የኤልሣቤጥም የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ፤ ወንድ ልጅም ወለደች። ዘመዶችዋና ጎረቤቶችዋም እግዚአብሔር ቸርነቱን እንዳበዛላት በሰሙ ጊዜ ከእርስዋ ጋር ደስ አላቸው። ከዚህም በኋላ በስምንተኛው ቀን ሕፃኑን ሊገዝሩት መጡ፤ በአባቱም ስም ዘካርያስ ብለው ጠሩት። እናቱ ግን መልሳ፥ “አይሆንም፥ ዮሐንስ ይባል እንጂ” አለች። እነርሱም፥ “ከዘመዶችሽ ስሙ እንደዚህ የሚባል የለም” አሉአት። አባቱንም ጠቅሰው፥ “ማን ሊሉት ትወዳለህ?” አሉት። ብራናም ለመነና “ስሙ ዮሐንስ ይባል” ብሎ ጻፈ፤ ሁሉም አደነቁ። ያንጊዜም አፉ ተከፈተ፤ አንደበቱም ተናገረ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነ። በዚያም ሀገር ሰው ሁሉ ላይ ፍርሀት ሆነ፤ ይህም ነገር ሁሉ በይሁዳ በተራራማው ሀገር ሁሉ ተወራ። የሰሙትም ሁሉ፥ “እንግዲህ ይህ ሕፃን ምን ይሆን?” እያሉ በልባቸው አኖሩት፤ የእግዚአብሔር እጅ በእርሱ ላይ ነበረችና። በአባቱ በዘካርያስም መንፈስ ቅዱስ መላበት፤ እንዲህም ብሎ ትንቢት ተናገረ፦ “ይቅር ያለን፥ ለወገኖቹም ድኅነትን ያደረገ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ ከባርያው ከዳዊት ቤት የምንድንበትን ቀንድ አስነሣልን፤ ከጥንት ጀምሮ በነበሩ በቅዱሳን በነቢያት አፍ እንደ ተናገረ። ከጠላቶቻችን እጅ፥ ከሚጠሉንም ሁሉ እጅ ያድነን ዘንድ። ቸርነቱን ከአባቶቻችን ጋር ያደርግ ዘንድ፥ ቅዱስ ኪዳኑንም ያስብ ዘንድ። ለአባታችን ለአብርሃም የማለውን መሐላ ያስብ ዘንድ። ከጠላቶቻችን እጅ ድነን ያለ ፍርሀት፥ በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ በዘመናችን ሁሉ እንድናመልከው ይሰጠን ዘንድ። አንተም ሕፃን፥ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ መንገዱን ትጠርግ ዘንድ በፊቱ ትሄዳለህና። ኀጢአታቸው ይሰረይላቸው ዘንድ መድኀኒታቸውን እንዲያውቁ ለአሕዛብ ትሰጣቸው ዘንድ። ከአርያም በጐበኘን በአምላካችን በይቅርታውና በቸርነቱ። በጨለማና በሞት ጥላ ለነበሩት ብርሃኑን ያሳያቸው ዘንድ፥ እግሮቻችንንም ወደ ሰላም ጎዳና ያቀና ዘንድ ወጣ።”
የሉቃስ ወንጌል 1 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 1
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 1:57-79
8 ቀናት
ኢየሱስ ስለራሱ ማን ብሎ ይላል?
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች