ኢዮብ 9:15-35
ኢዮብ 9:15-35 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ጻድቅ ብሆንም እንኳ፣ ልመልስለት አልችልም፤ ዳኛዬን ምሕረት ከመለመን ሌላ ላደርግ የምችለው የለም። ጠርቼው ‘አቤት!’ ቢለኝም፣ ያዳምጠኛል ብዬ አላምንም። በዐውሎ ነፋስ ይሰብረኛል፤ ቍስሌንም ያለ ምክንያት ያበዛል፤ ምሬትን አጠገበኝ እንጂ፣ ለመተንፈስ እንኳ ፋታ አልሰጠኝም። የኀይል ነገር ከተነሣ፣ እርሱ ኀያል ነው! የፍትሕም ነገር ከተነሣ፣ መጥሪያ ሊሰጠው የሚችል ማን ነው? ንጹሕ ብሆን እንኳ፣ አንደበቴ ይፈርድብኛል፤ እንከን የለሽ እንኳ ብሆን፣ በደለኛ ያደርገኛል። “ያለ ነቀፋ ብሆንም እንኳ፣ ስለ ራሴ ግድ የለኝም፤ የገዛ ሕይወቴንም እንቃታለሁ። ሁሉም አንድ ነው፤ ‘እርሱ ጻድቁንና ኀጥኡን ያጠፋል’ የምለውም ለዚህ ነው። መዓት ወርዶ ድንገት ሰው ሲጨርስ፣ በንጹሓን መከራ ይሣለቃል። ምድር በክፉዎች እጅ ስትወድቅ፣ እርሱ የፈራጆቿን ዐይን ይሸፍናል፤ ታዲያ፣ ይህን ያደረገው እርሱ ካልሆነ ማን ሊሆን ይችላል? “ዘመኔ ከሚሮጥ ሰው ይልቅ ይፈጥናል፤ አንዳችም ደስታ ሳያይ ያልፋል። ከደንገል እንደ ተሠራ ታንኳ፣ ለመንጠቅ ቍልቍል እንደሚበርር ንስር ይፈጥናል። ‘ማጕረምረሜን እረሳለሁ፤ ገጽታዬን ቀይሬ ፈገግ እላለሁ’ ብል፣ ንጹሕ አድርገህ እንደማትቈጥረኝ ስለማውቅ፣ መከራዬን ሁሉ እፈራለሁ። በደለኛ መሆኔ ካልቀረ፣ ለምን በከንቱ እለፋለሁ? ሰውነቴን በሳሙና ብታጠብ፣ እጄንም በልዩ መታጠቢያ ባነጻ፣ ልብሴ እንኳ እስኪጸየፈኝ ድረስ፣ በዐዘቅት ውስጥ ታሰጥመኛለህ። “መልስ እሰጠው ዘንድ፣ እሟገተውም ዘንድ፣ እርሱ እንደ እኔ ሰው አይደለም። በሁለታችን ላይ እጅ የሚጭን፣ በመካከላችንም የሚዳኝ ቢኖር፣ ግርማው እንዳያስፈራኝ፣ እግዚአብሔር በትሩን ከእኔ ላይ ቢያነሣ፣ ሳልፈራው በተናገርሁት ነበር፤ አሁን ባለሁበት ሁኔታ ግን፣ አልችልም።
ኢዮብ 9:15-35 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በጽድቅ ብጠራው፥ ባይሰማኝም፥ የእርሱን ፍርድ እለምናለሁ። ብጠራው፥ እርሱም ቢመልስልኝ ኖሮ፥ እንደ ሰማኝ አላምንም ነበር። “በዐውሎ ነፋስ ይቀጠቅጠኛል፤ ያለ ምክንያት ብዙ ጊዜ ያቈስለኛል። እተነፍስ ዘንድ አይተወኝም፤ ነገር ግን መራራ ነገርን አጥግቦኛል። እርሱ በኀይል ይይዛልና፤ ፍርዱን ማን ይቃወማል? ጻድቅ ብሆን አፌ ይወቅሰኛል፤ ፍጹምም ብሆን ጠማማ ያደርገኛል። ንጹሕ ነኝ፤ ራሴንም አላውቅም፤ ነገር ግን ሕይወቴ ጠፋች። “ስለዚህ እንዲህ እላለሁ፦ ታላቁና ኀያሉ መቅሠፍትን ይልካል። የኃጥኣን ሞታቸው ክፉ ነውና፥ በጻድቃን ይስቃሉ። በኃጥኣን እጅ ተሰጥተዋልና፤ የምድር ፈራጆችን ፊት ይሸፍናል፤ እርሱ ካልሆነ ማን ነው? ሕይወቴ ከሚሮጥ ሰው ይልቅ ይፈጥናል፤ ይሸሻል፥ መልካምንም አያይም። የመርከብ መንገድ ፍለጋ፥ ወይም የሚበርና የሚበላውን የሚፈልግ የንስር ፍለጋ እንደማይታወቅ ሕይወቴ እንዲሁ ሆነ። እኔ ብናገር የሚጠቅመኝ የለም፤ ፊቴም በጩኸት ወደቀ፤ ሰውነቶቼ ሁሉ ተነዋወጡ፤ እንግዲህ ንጹሕ አድርገህ እንደማትተወኝ አውቃለሁ፥ “ኃጢኣተኛ ሰው ከሆንሁ፤ ስለ ምን አልሞትሁም? ብታጠብ፥ እንደ በረዶም ብነጻ፥ እጆቼንም እጅግ ባነጻ፥ በአዘቅት ውስጥ ታሰጥመኛለህ፤ ልብሴም ይጸየፈኛል። የሚከራከረኝ ሰው ቢሆን ኖሮ፥ ወደ አደባባይ በአንድነት በሄድን ነበር! ማዕከላዊ ዳኛ ቢኖር፥ በሁለታችንም መካከል የሚሰማ ቢገኝ ኖሮ፥ በትሩ ከእኔ ላይ በራቀ ነበር፤ ግርማውም ባላስፈራኝ ነበር። እናገርም ነበር፤ አልፈራምም ነበር፤ የማውቀውም ነገር የለም።
ኢዮብ 9:15-35 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ጻድቅ ብሆን ኖሮ አልመልስለትም ነበር፥ ወደ ፈራጄም እለምን ነበር። ብጠራው እርሱም ቢመልስልኝ ኖሮ፥ ቃሌን እንደ ሰማ አላምንም ነበር። በዐውሎ ነፋስ ይሰብረኛል፥ ቍስሌንም ያለ ምክንያት ያበዛል። እተነፍስ ዘንድ አይተወኝም፥ ነገር ግን መራራን ነገር አጥግቦኛል። የኃይል ነገር ቢሆን እርሱ ኃያል ነው፥ የፍርድ ነገር ቢሆን፦ ጊዜን ወሳኙ ማን ነው? ይላል። ጻድቅ ብሆን አፌ ይወቅሰኛል፥ ፍጹምም ብሆን ጠማማ ያደርገኛል። ፍጹም ነኝ ራሴንም አልመለከትም፥ ሕይወቴንም እንቃታለሁ። ይህ ሁሉ አንድ ነው፥ ስለዚህ፦ ፍጹማንንና ክፉዎችን ያጠፋል እላለሁ። መቅሠፍቱ ፈጥኖ ቢገድል፥ በንጹሐን ፈተና ይሳለቃል። ምድር በኃጥአን እጅ ተሰጥታለች፥ የፈራጆችዋን ፊት ሸፍኖአል፥ እርሱ ካልሆነ ማን ነው? ዘመኔ ከሚሮጥ ሰው ይልቅ ይፈጥናል፥ ይሸሻል፥ መልካምንም አያይም። የደንገል ታንኳ እንደሚፈጥን፥ ንስርም ወደ ንጥቂያው እንደሚበርር ያልፋል። እኔ፦ የኀዘን እንጕርጕሮዬን እረሳለሁ፥ ፊቴን መልሼ እጽናናለሁ ብል፥ ንጹሕ እንደማታደርገኝ እኔ አውቃለሁና ከመከራዬ ሁሉ እፈራለሁ። በደለኛ እንደሚሆን ሰው እሆናለሁ፥ ስለ ምንስ በከንቱ እደክማለሁ? በአመዳይ ውስጥ ብታጠብ፥ እጆቼንም እጅግ ባነጻ፥ በአዘቅት ውስጥ ታሰጥመኛለህ፥ ልብሴም ይጸየፈኛል። እንድመልስለት አብረን ወደ ፍርድ እንገባ ዘንድ፥ እርሱ እንደ እኔ ሰው አይደለም። እጁን በሁለታችን ላይ የሚያኖር ዳኛ በመካከላችን ምነው በተገኘ! በትሩን ከእኔ ላይ ያርቅ፥ ግርማውም አያስፈራኝ፥ እናገርም ነበር፥ አልፈራውምም ነበር፥ በራሴ እንዲህ አይደለሁምና።
ኢዮብ 9:15-35 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ንጹሕ ሆኜ ብገኝ እንኳ፥ ፈራጁ አምላክ እንዲምረኝ እለምነዋለሁ እንጂ መልስ ልሰጠው አልደፍርም። የእርሱን ስም ብጠራና መልስ ቢሰጠኝም እንኳ አቤቱታዬን ያዳምጣል ብዬ አላምንም። በዐውሎ ነፋስ ያደቀኛል ያለ ምክንያትም ቊስሌን ያበዛል። ትንፋሽ እስካገኝ እንኳ ፋታ አይሰጠኝም፤ ሕይወቴን በሥቃይ ሞልቶታል። ባለኝ ኀይል ልታገለው እንዳልል፥ በኀይል እርሱን የሚቋቋም የለም፤ ተሟግቼ እረታዋለሁ እንዳልል፥ እርሱን ወደ ፍርድ ሸንጎ ሊያቀርበው የሚችል የለም። እኔ ንጹሕና እውነተኛ ነኝ፤ ነገር ግን አነጋገሬ በደለኛ ያደርገኛል፤ የምናገራቸው ንግግሮች ሁሉ ይፈርዱብኛል። ምንም እንኳ ፍጹም ብሆን ስለ ራሴ አላስብም ሕይወቴንም እጸየፈዋልሁ። እግዚአብሔር ፍጹሙንና በደለኛውን ስለሚያጠፋ ምንም ልዩነት የለም ያልሁት ስለዚህ ነው። በአደጋ ሰው ሲቀሠፍ እርሱ በንጹሕ ሰው ችግር ይሳለቃል። ምድር በክፉ ሰዎች እጅ ተላልፋ ስትሰጥ እርሱ የዳኞችን ዐይን ይሸፍናል፤ ይህን ያደረገ እግዚአብሔር ካልሆነ ታዲያ፥ ማነው? “የዕድሜዬ ቀኖች ከሯጭ ይልቅ የፈጠኑ ናቸው ምንም ደስታ ሳላይ ያልፋሉ። እነርሱም ከደንገል እንደ ተሠራ ታንኳ ይሮጣሉ፤ እንደ ነጣቂ ንስርም ይፈጥናሉ። ሮሮዬን ልርሳ፥ ፊቴንም ማጥቈር ትቼ ፈገግታ ላሳይ ብል፥ እግዚአብሔር ንጹሕ አድርጎ እንደማይቈጥረኝ ስለማውቅ፥ መከራና ሥቃይ ይመጣብኛል ብዬ እፈራለሁ። እንግዲህ በደለኛ ሆኜ ከተቈጠርኩ፥ በከንቱ መድከሜ ለምንድን ነው? ሰውነቴን በሳሙና ባጥብ፥ እጄንም በእንዶድ ባጸዳ ይህም ሁሉ ሆኖ አንተ ወደ አዘቅት ትጥለኛለህ፤ የገዛ ልብሴ እንኳ ይጸየፈኛል። እርሱ እንደ እኔ ሰው ስላልሆነ፥ ወደ ፍርድ ሸንጎ ሄደን፥ እንፋረድ ልለው አልችልም። ከጀርባዬ እግዚአብሔር በትሩን እንዲያነሣና ግርማውም እንዳያስፈራኝ እጁን በሁለታችን ላይ የሚያኖር ዳኛ በመካከላችን ምነው በተገኘ! እኔ ሰዎች እንደሚያስቡኝ ስላልሆንኩ እርሱን ሳልፈራው በተናገርኩት ነበር።
ኢዮብ 9:15-35 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጻድቅ ብሆንም እንኳን ልመልስለት አልችልም፥ ፈራጄን እማጸናለሁ እንጂ። ብጠራው እርሱም ቢመልስልኝ ኖሮ፥ ቃሌን ሰማ ብዬ አላምንም ነበር። በዐውሎ ነፋስ ይሰብረኛል፥ ቁስሌንም ያለ ምክንያት ያበዛል። እተነፍስ ዘንድ አይተወኝም፥ ነገር ግን መራራን ነገር አጥግቦኛል። የኃይል ነገር ከሆነ፥ ኃያሉ እርሱ እነሆ፥ የፍርድ ነገር ከሆነም፥ የችሎቱን ጊዜ ወሳኙ ማን ነው? ይላል። ጻድቅ ብሆን እንኳን አፌ ይወቅሰኛል፥ ፍጹምም ብሆን ጠማማ ያደርገኛል። ፍጹም ነኝ ራሴንም አልመለከትም፥ ሕይወቴንም እንቃታለሁ። ይህ ሁሉ አንድ ነው፥ ስለዚህ፦ ፍጹማንንና ክፉዎችን ያጠፋል እላለሁ። መቅሠፍቱ ፈጥኖ ቢገድል፥ በንጹሐን ፈተና ይሳለቃል። ምድር በኃጥአን እጅ ተሰጥታለች፥ የፈራጆችዋን ፊት ሸፍኖአል፥ ይህንን ያደረገው እርሱ ካልሆነ ሌላ ማን ነው?” “ቀኖቼ ከሚሮጥ ሰው ይልቅ ይፈጥናሉ፥ ይሸሻሉ፥ መልካምንም አያዩም። የደንገል ታንኳ እንደሚፈጥን፥ ንስርም ወደ ንጥቂያው እንደሚበርር ያልፋሉ። እኔ፦ የኀዘን እንጉርጉሮዬን እረሳለሁ፥ ፊቴን መልሼ እጽናናለሁ ብል፥ ንጹሕ እንደማታደርገኝ እኔ አውቃለሁና ከመከራዬ ሁሉ የተነሣ እፈራለሁ። በደለኛ እሆናለሁ፥ ስለ ምንስ በከንቱ እደክማለሁ? በአመዳይ ውስጥ ብታጠብ፥ እጆቼንም እጅግ ባነጻ፥ በአዘቅት ውስጥ ታሰጥመኛለህ፥ ልብሴም ይጸየፈኛል። እንድመልስለት አብረን ወደ ፍርድ እንገባ ዘንድ፥ እርሱ እንደ እኔ ሰው አይደለም። እጁን በሁለታችን ላይ የሚያኖር ዳኛ በመካከላችን ምነው በተገኘ! በትሩን ከእኔ ላይ ያርቅ፥ ግርማውም አያስፈራኝ፥ እናገርም ነበር፥ አልፈራውምም ነበር፥ በራሴ እንዲህ አይደለሁምና።”