የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢዮብ 9:15-35

መጽሐፈ ኢዮብ 9:15-35 መቅካእኤ

ጻድቅ ብሆንም እንኳን ልመልስለት አልችልም፥ ፈራጄን እማጸናለሁ እንጂ። ብጠራው እርሱም ቢመልስልኝ ኖሮ፥ ቃሌን ሰማ ብዬ አላምንም ነበር። በዐውሎ ነፋስ ይሰብረኛል፥ ቁስሌንም ያለ ምክንያት ያበዛል። እተነፍስ ዘንድ አይተወኝም፥ ነገር ግን መራራን ነገር አጥግቦኛል። የኃይል ነገር ከሆነ፥ ኃያሉ እርሱ እነሆ፥ የፍርድ ነገር ከሆነም፥ የችሎቱን ጊዜ ወሳኙ ማን ነው? ይላል። ጻድቅ ብሆን እንኳን አፌ ይወቅሰኛል፥ ፍጹምም ብሆን ጠማማ ያደርገኛል። ፍጹም ነኝ ራሴንም አልመለከትም፥ ሕይወቴንም እንቃታለሁ። ይህ ሁሉ አንድ ነው፥ ስለዚህ፦ ፍጹማንንና ክፉዎችን ያጠፋል እላለሁ። መቅሠፍቱ ፈጥኖ ቢገድል፥ በንጹሐን ፈተና ይሳለቃል። ምድር በኃጥአን እጅ ተሰጥታለች፥ የፈራጆችዋን ፊት ሸፍኖአል፥ ይህንን ያደረገው እርሱ ካልሆነ ሌላ ማን ነው?” “ቀኖቼ ከሚሮጥ ሰው ይልቅ ይፈጥናሉ፥ ይሸሻሉ፥ መልካምንም አያዩም። የደንገል ታንኳ እንደሚፈጥን፥ ንስርም ወደ ንጥቂያው እንደሚበርር ያልፋሉ። እኔ፦ የኀዘን እንጉርጉሮዬን እረሳለሁ፥ ፊቴን መልሼ እጽናናለሁ ብል፥ ንጹሕ እንደማታደርገኝ እኔ አውቃለሁና ከመከራዬ ሁሉ የተነሣ እፈራለሁ። በደለኛ እሆናለሁ፥ ስለ ምንስ በከንቱ እደክማለሁ? በአመዳይ ውስጥ ብታጠብ፥ እጆቼንም እጅግ ባነጻ፥ በአዘቅት ውስጥ ታሰጥመኛለህ፥ ልብሴም ይጸየፈኛል። እንድመልስለት አብረን ወደ ፍርድ እንገባ ዘንድ፥ እርሱ እንደ እኔ ሰው አይደለም። እጁን በሁለታችን ላይ የሚያኖር ዳኛ በመካከላችን ምነው በተገኘ! በትሩን ከእኔ ላይ ያርቅ፥ ግርማውም አያስፈራኝ፥ እናገርም ነበር፥ አልፈራውምም ነበር፥ በራሴ እንዲህ አይደለሁምና።”