ዘሌዋውያን 25:18-23
ዘሌዋውያን 25:18-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“ሥርዐቴንም አድርጉ፤ ፍርዴንም ጠብቁ፤ አድርጉትም፤ በምድሪቱም ውስጥ ተዘልላችሁ ትኖራላችሁ። ምድሪቱም ፍሬዋን ትሰጣለች፤ እስክትጠግቡም ድረስ ትበላላችሁ፤ በእርስዋም ውስጥ ተዘልላችሁ ትኖራላችሁ። እናንተም፦ ‘ካልዘራን፥ እህላችንንም ካላከማቸን በሰባተኛው ዓመት ምን እንበላለን?’ ብትሉ፥ እኔ በስድስተኛው ዓመት በረከቴን በላያችሁ እሰጣለሁ፤ ምድሪቱም የሦስት ዓመት ፍሬ ታፈራለች። በስምንተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ፤ ከከረመውም እህል ትበላላችሁ፤ ፍሬዋ እስኪገባ፥ እስከ ዘጠነኛው ዓመት ድረስ፥ ከከረመው እህል ትበላላችሁ። “ምድርም ለእኔ ናትና፥ እናንተም በእኔ ፊት እንግዶችና መጻተኞች ናችሁና ምድርን ለዘለዓለም አትሽጡ።
ዘሌዋውያን 25:18-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ ‘ሥርዐቴን ጠብቁ፤ ሕጌን በጥንቃቄ አድርጉ፤ በምድሪቱም በሰላም ትኖራላችሁ። ምድሪቱ ፍሬዋን ትሰጣለች፤ እስክትጠግቡ ትበላላችሁ፤ በዚያም በሰላም ትኖራላችሁ። እናንተም፣ “ካልዘራን ወይም ሰብላችንን ካልሰበሰብን በሰባተኛው ዓመት ምን እንበላለን?” በማለት ትጠይቁ ይሆናል። በስድስተኛው ዓመት በረከቴን እሰድድላችኋለሁ፤ ምድሪቱም ለሦስት ዓመት የሚበቃ ፍሬ ትሰጣለች። በስምንተኛው ዓመት በምትዘሩበት ጊዜ፣ የምትበሉት ቀድሞ ከሰበሰባችሁት ሰብል ይሆናል፤ የዘጠነኛውን ዓመት መከር እስክትሰበስቡ ድረስ ከዚሁ እህል ትበላላችሁ። “ ‘መሬት ለዘለቄታ አይሸጥ፤ ምክንያቱም ምድሪቱ የእኔ ናት፤ እናንተም መጻተኞችና እንግዶች ናችሁ።
ዘሌዋውያን 25:18-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሥርዓቴንም አድርጉ፥ ፍርዶቼንም ጠብቁ አድርጉትም፤ በምድሪቱም ውስጥ በጸጥታ ትኖራላችሁ። ምድሪቱም ፍሬዋን ትሰጣለች፥ እስክትጠግቡም ድረስ ትበላላችሁ፤ በእርስዋም ውስጥ በጸጥታ ትኖራላችሁ። እናንተም፦ ካልዘራን፥ እህላችንንም ካላከማቸን በሰባተኛው ዓመት ምን እንበላለን? ብትሉ፥ እኔ በስድስተኛው ዓመት በረከቴን በላያችሁ አዝዛለሁ፤ ምድሪቱም የሦስት ዓመት ፍሬ ታፈራለች። በስምንተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ፥ ከአሮጌውም እህል ትበላላችሁ፤ ፍሬዋ እስኪገባ፥ እስከ ዘጠነኛው ዓመት ድረስ፥ ከአሮጌው እህል ትበላላችሁ። ምድርም ለእኔ ናትና፥ እናንተም ከእኔ ጋር እንግዶችና መጻተኞች ናችሁና ምድርን ለዘላለም አትሽጡ።
ዘሌዋውያን 25:18-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“በምድሪቱ ላይ በሰላም ትኖሩ ዘንድ የእግዚአብሔርን ሕግና ሥርዓት ሁሉ አክብሩ፤ ምድሪቱም ራስዋ በቂ ሰብል ስለምታስገኝ የምትበሉትን ሁሉ አግኝታችሁ በምቾትና በሰላም ትኖራላችሁ። “ነገር ግን በሰባተኛው ዓመት ዘር ካልዘራንና ሰብል ካልሰበሰብን ምን እንበላለን ብላችሁ ብትጠይቁ፤ በስድስተኛው ዓመት እኔ ምድሪቱን እባርካታለሁ፤ ስለዚህም ለሦስት ዓመት የሚበቃ ሰብል ታስገኛለች፤ በስምንተኛው ዓመት እንኳ ዘራችሁን ስትዘሩ የምትመገቡት ቀድሞ የሰበሰባችሁትን መከር ነው፤ ይህንኑ መከር የዘጠነኛውን ዓመት መከር እስከምትሰበስቡ ድረስ ትበላላችሁ። “ምድሪቱ ለዘለቄታ መሸጥ አይገባትም፤ እርስዋ የእኔ እንጂ የእናንተ አይደለችም፤ እናንተ እንደ መጻተኛ ሆናችሁ እንድትጠቀሙባት ብቻ ፈቅጃለሁ።
ዘሌዋውያን 25:18-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“ሥርዓቶቼን አድርጉ፥ ፍርዴንም ጠብቁ አድርጉትም፤ በምድሪቱም ላይ በደኅንነት ትቀመጣላችሁ። ምድሪቱም ፍሬዋን ትሰጣለች፥ እስክትጠግቡም ድረስ ትበላላችሁ፤ በእርሷም ላይ በደኅንነት ትቀመጣላችሁ። ዳሩ ግን እናንተ፦ ‘ካልዘራን፥ እህላችንንም ካላከማቸን በሰባተኛው ዓመት ምን እንበላለን?’ ብትሉ፥ እኔ በስድስተኛው ዓመት በረከቴን በእናንተ ላይ አዝዛለሁ፤ ምድሪቱም የሦስት ዓመት ፍሬ ታፈራለች። በስምንተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ፥ ቀድሞ ከተመረተው እህል ትበላላችሁ፤ የእርሷ ፍሬ እስከሚገባ፥ እስከ ዘጠነኛው ዓመት ድረስ፥ ቀድሞ ከተመረተው እህል ትበላላችሁ። ምድሪቱም የእኔ ናትና፥ እናንተም ከእኔ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች ናችሁና ምድሪቱን ለዘለዓለም አትሽጧት።