ኦሪት ዘሌዋውያን 27
27
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ማናቸውም ሰው ሰውን ለእግዚአብሔር ሊሰጥ ቢሳል አንተ እንደምትገምተው መጠን ስለ ሰው ዋጋውን ይስጥ። 3ለወንድ ከሃያ ዓመት ጀምሮ እስከ ስድሳ ዓመት ድረስ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ግምቱ አምሳ የብር ሰቅል ይሁን። 4ሴትም ብትሆን ግምትዋ ሠላሳ ሰቅል ይሁን። 5ከአምስት ዓመትም ጀምሮ እስከ ሀያ ዓመት ድረስ ግምቱ ለወንድ ሀያ ሰቅል፥ ለሴትም አሥር ሰቅል ይሁን። 6ከአንድ ወርም እስከ አምስት ዓመት ድረስ ለወንድ ግምቱ አምስት የብር ሰቅል፥ ለሴትም ግምትዋ ሦስት የብር ሰቅል ይሁን። 7ከስድሳ ዓመትም ጀምሮ ከዚያም በላይ ወንድ ቢሆን ግምቱ አሥራ አምስት ሰቅል፥ ለሴትም አሥር ሰቅል ይሁን። 8ለግምቱም የሚከፍለውን ቢያጣ ግን በካህኑ ፊት ይቁም፥ ካህኑም የተሳለውን ሰው ይገምተው፤ ካህኑም የተሳለው ሰው እንደሚችል መጠን ይገምተው። 9ለእግዚአብሔርም መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርበው እንስሳ ቢሆን፥ ሰው ከእነዚህ ለእግዚአብሔር የሚሰጠው ሁሉ ቅዱስ ይሆናል። 10መልካሙን በክፉ፥ ክፉውንም በመልካም አይለውጥ፤ እንስሳንም በእንስሳ ቢለውጥ እርሱና ልዋጩ የተቀደሱ ይሆናሉ። 11እንስሳው ለእግዚአብሔር መሥዋዕት መሆን የማይገባው ርኩስ ቢሆን፥ እንስሳውን በካህኑ ፊት ያኑረው። 12መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን ካህኑ ይገምተው፤ ካህኑም እንደሚገምተው መጠን እንዲሁ ይሁን። 13ይቤዠውም ዘንድ ቢወድድ ከግምቱ በላይ አምስተኛ ይጨምር። 14ሰውም ለእግዚአብሔር ቅዱስ ይሆን ዘንድ ቤቱን ቢቀድስ፥ ካህኑ መልካም ወይም ክፉ እንደ ሆነ ይገምተዋል፤ ካህኑም እንደሚገምተው መጠን እንዲሁ ይቆማል። 15የቀደሰውም ሰው ቤቱን ይቤዠው ዘንድ ቢወድድ ከግምቱ ገንዘብ በላይ አምስተኛ ይጨምር፤ ቤቱም ለእርሱ ይሆናል። 16ሰውም ከርስቱ እርሻ ለእግዚአብሔር ቢቀድስ፥ እንደ መዘራቱ መጠን ይገመት፤ አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ የሚዘራበት እርሻ አምሳ የብር ሰቅል ይገመታል። 17እርሻውንም ከኢዮቤልዩ ዓመት ጀምሮ ቢቀድስ፥ እንደ ግምቱ መጠን ይቆማል። 18እርሻውንም ከኢዮቤልዩ ዓመት በኋላ ቢቀድስ፥ ካህኑ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ እንደ ቀሩት ዓመታት ገንዘቡን ይቈጥርለታል፤ ከግምቱም ይጐድላል። 19እርሻውንም የቀደሰ ሰው ይቤዠው ዘንድ ቢወድድ፥ ከግምቱ ገንዘብ በላይ አምስተኛ ይጨምር፤ ለእርሱም ይሆናል። 20እርሻውንም ባይቤዠው፥ ወይም ለሌላ ሰው ቢሸጥ፥ እንደገና ይቤዠው ዘንድ አይቻለውም። 21እርሻው ግን በኢዮቤልዩ ሲወጣ እንደ እርም ለእግዚአብሔር የተቀደሰ እርሻ ይሆናል፤ ርስቱ ለካህኑ ይሆናል። 22ከርስቱ እርሻ ያልሆነውን የገዛውን እርሻ ለእግዚአብሔር ቢቀድስ፥ 23ካህኑ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ የግምቱን ዋጋ ይቈጥርለታል፤ በዚያም ቀን ግምቱን እንደ ተቀደሰ ነገር ለእግዚአብሔር ይሰጣል። 24በኢዮቤልዩ ዓመት እርሻው የምድሪቱ ባለ ርስት ወደ ነበረው ወደ ሸጠው ሰው ይመለሳል። 25ግምቱም ሁሉ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ይሆናል፤ ሰቅሉ ሀያ አቦሊ ይሆናል። 26ለእግዚአብሔር ግን የሚቀርበውን የእንስሳ በኵራት ማንም ይቀድሰው ዘንድ አይቻለውም፤ በሬ ቢሆን ወይም በግ ለእግዚአብሔር ነው። 27የረከሰም እንስሳ ቢሆን እንደ ግምቱ ይቤዠው፥ በእርሱም የዋጋውን አምስተኛ ይጨምርበታል፤ ባይቤዥም እንደ ግምቱ ይሸጣል። 28ለእግዚአብሔርም የተለየ እርም የሆነ ነገር ሁሉ፥ ሰው ቢሆን ወይም እንስሳ ወይም የርስቱ እርሻ ቢሆን፥ አይሸጥም፥ አይቤዥም፤ እርም የሆነ ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። 29ከሰዎችም እርም የሆነ ሁሉ አይቤዥም፤ ፈጽሞ ይገደላል። 30የምድርም አሥራት፥ ወይም የምድር ዘር ወይም የዛፍ ፍሬ ቢሆን፥ የእግዚአብሔር ነው፤ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነው። 31ሰውም አሥራቱን ሊቤዥ ቢወድድ፥ አምስተኛ ይጨምርበታል። 32ከበሬም ሁሉ ከአሥር አንድ፥ ከእረኛውም በትር በታች ከሚያልፍ በግና ፍየል ሁሉ ከአሥር አንድ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል። 33መልካም ወይም ክፉ እንዲሆን አይመርምር፥ አይለውጥም፤ ቢለውጠውም እርሱና ልዋጩ የተቀደሱ ይሆናሉ፤ አይቤዠውም። 34እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ለእስራኤል ልጆች ሙሴን ያዘዘው ትእዛዛት እነዚህ ናቸው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 27: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ