መጽሐፈ ኢዮብ 9
9
1 #
ኢዮብ 4፥17። ኢዮብም መለሰ፤ እንዲህም አለ፦
2“በእውነት እንዲህ እንደሆነ አወቅሁ፥
ሰውስ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ መሆን እንዴት ይችላል?
3ከእርሱ ጋር መከራከር ቢፈልግ፥
ከሺህ ነገር አንዱን መመለስ አይችልም።
4ልቡ ጠቢብ፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥
እርሱንስ ተዳፍሮ በደኅና የቆየ ማን ነው?
5ተራሮችን ይነቅላል፥ ነገር ግን አያውቁትም፥
በቁጣውም ይገለብጣቸዋል።
6ምድርን ከስፍራዋ ያናውጣታል፥
ምሰሶችዋም ይንቀጠቀጣሉ።
7 #
ባሮክ 3፥34፤35። ፀሐይን ያዝዛታል፥ አትወጣምም፥
ከዋክብትንም ያትማል።
8ሰማያትን ብቻውን ይዘረጋል፥
በባሕሩም ማዕበል ላይ ይረግጣል።
9 #
ኢዮብ 38፥31፤ አሞጽ 5፥8። ድብ የሚባለውን እና ኦሪዮን የሚባለውን ኮከብ፥ ሰባቱንም ከዋክብት፥
በደቡብም በኩል ያሉትን የከዋክብት ማደሪያዎች ሠርቶአል።
10የማይመረመረውን ታላላቅ ነገር፥
የማይቈጠረውንም ተአምራት ያደርጋል።
11እነሆ፥ ቢመጣብኝ አላየውም፥
ቢያልፍብኝም አላውቀውም።
12እነሆ፥ ፈጥኖ ቢነጥቅ የሚከለክለው ማን ነው?
እርሱንስ፦ ምን ታደርጋለህ? የሚለው ማን ነው?”
13“እግዚአብሔር ቁጣውን አይመልስም፥
ከእርሱ በታች ረዓብን#9፥13 የጥልቅ ባሕር አውሬ። የሚረዱ ይዋረዳሉ።
14ይልቁንስ እመልስለት ዘንድ፥
ቃሌንስ በፊቱ እመርጥ ዘንድ እኔ ማን ነኝ?
15ጻድቅ ብሆንም እንኳን ልመልስለት አልችልም፥
ፈራጄን እማጸናለሁ እንጂ።
16ብጠራው እርሱም ቢመልስልኝ ኖሮ፥#9፥16 ኢዮብ “ብጠራው” ሲል “አቤቱታ አቅርቤ እግዚብሔርን ለፍርድ ብጠራው” ማለቱ ነው።
ቃሌን ሰማ ብዬ አላምንም ነበር።
17በዐውሎ ነፋስ ይሰብረኛል፥
ቁስሌንም ያለ ምክንያት ያበዛል።
18እተነፍስ ዘንድ አይተወኝም፥
ነገር ግን መራራን ነገር አጥግቦኛል።
19የኃይል ነገር ከሆነ፥ ኃያሉ እርሱ እነሆ፥
የፍርድ ነገር ከሆነም፥ የችሎቱን ጊዜ ወሳኙ ማን ነው? ይላል።
20ጻድቅ ብሆን እንኳን አፌ ይወቅሰኛል፥
ፍጹምም ብሆን ጠማማ ያደርገኛል።
21ፍጹም ነኝ ራሴንም አልመለከትም፥
ሕይወቴንም እንቃታለሁ።
22ይህ ሁሉ አንድ ነው፥ ስለዚህ፦
ፍጹማንንና ክፉዎችን ያጠፋል እላለሁ።
23መቅሠፍቱ ፈጥኖ ቢገድል፥
በንጹሐን ፈተና ይሳለቃል።
24ምድር በኃጥአን እጅ ተሰጥታለች፥
የፈራጆችዋን ፊት ሸፍኖአል፥
ይህንን ያደረገው እርሱ ካልሆነ ሌላ ማን ነው?”
25“ቀኖቼ ከሚሮጥ ሰው ይልቅ ይፈጥናሉ፥
ይሸሻሉ፥ መልካምንም አያዩም።
26የደንገል ታንኳ እንደሚፈጥን፥
ንስርም ወደ ንጥቂያው እንደሚበርር ያልፋሉ።
27እኔ፦ የኀዘን እንጉርጉሮዬን እረሳለሁ፥
ፊቴን መልሼ እጽናናለሁ ብል፥
28ንጹሕ እንደማታደርገኝ እኔ አውቃለሁና
ከመከራዬ ሁሉ የተነሣ እፈራለሁ።
29በደለኛ እሆናለሁ፥
ስለ ምንስ በከንቱ እደክማለሁ?
30በአመዳይ ውስጥ ብታጠብ፥
እጆቼንም እጅግ ባነጻ፥
31በአዘቅት ውስጥ ታሰጥመኛለህ፥
ልብሴም ይጸየፈኛል።
32እንድመልስለት አብረን ወደ ፍርድ እንገባ ዘንድ፥
እርሱ እንደ እኔ ሰው አይደለም።
33እጁን በሁለታችን ላይ የሚያኖር ዳኛ
በመካከላችን ምነው በተገኘ!
34በትሩን ከእኔ ላይ ያርቅ፥
ግርማውም አያስፈራኝ፥
35እናገርም ነበር፥ አልፈራውምም ነበር፥
በራሴ እንዲህ አይደለሁምና።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 9: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ