ኦሪት ዘኍልቊ መግቢያ

መግቢያ
ይህ መጽሐፍ ኦሪት ዘኍልቊ የሚለውን ስያሜ ያገኘው በምዕራፍ አንድና በምዕራፍ ሀያ ስድስት ላይ ከተጠቀሱት ሁለት የሕዝብ ቈጠራዎች ነው። ይህ መጽሐፍ እስራኤላውያን የተስፋይቱን ምድር ከመውረሳቸው በፊት ያለውን የአርባ ዓመት የምድረ በዳ የጉዞ ታሪክና እግዚአብሔር የሰጣቸውን ሕጎች ይመለከታል። እስራኤላውያን በዚህ የአርባ ዓመት የምድረ በዳ ጉዞ አርባ በሚሆኑ ቦታዎች ላይ ሰፍረዋል (ዘኍ. 33) ከእነዚህም ስፍራዎች የጉዞውን ጠቅላላ ገጽታ የሚያሳዩን ሦስት ስፍራዎች አሉ፤ እነርሱም የሲና ምድረ በዳ (1፥1) የፋራን ምድረ በዳና (10፥12) የሞዓብ ሜዳ (36፥13) ናቸው። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመጓዝ ሁለት የጉዞ መስመሮችን ተጠቅመዋል። አንደኛው የቃዴስ የጉዞ መስመር ሲሆን እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ተራራ በመነሣት በሦስት ቀን ጉዞ (10፥33) ወደ ሐጼሮት የሚያደርጉት ጉዞ ነው (13—35)። ከዚያም ከቃዴስ ወይም ከጺን ምድረ በዳ ወደ ሖር ተራራ ይጓዛሉ (20፥22)። ሁለተኛው የፋራን የጉዞ መስመር ሲሆን እስራኤላውያን ከሲን ጉዞአቸውን ይጀምራሉ (10፥12) የሚያበቁትም በፋራን ምድረ በዳ ነው (12፥16)። ከዚያም ከፋራን ምድረ በዳ ወደ ቃዴስ ወይም ወደ ጺን ምድረ በዳ ይጓዛሉ (20፥1)። ኦሪት ዘኍልቊ ሲጀምር የእስራኤል ማኅበር የእግዚአብሔርን ማድረያ ማዕከል በማድረግ እንዴት እንደተዋቀረ ይናገራል። ይህም የአሮን ልጆች፤ ሌዋውያኑና የእስራኤል ማኅበር ግዴታቸውን መፈጸም ስላለባቸው ኃላፊነት ይገልጻል (1—9)። ከዚህ በኋላ የእስራኤል ማኅበር በእግዚአብሔር ምሪት በምድረ በዳ ሲጓዝና በተለያዩ ፈተናዎች በእግዚአብሔር ላይ ያለውን እምነት ሲያጎድልና ኃጢአት ሲሠራ ይገልጻል (9—25)። የእስራኤል ማኅበር የተላኩትን ሰላዮች አለማመኑ (13፥1—14፥45) የሌዋውያኑ በደልና ውጤቱ። መጨረሻም መጽሐፉ እስራኤላውያን የተስፋይቱን ምድር ለመውረስ መዘጋጀታቸውንና ሙሴ ሥልጣኑን ለኢያሱ የሚያስተላልፍ መሆኑን ይገልጻል (27፥12-23) (26፥13—36፥13)። ኦሪት ዘኍልቊ እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ እስራኤላውያንን በመቤዠት (ዘኍ. 11) ወደ ተስፋይቱ ምድር በሚያደርጉት ጉዞ የሚሰጣቸውን መለኮታዊ ምሪት (9፥15-23) የሚናገር መጽሐፍ ነው።
መጽሐፉ በሁለት ዐበይት ክፍሎች ይከፈላል። አንደኛው ክፍል ከምዕራፍ አንድ እስከ ምዕራፍ ሀያ አምስት ያለውን የሚያካትት ሲሆን ዓመፀኛ ስለ ሆነው የመጀመርያው ማለትም ስለ ጥንቱ ትውልድ የሚናገር ነው። ሁለተኛው ክፍል ከምዕራፍ ሀያ ስድስት እስከ ሠላሳ ስድስት ያለውን የሚያጠቃልል ሲሆን የከነዓንን ምድር ለመውረስ ተስፋ ስለ ሰነቀው ስለ ሁለተኛው ማለትም ስለ አዲሱ ትውልድ ይናገራል። እንዲሁም ይህ መጽሐፍ በሦስት ንዑስ ክፍሎች ይከፈላል። አንደኛው ንዑስ ክፍል ከምዕራፍ አንድ እስከ ምዕራፍ ዐሥር ቊጥር ዐሥር ያለውን የሚያካትት ሲሆን በሲና ምድረ በዳ በቅዱስ እግዚአብሔር ማደርያ ዘንድ የተዋቀረውን የእስራኤልን ማኅበር ይመለከታል። ሁለተኛው ንዑስ ክፍል ከምዕራፍ ዐሥር ቊጥር ዐሥራ አንድ እስከ ምዕራፍ ሀያ አንድ ቊጥር ሠላሳ አምስት ድረስ ያለው ሲሆን የመጀመርያው ማለትም የጥንቱ ትውልድ በምድረ በዳ ውስጥ ያደረገውን ጉዞ ይመለከታል። ሦስተኛው ንዑስ ክፍል ከምዕራፍ ሀያ ሁለት ቊጥር አንድ እስከ ምዕራፍ ሠላሳ ስድስት ቊጥር ዐሥራ ሦስት ድረስ ያለው ሲሆን ሁለተኛው አዲሱ ትውልድ ወደ ከነዓን ለመግባት በሞዓብ ሜዳ ላይ ዝግጅቱን ሲያደርግ የሚመለከት ነው።
ኦሪት ዘኍልቊ በዋነኝነት ቅዱስ እግዚአብሔር በእስራኤል ማኅበር ውስጥ ማዕከላዊ ስፍራ እንዳለው፥ በምድረ በዳ የእስራኤል ማኅበር እንደ መንግሥት ሆኖ እንደ ተመሠረተ፥ ለእግዚአብሔር በፈተና ውስጥ ፍጹም መታዘዝ እንደሚገባ፥ አለመታዘዝ ግን ምን ዓይነት አስከፊ ውጤት እንዳለው፥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ በማስተዳደርና በመምራት ሙሴና ካህናቱ ምን ዓይነት ሚና እንደተጫወቱ፥ የሚገልጽና ጠንካራ መልእክቶችን የሚያስተላልፍ መጽሐፍ ነው።
አጠቃላይ የመጽሐፉ ይዘት
እስራኤላውያን ከሲና ተራራ ተነሥተው ለመሄድ መዘጋጀታቸው (1፥1—9፥23)
የመጀመሪያው የሕዝብ ቈጠራ (1፥1—4፥49)
የተለያዩ ሕጎችና ደንቦች (5፥1—8፥26)
ሁለተኛው ፋሲካ (9፥1-23)
ከሲና ተራራ ወደ ሞዓብ (10፥1—21፥35)
በሞዓብ የተፈጸሙ ሁኔታዎች (22፥1—32፥42)
ከግብጽ እስከ ሞዓብ የተደረገው ጉዞ ባጭሩ (33፥1-49)
ዮርዳኖስን ከመሻገር በፊት የተሰጡ መመሪያዎች (33፥50—36፥13)
ምዕራፍ

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ