ዘሌዋውያን 27:1-15
ዘሌዋውያን 27:1-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ማናቸውም ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ለእግዚአብሔር ስእለት ቢሳል አንተ እንደምትገምተው መጠን ስለ ሰውነቱ ዋጋውን ይስጥ። ለወንድ ከሃያ ዓመት ጀምሮ እስከ ስድሳ ዓመት ድረስ እንደ መቅደሱ ሚዛን ግምቱ አምሳ የብር ዲድርክም ይሁን። ሴትም ብትሆን ግምቷ ሠላሳ የብር ዲድርክም ይሁን። ከአምስት ዓመትም ጀምሮ እስከ ሃያ ዓመት ድረስ ግምቱ ለወንድ ሃያ የብር ዲድርክም፥ ለሴትም ዐሥር የብር ዲድርክም ይሁን። ከአንድ ወርም እስከ አምስት ዓመት ድረስ ለወንድ ግምቱ አምስት የብር ዲድርክም፥ ለሴትም ግምቷ ሦስት የብር ዲድርክም ይሁን። ከስድሳ ዓመትም ጀምሮ ከዚያም በላይ ወንድ ቢሆን ግምቱ ዐሥራ አምስት ዲድርክም፥ ለሴትም ዐሥር ዲድርክም ይሁን። ለግምቱ የሚከፍለውን ቢያጣ ግን በካህኑ ፊት ይቁም፤ ካህኑም የተሳለውን ሰው ከእጁ ባለው ገንዘብ መጠን ይገምትለት፤ ካህኑም የተሳለው ሰው እንደሚችል መጠን ይገምትለት። “ለእግዚአብሔርም መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርበው እንስሳ ቢሆን፥ ሰው ከእነዚህ ለእግዚአብሔር የሚሰጠው ሁሉ ቅዱስ ይሆናል። መልካሙን በክፉ፥ ክፉውንም በመልካም አይለውጥ፤ እንስሳንም በእንስሳ ቢለውጥ እርሱና ልዋጩ የተቀደሱ ይሆናሉ። እንስሳው ለእግዚአብሔር መሥዋዕት መሆን የማይገባው ርኩስ ቢሆን፥ እንስሳውን በካህኑ ፊት ያቁመው። መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን ካህኑ ይገምተው፤ ካህኑም እንደሚገምተው መጠን እንዲሁ ይሁን። ይቤዠው ዘንድ ቢወድድ ግን ከግምቱ በላይ አምስተኛ እጅ ይጨምር። “ሰውም ለእግዚአብሔር ቅዱስ ይሆን ዘንድ ቤቱን ቢቀድስ፥ ካህኑ መልካም ወይም ክፉ እንደ ሆነ ይገምተዋል፤ ካህኑም እንደሚገምተው መጠን እንዲሁ ይቆማል። የተሳለውም ሰው ቤቱን ይቤዠው ዘንድ ቢወድድ ከግምቱ ገንዘብ በላይ አምስተኛ እጅ ይጨምር፤ ቤቱም ለእርሱ ይሆናል።
ዘሌዋውያን 27:1-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ማንኛውም ሰው ተመጣጣኙን ዋጋ በመክፈል ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰውን ለመስጠት የተለየ ስእለት ቢሳል፣ ዕድሜው ከሃያ እስከ ስድሳ ዓመት ለሆነ ወንድ፣ በቤተ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መሠረት፣ ግምቱ አምሳ ጥሬ ሰቅል ብር ይሁን። ለሴት ከሆነ ግምቱ ሠላሳ ሰቅል ይሁን። ዕድሜው ከአምስት እስከ ሃያ ዓመት ለሆነ ሰው፣ ወንድ ከሆነ ግምቱ ሃያ ሰቅል፣ ሴት ከሆነች ግምቷ ዐሥር ሰቅል ይሁን። ዕድሜው ከአንድ ወር እስከ አምስት ዓመት ለሆነ ሰው፣ ወንድ ከሆነ ግምቱ አምስት ሰቅል ጥሬ ብር፣ ለሴት ከሆነ ሦስት ሰቅል ጥሬ ብር ይሁን። ስድሳ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ለሆነ ሰው፣ ወንድ ከሆነ ግምቱ ዐሥራ አምስት ሰቅል፣ ሴት ከሆነች ዐሥር ሰቅል ይሁን። ስእለት የተሳለው ድኻ ከሆነና ግምቱን መክፈል ካልቻለ ግን፣ ለስጦታ ያሰበውን ሰው ወደ ካህኑ ያምጣ፤ ካህኑም የተሳለው ሰው ባለው ዐቅም መሠረት መክፈል የሚገባውን ይተምንለታል። “ ‘ሰውየው የተሳለው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት ሆኖ መቅረብ የሚችል እንስሳ ከሆነ፣ እንዲህ ያለው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሰጠ እንስሳ የተቀደሰ ይሆናል። ሰውየው መልካም የሆነውን እንስሳ መልካም ባልሆነው፣ መልካም ያልሆነውንም መልካም በሆነው አይለውጥ ወይም አይተካ፤ አንዱን እንስሳ በሌላው ከተካም ሁለቱ የተቀደሱ ይሆናሉ። እንስሳው በሥርዐቱ መሠረት የረከሰ፣ ለእግዚአብሔርም (ያህዌ) መሥዋዕት ሆኖ መቅረብ የማይገባው ከሆነ፣ ሰውየው እንስሳውን ወደ ካህኑ ያቅርብ፤ መልካም ቢሆን ወይም ባይሆን፣ ካህኑ ዋጋውን ይወስን፤ የካህኑም ውሳኔ የጸና ይሆናል። ባለቤቱ እንስሳውን መዋጀት ከፈለገ ግን፣ በተተመነው ዋጋ ላይ አንድ አምስተኛ መጨመር አለበት። “ ‘አንድ ሰው ቤቱን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ይሆን ዘንድ ቢቀድስ፣ መልካም ቢሆን ወይም ባይሆን ካህኑ ዋጋውን ይተምን፤ ካህኑም የተመነው ዋጋ የጸና ይሆናል። ቤቱን የቀደሰው ሰው መልሶ ሊዋጀው ከፈለገ ግን፣ የዋጋውን አንድ አምስተኛ በዋጋው ላይ መጨመር አለበት፤ ቤቱም ዳግመኛ የራሱ ይሆናል።
ዘሌዋውያን 27:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ማናቸውም ሰው ሰውን ለእግዚአብሔር ሊሰጥ ቢሳል አንተ እንደምትገምተው መጠን ስለ ሰው ዋጋውን ይስጥ። ለወንድ ከሃያ ዓመት ጀምሮ እስከ ስድሳ ዓመት ድረስ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ግምቱ አምሳ የብር ሰቅል ይሁን። ሴትም ብትሆን ግምትዋ ሠላሳ ሰቅል ይሁን። ከአምስት ዓመትም ጀምሮ እስከ ሀያ ዓመት ድረስ ግምቱ ለወንድ ሀያ ሰቅል፥ ለሴትም አሥር ሰቅል ይሁን። ከአንድ ወርም እስከ አምስት ዓመት ድረስ ለወንድ ግምቱ አምስት የብር ሰቅል፥ ለሴትም ግምትዋ ሦስት የብር ሰቅል ይሁን። ከስድሳ ዓመትም ጀምሮ ከዚያም በላይ ወንድ ቢሆን ግምቱ አሥራ አምስት ሰቅል፥ ለሴትም አሥር ሰቅል ይሁን። ለግምቱም የሚከፍለውን ቢያጣ ግን በካህኑ ፊት ይቁም፥ ካህኑም የተሳለውን ሰው ይገምተው፤ ካህኑም የተሳለው ሰው እንደሚችል መጠን ይገምተው። ለእግዚአብሔርም መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርበው እንስሳ ቢሆን፥ ሰው ከእነዚህ ለእግዚአብሔር የሚሰጠው ሁሉ ቅዱስ ይሆናል። መልካሙን በክፉ፥ ክፉውንም በመልካም አይለውጥ፤ እንስሳንም በእንስሳ ቢለውጥ እርሱና ልዋጩ የተቀደሱ ይሆናሉ። እንስሳው ለእግዚአብሔር መሥዋዕት መሆን የማይገባው ርኩስ ቢሆን፥ እንስሳውን በካህኑ ፊት ያኑረው። መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን ካህኑ ይገምተው፤ ካህኑም እንደሚገምተው መጠን እንዲሁ ይሁን። ይቤዠውም ዘንድ ቢወድድ ከግምቱ በላይ አምስተኛ ይጨምር። ሰውም ለእግዚአብሔር ቅዱስ ይሆን ዘንድ ቤቱን ቢቀድስ፥ ካህኑ መልካም ወይም ክፉ እንደ ሆነ ይገምተዋል፤ ካህኑም እንደሚገምተው መጠን እንዲሁ ይቆማል። የቀደሰውም ሰው ቤቱን ይቤዠው ዘንድ ቢወድድ ከግምቱ ገንዘብ በላይ አምስተኛ ይጨምር፤ ቤቱም ለእርሱ ይሆናል።
ዘሌዋውያን 27:1-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ አንድ ሰው ለእግዚአብሔር ስእለት ተስሎ ሲፈጸምለት፥ ያ የተሳለው ስለት ሰውን ለመስጠት ከሆነ የመዋጀት ዋጋው እንደ ገመትከው ሆኖ እንደሚከተለው ይሁን፦ በቤተ መቅደሱስ በታወቀው ሚዛን ልክ ዕድሜው ከኻያ እስከ ሥልሳ ለሆነ ወንድ 600 ግራም የሚመዝን ጥሬ ብር ይሁን፤ በዚሁ ዕድሜ ክልል ለምትገኝ ሴት ሠላሳ ጥሬ ብር ይሁን፤ ከአምስት እስከ ኻያ ዓመት ለሆነው ወንድ ኻያ ጥሬ ብር ይሁን፤ በዚሁ ዕድሜ ክልል ላለች ሴት ዐሥር ጥሬ ብር ይሁን፤ ዕድሜው ከአንድ ወር እስከ አምስት ዓመት ለሆነ ወንድ አምስት ጥሬ ብር፥ በዚሁ ዕድሜ ክልል ውስጥ ለምትገኝ ሴት ሦስት ጥሬ ብር ይሁን፤ ዕድሜው ከስድሳ ዓመት በላይ ለሆነው ወንድ ዐሥራ አምስት ጥሬ ብር፤ ዕድሜዋ ከስድሳ ዓመት በላይ ለሆናት ሴት ዐሥር ጥሬ ብር ይሁን። “ስእለት ያደረገው ሰው ይህን ተመን ለመክፈል የማይችል ሆኖ ከተገኘ ያ ለስጦታ የቀረበውን ሰው ወደ ካህኑ ያምጣው፤ ካህኑም ያ ሰው የሚችለውን ያኽል ገምቶ ዝቅተኛ ዋጋ ያስከፍለው። “ስእለቱ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርበው እንስሳ ከሆነ አይዋጅም፤ ለእግዚአብሔር የቀረበው መባ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናል። ሰውየውም ለዚያ እንስሳ ሌላ ምትክ ማቅረብ አይገባውም፤ ምትክ አቅርቦ በተገኘ ጊዜ ግን ሁለቱም እንስሶች ለእግዚአብሔር የተለዩ ይሁኑ። ስጦታው ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ሆኖ ለመቅረብ ተቀባይነት የሌለው ንጹሕ ያልሆነ እንስሳ ከሆነ ግን ሰውየው እንስሳውን ወደ ካህኑ ያምጣ፤ ካህኑም የእንስሳውን መልካምነት ወይም መጥፎነት ገምቶ ዋጋውን ይወስን፤ ያም ዋጋ የመጨረሻ ይሆናል፤ ባለቤቱም እንስሳውን መልሶ ለመግዛት ቢፈልግ በዋጋው ላይ በመቶ ኻያ እጅ ይጨምር። “አንድ ሰው ቤቱን ለእግዚአብሔር የተለየ ስጦታ አድርጎ ሲያቀርብ ካህኑ የቤቱን መልካምነትና መጥፎነት ገምቶ ዋጋውን ይወስን፤ ያም ዋጋ የመጨረሻ ይሆናል። ባለንብረቱ ያንን ቤት መልሶ ለመግዛት ቢፈልግ ግን በዋጋው ላይ በመቶ ሃያ እጅ ይጨምር።
ዘሌዋውያን 27:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታ ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ ማናቸውም ሰው ሰውን ለጌታ ሊሰጥ ቢሳል፥ አንተ እንደምትገምተው መጠን ስለ ሰው ተመጣጣኝ የሆነውን ዋጋ ይስጥ። ለወንድ ከሃያ ዓመት ጀምሮ እስከ ስልሳ ዓመት ድረስ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ግምትህ ኀምሳ የብር ሰቅል ይሁን። ሴትም ብትሆን ግምትህ ሠላሳ ሰቅል ይሁን። ከአምስት ዓመትም ጀምሮ እስከ ሀያ ዓመት ድረስ ግምትህ ለወንድ ሀያ ሰቅል፥ ለሴትም ዐሥር ሰቅል ይሁን። ከአንድ ወርም እስከ አምስት ዓመት ድረስ ለወንድ ግምትህ አምስት የብር ሰቅል፥ ለሴትም ግምትህ ሦስት የብር ሰቅል ይሁን። ዕድሜውም ስልሳ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆነው ሰው ቢሆን ለወንድ ግምትህ ዐሥራ አምስት ሰቅል፥ ለሴትም ዐሥር ሰቅል ይሁን። ማናቸውም ሰው ለግምትህ ከድህነቱ የተነሣ የሚከፍለውን ቢያጣ እርሱም በካህኑ ፊት የስለቱን ሰው የምጣው፥ ካህኑም እርሱን ይገምተው፤ ካህኑም የተሳለው ሰው አቅሙ እንደሚፈቅደው መጠን ይገምትለት። “ለጌታም መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርበው እንስሳ ቢሆን፥ ሰው ከእነዚህ ለጌታ የሚሰጠው ሁሉ ቅዱስ ይሆናል። መልካሙን በክፉ ወይም ክፉውን በመልካም ቢሆንም እንኳ እርሱን በሌላ አትተካ ወይንም አትለውጥ፤ እንስሳንም በእንስሳ ቢለውጥ እርሱና ልዋጩ ሁለቱም የተቀደሱ ይሆናሉ። እንስሳው ለጌታ መሥዋዕት መሆን የማይገባው ርኩስ ቢሆን፥ እንስሳውን በካህኑ ፊት ያምጣው። ካህኑም መልካም ወይም መጥፎ እንደሆነ ይገምተዋል፤ ካህኑም እንደሚገምተው መጠን እንዲሁ ይሁን። እርሱም ሊቤዠው ቢወድድ ግን በተገመተው ላይ አምስት እጅ ይጨምር። “ለጌታም ቅዱስ ይሆን ዘንድ ሰው ቤቱን ቢቀድስ፥ ካህኑ መልካም ወይም መጥፎ እንደሆነ ይገምተዋል፤ ካህኑም እንደሚገምተው መጠን እንዲሁ ይጸናል። የቀደሰውም ሰው ቤቱን ሊቤዠው ቢወድድ በገመትከው የገንዘብ መጠን ላይ አምስት እጅ ይጨምራል፤ ቤቱም ለእርሱ ይሆናል።