ኦሪት ዘሌዋውያን 27
27
የመጠጥ ቁርባን
1ጌታ ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ ማናቸውም ሰው ሰውን ለጌታ ሊሰጥ ቢሳል፥ አንተ እንደምትገምተው መጠን ስለ ሰው ተመጣጣኝ የሆነውን ዋጋ ይስጥ። 3ለወንድ ከሃያ ዓመት ጀምሮ እስከ ስልሳ ዓመት ድረስ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ግምትህ ኀምሳ የብር ሰቅል ይሁን። 4ሴትም ብትሆን ግምትህ ሠላሳ ሰቅል ይሁን። 5ከአምስት ዓመትም ጀምሮ እስከ ሀያ ዓመት ድረስ ግምትህ ለወንድ ሀያ ሰቅል፥ ለሴትም ዐሥር ሰቅል ይሁን። 6ከአንድ ወርም እስከ አምስት ዓመት ድረስ ለወንድ ግምትህ አምስት የብር ሰቅል፥ ለሴትም ግምትህ ሦስት የብር ሰቅል ይሁን። 7ዕድሜውም ስልሳ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆነው ሰው ቢሆን ለወንድ ግምትህ ዐሥራ አምስት ሰቅል፥ ለሴትም ዐሥር ሰቅል ይሁን። 8ማናቸውም ሰው ለግምትህ ከድህነቱ የተነሣ የሚከፍለውን ቢያጣ እርሱም በካህኑ ፊት የስለቱን ሰው የምጣው፥ ካህኑም እርሱን ይገምተው፤ ካህኑም የተሳለው ሰው አቅሙ እንደሚፈቅደው መጠን ይገምትለት።
9“ለጌታም መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርበው እንስሳ ቢሆን፥ ሰው ከእነዚህ ለጌታ የሚሰጠው ሁሉ ቅዱስ ይሆናል። 10መልካሙን በክፉ ወይም ክፉውን በመልካም ቢሆንም እንኳ እርሱን በሌላ አትተካ ወይንም አትለውጥ፤ እንስሳንም በእንስሳ ቢለውጥ እርሱና ልዋጩ ሁለቱም የተቀደሱ ይሆናሉ። 11እንስሳው ለጌታ መሥዋዕት መሆን የማይገባው ርኩስ ቢሆን፥ እንስሳውን በካህኑ ፊት ያምጣው። 12ካህኑም መልካም ወይም መጥፎ እንደሆነ ይገምተዋል፤ ካህኑም እንደሚገምተው መጠን እንዲሁ ይሁን። 13እርሱም ሊቤዠው ቢወድድ ግን በተገመተው ላይ አምስት እጅ ይጨምር።
14“ለጌታም ቅዱስ ይሆን ዘንድ ሰው ቤቱን ቢቀድስ፥ ካህኑ መልካም ወይም መጥፎ እንደሆነ ይገምተዋል፤ ካህኑም እንደሚገምተው መጠን እንዲሁ ይጸናል። 15የቀደሰውም ሰው ቤቱን ሊቤዠው ቢወድድ በገመትከው የገንዘብ መጠን ላይ አምስት እጅ ይጨምራል፤ ቤቱም ለእርሱ ይሆናል።
16“ሰውም ከርስቱ እርሻ ለጌታ ቢቀድስ፥ ግምትህ ለእርሻው እንደሚያስፈልገው የዘር መጠን ይሁን፤ አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ የሚዘራበት እርሻ ኀምሳ የብር ሰቅል ይገመታል። 17እርሻውንም ከኢዮቤልዩ ዓመት ጀምሮ ቢቀድስ፥ እንደ ግምትህ መጠን ይጸናል። 18ነገር ግን እርሻውን ከኢዮቤልዩ ዓመት በኋላ ቢቀድስ፥ ካህኑ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ እንደ ቀሩት ዓመታት ቊጥር ገንዘቡን ያስላልህስ፤ ከዚያም ከግምትህ ላይ ይቀነሳል። 19እርሻውንም የቀደሰ ሰው ሊቤዠው ቢወድድ፥ በገመትከው የገንዘብ መጠን ላይ አምስት እጅ ይጨምራል፤ ከዚያም ለእርሱ ይጸናለታል። 20እርሻውንም ባይቤዠው፥ ወይም ለሌላ ሰው ቢሸጥ፥ እንደገና ሊቤዠው አይችልም። 21እርሻው ግን በኢዮቤልዩ ነፃ ሲወጣ እንደ እርም ለጌታ የተቀደሰ እርሻ ይሆናል፤ ለካህኑ ርስቱ ይሆናል። 22ከርስቱ እርሻ ያልሆነውን የገዛውን እርሻ ለጌታ ቢቀድስ፥ 23ካህኑ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ የግምቱን ዋጋ ያሰላለታል፤ በዚያም ቀን ግምቱን እንደ ተቀደሰ ነገር ለጌታ ይሰጣል። 24በኢዮቤልዩ ዓመት እርሻው የምድሪቱ ባለ ርስት ወደነበረው ወደሸጠው ሰው ይመለሳል። 25ግምትህም ሁሉ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ይሆናል፤ ሰቅሉ ሀያ አቦሊ ይሆናል።
26“ዳሩ ግን ለጌታ የሆነውን የእንስሳ በኵራት ማንም ሰው ሊቀድሰው አይችልም፤ በሬ ቢሆን ወይም በግ ለጌታ ነው። 27የረከሰም እንስሳ ቢሆን እንደ ግምትህ መጠን ይቤዠዋል፤ በእርሱም ዋጋ ላይ አምስት እጅ ይጨምርበታል፤ ባይቤዥም እንደ ግምትህ ይሸጣል።
28 #
ዘኍ. 18፥14። “ነገር ግን ሰው የእርሱ ከሆነው ነገር ሁሉ ለጌታ ለይቶ እርም ያደረገው፥ ሰው ቢሆን ወይም እንስሳ ወይም የርስቱ እርሻ ቢሆን፥ አይሸጥም፥ አይቤዥም፤ እርም የሆነ ነገር ሁሉ ለጌታ እጅግ የተቀደሰ ነው። 29ከሰዎችም እርም የሆነ ሰው ሁሉ አይዋጅም፤ ፈጽሞ ይገደላል።
30 #
ዘኍ. 18፥21፤ ዘዳ. 14፥22-29። “የምድሪቱም አሥራት ሁሉ፥ ከምድሪቱ ዘር ወይም ከዛፍ ፍሬ ቢሆን፥ የጌታ ነው፤ ለጌታ የተቀደሰ ነው። 31ሰውም አሥራቱን ሊቤዥ ቢወድድ፥ በእርሱ ላይ አምስት እጅ ይጨምርበት። 32ከበሬም ሁሉ ከዐሥር አንድ፥ ከእረኛውም በትር በታች ከሚያልፍ በግና ፍየል ሁሉ ከዐሥር አንድ ለጌታ የተቀደሰ ይሆናል። 33መልካም ወይም መጥፎ እንደሆነ አይመርምር፥ አይለውጥም፤ ቢለውጠውም እርሱና ልዋጩ ሁለቱም የተቀደሱ ይሆናሉ፤ አይቤዥም።”
34ጌታ በሲና ተራራ ላይ ለእስራኤል ልጆች ሙሴን ያዘዘው ትእዛዛት እነዚህ ናቸው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 27: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ