ኦሪት ዘሌዋውያን 26
26
1እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ለእናንተ ጣዖት አታድርጉ፥ የተቀረጸም ምስል ወይም ሐውልት አታቁሙ፤ ትሰግዱለትም ዘንድ በምድራችሁ ላይ የተቀረጸ ድንጋይ አታኑሩ። 2ሰንበታቴን ጠብቁ፥ መቅደሴንም ፍሩ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 3በሥርዓቴ ብትሄዱ፥ ትእዛዛቴንም ብትጠብቁ ብታደርጉትም፥ 4ዝናባችሁን በወቅቱ አዘንባለሁ፥ ምድሪቱም እህልዋን ትሰጣለች፥ የሜዳው ዛፎችም ፍሬአቸውን ይሰጣሉ። 5የእህሉም ማበራየት በእናንተ ዘንድ እስከ ወይኑ መቍረጥ ይደርሳል፥ የወይኑም መቍረጥ እስከ እህሉ መዝራት ይደርሳል፤ እስክትጠግቡም ድረስ እንጀራችሁን ትበላላችሁ፥ በምድራችሁም ላይ በጸጥታ ትኖራላችሁ። 6በምድራችሁም ላይ ሰላምን እሰጣለሁ፥ ማንም ሳያስፈራችሁ ትተኛላችሁ፤ ክፉዎችንም አራዊት ከምድራችሁ አጠፋለሁ፥ ሰይፍም በምድራችሁ ላይ አያልፍም። 7ጠላቶቻችሁንም ታሳድዳላችሁ፥ በፊታችሁም በሰይፍ ይወድቃሉ። 8ከእናንተም አምስቱ መቶውን ያሳድዳሉ፥ መቶውም አሥሩን ሺህ ያሳድዳሉ፤ ጠላቶቻችሁም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ። 9ፊቴም ወደ እናንተ ይሆናል፥ እንድታፈሩም አደርጋችኋለሁ፥ አበዛችሁማለሁ፤ ቃል ኪዳኔንም ከእናንተ ጋር አጸናለሁ። 10ብዙ ጊዜ የተቀመጠውንም አሮጌውን እህል ትበላላችሁ፤ ከአዲሱም በፊት አሮጌውን ታወጣላችሁ። 11ማደሪያዬንም በእናንተ መካከል አደርጋለሁ፤ ነፍሴም አትጸየፋችሁም። 12በመካከላችሁም እሄዳለሁ፥ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፥ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ። 13ባሪያዎች እዳትሆኑአቸው ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ የባርነታችሁን ቀንበር ሰብሬአለሁ፤ ቀና ብላችሁ እንድትሄዱ አድርጌአችኋለሁ። 14ነገር ግን ባትሰሙኝ፥ እነዚህንም ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፥ 15ሥርዓቴንም ብትንቁ፥ ትእዛዛቴንም ሁሉ እንዳታደርጉ፥ ቃል ኪዳኔንም እንድታፈርሱ ነፍሳችሁ ፍርዴን ብትጸየፍ፥ 16እኔም እንዲህ አደርግባችኋለሁ፤ ፍርሃትን፥ ክሳትንም፥ ዓይናችሁንም የሚያፈዝዝ፥ ሰውነታችሁንም የሚያማስን ትኩሳት አወርድባችኋለሁ፤ ዘራችሁንም በከንቱ ትዘራላችሁ፥ ጠላቶቻችሁ ይበሉታልና። 17ፊቴንም አከብድባችኋለሁ፥ በጠላቶቻችሁም ፊት ትወድቃላችሁ፤ የሚጠሉአችሁም ይገዙአችኋል፤ ማንም ሳያሳድዳችሁ ትሸሻላችሁ። 18እስከዚህም ድረስ ባትሰሙኝ፥ ስለ ኃጢአታችሁ በቅጣታችሁ ላይ ሰባት እጥፍ እጨምራለሁ። 19የኃይላችሁንም ትዕቢት እሰብራለሁ፤ ሰማያችሁንም እንደ ብረት፥ ምድራችሁንም እንደ ናስ አደርጋለሁ። 20ጕልበታችሁም በከንቱ ያልቃል፤ ምድራችሁም እህልዋን አትሰጥም፥ የምድርም ዛፎች ፍሬአቸውን አይሰጡም። 21በእንቢተኝነትም ብትሄዱብኝ ባትሰሙኝም፥ እንደ ኃጢአታችሁ መጠን በመቅሠፍት ላይ ሰባት እጥፍ እጨምራለሁ። 22በመካከላችሁም የምድርን አራዊት እሰድዳለሁ፤ ልጆቻችሁንም ይነጥቃሉ፥ እንሰሶቻችሁንም ያጠፋሉ፥ እናንተንም ያሳንሳሉ፤ መንገዶቻችሁም በረሃ ይሆናሉ። 23እስከዚህም ድረስ ባትቀጡ፥ በእንቢተኝነትም ብትሄዱ፥ 24እኔ ደግሞ በእንቢተኝነት እሄድባችኋለሁ፤ ስለ ኃጢአታችሁም ሰባት እጥፍ እመታችኋለሁ። 25የቃል ኪዳኔንም በቀል ይበቀልባችሁ ዘንድ ሰይፍ አመጣባችኋለሁ፤ ወደ ከተማችሁም ትሰበሰባላችሁ፥ ቸነፈርንም እሰድድባችኋለሁ፤ በጠላትም እጅ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ። 26የእህላችሁንም ድጋፍ በሰበርሁ ጊዜ፥ አሥር ሴቶች እንጀራቸውን በአንድ ምጣድ ይጋግራሉ፥ በሚዛንም መዝነው እንጀራችሁን ይመልሱላችኋል፤ በበላችሁም ጊዜ አትጠግቡም። 27እስከዚህም ድረስ ባትሰሙኝ፥ በእንቢተኝነትም ብትሄዱብኝ፥ 28እኔ ደግሞ በቍጣ እሄድባችኋለሁ፤ ስለ ኃጢአታችሁም ሰባት እጥፍ እቀጣችኋለሁ። 29የወንዶች ልጆቻችሁንም ሥጋ ትበላላችሁ፤ የሴቶች ልጆቻችሁንም ሥጋ ትበላላችሁ። 30የኮረብታ መስገጃዎቻችሁንም አፈርሳለሁ፥ የፀሐይ ምስሎቻችሁንም አጠፋለሁ፥ ሬሳችሁንም በጣዖቶቻችሁ ሬሳዎች ላይ እጥላለሁ፤ ነፍሴም ትጸየፋችኋለች። 31ከተሞቻችሁንም ባድማ አደርጋለሁ፥ መቅደሶቻችሁንም አፈርሳለሁ፥ መልካሙንም መዓዛችሁን አላሸትትም። 32ምድሪቱንም የተፈታች አደርጋለሁ፤ የሚቀመጡባት ጠላቶቻችሁም በእርስዋ የተነሣ ይደነቃሉ። 33እናንተም ከአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፥ ሰይፍንም አስመዝዝባችኋለሁ፤ ምድራችሁም የተፈታች ትሆናለች፥ ከተሞቻችሁም ባድማ ይሆናሉ። 34በዚያም በተፈታችበት ዘመን ሁሉ እናንተም በጠላቶቻችሁ ምድር ሳላችሁ፥ ምድሪቱ ሰንበት በማድረግዋ ትደሰታለች፤ በዚያም ጊዜ ምድሪቱ ታርፋለች፥ ሰንበትንም በማድረግዋ ትደሰታለች። 35እናንተ ተቀምጣችሁባት በነበረ ጊዜ በሰንበቶቻችሁ አላረፈችም ነበርና በተፈታችበት ዘመን ሁሉ ታርፋለች። 36በጠላቶቻቸውም ምድሮች ሳሉ ከእናንተ ተለይተው በቀሩት ላይ በልባቸው ድንጋጤን እሰድድባቸዋለሁ፤ በነፋስም የምትንቀሳቀስ የቅጠል ድምፅ ታሸብራቸዋለች፤ ከሰይፍ እንደሚሸሹ ይሸሻሉ፤ ማንም ሳያሳድዳቸው ይወድቃሉ። 37ማንም ሳያሳድዳቸው ከሰይፍ እንዲሸሹ እርስ በርሳቸው ይሰነካከላሉ፤ እናንተም በጠላቶቻችሁ ፊት መቆም አትችሉም። 38በአሕዛብም መካከል ታልቃላችሁ፥ የጠላቶቻችሁም ምድር ትውጣችኋለች። 39ከእናንተም ተለይተው የቀሩት በጠላቶቻቸው ምድር ላይ በኃጢአታቸው ይከሳሉ፤ በአባቶቻቸውም ኃጢአት ደግሞ ከእነርሱ ጋር ይከሳሉ። 40በእኔም ላይ በእንቢተኝነት ስለ ሄዱብኝ የበደሉኝን በደል፥ ኃጢአታቸውንም፥ የአባቶቻቸውንም ኃጢአት ይናዘዛሉ። 41እኔም ደግሞ በእንቢተኝነት ሄድሁባቸው፤ ወደ ጠላቶቻቸውም ምድር አገባኋቸው፤ ነገር ግን በዚያን ጊዜ ያልተገረዘው ልባቸው ቢዋረድ፥ የኃጢአታቸውንም ቅጣት ቢቀበሉ፥ 42እኔ ለያዕቆብ የማልሁትን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ደግሞ ለይስሐቅና ለአብርሃም የማልሁትን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ምድሪቱንም አስባለሁ። 43ምድርም ከእነርሱ መጥፋት የተነሣ ባዶ ትቀራለች፤ እነርሱም ሳይኖሩ በተፈታችበት ዘመን ሰንበት በማድረግዋ ትደሰታለች፤ ፍርዴንም ስለ ናቁ፥ ነፍሳቸውም ሥርዓቴን ስለ ተጸየፈች የኃጢአታቸውን ቅጣት ይሸከማሉ። 44ነገር ግን እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ነኝና እነርሱ በጠላቶቻቸው ምድር ሳሉ፥ እስካጠፋቸው ድረስ ከእነርሱም ጋር ያለኝን ቃል ኪዳን እስካፈርስ ድረስ አልጥላቸውም አልጸየፋቸውምም። 45እኔ አምላካቸው እሆን ዘንድ አሕዛብ እያዩ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸውን የአባቶቻቸውን ቃል ኪዳን ስለ እነርሱ አስባለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 46እግዚአብሔርም በእርሱና በእስራኤል ልጆች መካከል በሲና ተራራ ላይ በሙሴ እጅ ያደረጋቸው ሥርዓቶችና ፍርዶች ሕግጋትም እነዚህ ናቸው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 26: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ