ የኀጢአታቸውን ስርየት ከማግኘታቸው የተነሣ፤ ለሕዝቡ የመዳንን ዕውቀት ትሰጥ ዘንድ፣ ከአምላካችንም ጥልቅ ምሕረት የተነሣ፣ የንጋት ፀሓይ ከሰማይ ወጣችልን፤ ይኸውም በጨለማ ለሚኖሩት፣ በሞት ጥላ ውስጥም ላሉት እንዲያበራና፣ እግሮቻችንንም ወደ ሰላም መንገድ እንዲመራ ነው።”
ሉቃስ 1 ያንብቡ
ያዳምጡ ሉቃስ 1
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሉቃስ 1:57-79
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች