ዘሌዋውያን 23:39-43
ዘሌዋውያን 23:39-43 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከሰባተኛውም ወር በዐሥራ አምስተኛው ቀን የምድሩን ፍሬ ካከማቻችሁ በኋላ፥ የእግዚአብሔርን በዓል ሰባት ቀን ታደርጋላችሁ፤ የመጀመሪያዋ ቀን ዕረፍት ትሁን፤ ስምንተኛዋም ቀን ዕረፍት ትሁን። በመጀመሪያዋ ቀን የመልካም ዛፍ ፍሬ፥ የዘንባባውንም ቅርንጫፍ፥ የለመለመውንም ዛፍ ቅርንጫፍ፥ የወንዝም አኻያ ዛፍ ውሰዱ፤ በአምላካችሁም በእግዚአብሔር ፊት በየዓመቱ ሰባት ቀን ደስ ይበላችሁ። በየዓመቱ በሰባተኛው ወር ይህን በዓል ታደርጉ ዘንድ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሕግ ይሁንላችሁ። ሰባት ቀን በዳሶች ውስጥ ትቀመጣላችሁ፤ ከግብፅ ምድር ባወጣኋቸው ጊዜ የእስራኤልን ልጆች በዳስ ውስጥ እንዳስቀመጥኋቸው የልጅ ልጆቻችሁ ያውቁ ዘንድ፥ በእስራኤል ያሉት የሀገር ልጆች ሁሉ በዳስ ውስጥ ይቀመጡ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና።”
ዘሌዋውያን 23:39-43 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ ‘የምድራችሁን ፍሬ ከሰበሰባችሁ በኋላ በሰባተኛው ወር ከዐሥራ አምስተኛው ቀን ጀምራችሁ ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓል አክብሩ፤ የመጀመሪያው ቀን የዕረፍት ዕለት ነው፤ ስምንተኛውም ቀን እንደዚሁ የዕረፍት ዕለት ይሆናል። በመጀመሪያው ቀን የመልካም ዛፍ ፍሬ፣ የዘንባባ ዝንጣፊ፣ የለመለመ ዛፍ ቅርንጫፍ የአኻያ ዛፍ ቅርንጫፍ ይዛችሁ ሰባት ቀን በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ደስ ይበላችሁ። በየዓመቱም የእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓል አድርጋችሁ ሰባት ቀን አክብሩ፤ ይህም ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዐት ነው፤ በሰባተኛውም ወር አክብሩት። ሰባት ቀን ዳስ ውስጥ ተቀመጡ፤ በትውልዱ እስራኤላዊ የሆነ ሁሉ ዳስ ውስጥ ይሰንብት፤ በዚህም እኔ እስራኤላውያንን ከግብፅ ባወጣሁ ጊዜ፣ ዳስ ውስጥ እንዲቀመጡ ማድረጌን የልጅ ልጆቻችሁ ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።’ ”
ዘሌዋውያን 23:39-43 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከሰባተኛውም ወር በአሥራ አምስተኛው ቀን የምድሩን ፍሬ ካከማቻችሁ በኋላ፥ የእግዚአብሔርን በዓል ሰባት ቀን ጠብቁ፤ በመጀመሪያው ቀን ዕረፍት ይሁን፥ በስምንተኛውም ቀን ዕረፍት ይሁን። በመጀመሪያው ቀን የመልካም ዛፍ ፍሬ፥ የሰሌን ቅርንጫፍ፥ የለመለመውን ዛፍ ቅርንጫፍ፥ የወንዝም አኻያ ዛፍ ውሰዱ፤ በአምላካችሁም በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ቀን ደስ ይበላችሁ። ይህንንም በዓል በየዓመቱ ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር አድርጉ፤ ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ነው፤ በሰባተኛው ወር ትጠብቁታላችሁ። ሰባት ቀን በዳሶች ውስጥ ትቀመጣላችሁ፤ ከግብፅ ምድር ባወጣኋቸው ጊዜ የእስራኤልን ልጆች በዳስ ውስጥ እንዳስቀመጥኋቸው የልጅ ልጆቻችሁ ያውቁ ዘንድ፥ በእስራኤል ያሉት የአገር ልጆች ሁሉ በዳስ ውስጥ ይቀመጡ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
ዘሌዋውያን 23:39-43 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ ሰባተኛው ወር ከገባ ከዐሥራ አምስተኛው ቀን በመጀመር ይህን የደስታ በዓል በእግዚአብሔር ፊት እስከ ሰባት ቀን ድረስ ታከብራላችሁ፤ መጀመሪያውና ስምንተኛው ቀን ልዩ የዕረፍት ቀን ይሆናል። በዚያም በመጀመሪያው ቀን ከምድራችሁ ዛፎች ምርጥ ፍሬ፥ የዘንባባ ዝንጣፊና የለምለም ዛፍ ቅርንጫፍ የወንዝ አኻያ ዛፍ ይዛችሁ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት እየተደሰታችሁ እስከ ሰባት ቀን ድረስ በዓል አድርጉ። ይህንንም በዓል በየዓመቱ በሰባተኛው ወር ለሰባት ቀን ለእግዚአብሔር በደስታ አክብሩ፤ ይህም ለልጅ ልጆቻችሁ የዘለዓለም ሥርዓት ነው፤ ለሰባት ቀኖች በዳሶች ትቀመጣላችሁ፤ መላው የእስራኤል ሕዝብ በዳስ ይቀመጣሉ። ስለዚህም እኔ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ከግብጽ ምድር ባወጣሁ ጊዜ ዳሶችን እየጣሉ እንዲኖሩ ማድረጌን የልጅ ልጆቻችሁ ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።”
ዘሌዋውያን 23:39-43 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“በሰባተኛውም ወር በዓሥራ አምስተኛው ቀን የምድሪቱን ምርት በሰበሰባችሁ ጊዜ የጌታን በዓል ሰባት ቀን ጠብቁ፤ በመጀመሪያው ቀን ዕረፍት ይሁን፥ በስምንተኛውም ቀን ዕረፍት ይሁን። በመጀመሪያው ቀን የመልካም ዛፍ ፍሬ፥ የዘንባባ ዝንጣፊ፥ የለመለመውን ዛፍ ቅርንጫፍ፥ የወንዝም አኻያ ዛፍ ውሰዱ፤ በአምላካችሁም በጌታ ፊት ሰባት ቀን ደስ ይበላችሁ። ይህንንም በዓል በየዓመቱ ሰባት ቀን ለጌታ አድርጉ፤ ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዓት አድርጋችሁ በሰባተኛው ወር ትጠብቁታላችሁ። ሰባት ቀን በዳሶች ውስጥ ትቀመጣላችሁ፤ በእስራኤል ያሉት የአገሩ ተወላጆች ሁሉ በዳሶች ውስጥ ይቀመጣሉ፤ በዚህም ከግብጽ ምድር ባወጣኋቸው ጊዜ የእስራኤልን ልጆች በዳሶች ውስጥ እንዳስቀመጥኋቸው የልጅ ልጆቻችሁ እንዲያውቁ ነው፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ።”