መጽሐፈ ኢዮብ 9
9
1ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ፦
2በእውነት እንዲህ እንደ ሆነ አወቅሁ፥
ሰውስ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ መሆን እንዴት ይችላል?
3ከእርሱ ጋር ይከራከር ዘንድ ቢወድድ፥
ከሺህ ነገር አንዱን መመለስ አይችልም።
4ልቡ ጠቢብ፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥
ደፍሮትስ በደኅና የሄደ ማን ነው?
5ተራሮችን ይነቅላል፥ አያውቁትም፥
በቍጣውም ይገለብጣቸዋል።
6ምድርን ከስፍራዋ ያናውጣታል፥
ምሰሶችዋም ይንቀጠቀጣሉ።
7ፀሐይን ያዝዛታል፥ አትወጣምም፥
ከዋክብትንም ያትማል።
8ሰማያትን ብቻውን ይዘረጋል፥
በባሕሩም ማዕበል ላይ ይረግጣል።
9ድብ የሚባለውን ኮከብና ኦሪዮን የሚባለውን ኮከብ፥ ሰባቱንም ከዋክብት፥
በደቡብም በኵል ያሉትን የከዋክብት ማደሪያዎች ሠርቶአል።
10የማይመረመረውን ታላላቅ ነገር፥
የማይቈጠረውንም ተአምራት ያደርጋል።
11እነሆ፥ ቢመጣብኝ አላየውም፥
ቢያልፍብኝም አላውቀውም።
12እነሆ፥ ፈጥኖ ቢነጥቅ የሚከለክለው ማን ነው?
እርሱንስ፦ ምን ታደርጋለህ? የሚለው ማን ነው?
13እግዚአብሔር ቍጣውን አይመልስም፥
ከእርሱ በታች ረዓብን የሚረዱ ይዋረዳሉ።
14ይልቁንስ እመልስለት ዘንድ፥
ቃሌንስ በፊቱ እመርጥ ዘንድ እኔ ማን ነኝ?
15ጻድቅ ብሆን ኖሮ አልመልስለትም ነበር፥
ወደ ፈራጄም እለምን ነበር።
16ብጠራው እርሱም ቢመልስልኝ ኖሮ፥
ቃሌን እንደ ሰማ አላምንም ነበር።
17በዐውሎ ነፋስ ይሰብረኛል፥
ቍስሌንም ያለ ምክንያት ያበዛል።
18እተነፍስ ዘንድ አይተወኝም፥
ነገር ግን መራራን ነገር አጥግቦኛል።
19የኃይል ነገር ቢሆን እርሱ ኃያል ነው፥
የፍርድ ነገር ቢሆን፦ ጊዜን ወሳኙ ማን ነው? ይላል።
20ጻድቅ ብሆን አፌ ይወቅሰኛል፥
ፍጹምም ብሆን ጠማማ ያደርገኛል።
21ፍጹም ነኝ ራሴንም አልመለከትም፥
ሕይወቴንም እንቃታለሁ።
22ይህ ሁሉ አንድ ነው፥ ስለዚህ፦
ፍጹማንንና ክፉዎችን ያጠፋል እላለሁ።
23መቅሠፍቱ ፈጥኖ ቢገድል፥
በንጹሐን ፈተና ይሳለቃል።
24ምድር በኃጥአን እጅ ተሰጥታለች፥
የፈራጆችዋን ፊት ሸፍኖአል፥
እርሱ ካልሆነ ማን ነው?
25ዘመኔ ከሚሮጥ ሰው ይልቅ ይፈጥናል፥
ይሸሻል፥ መልካምንም አያይም።
26የደንገል ታንኳ እንደሚፈጥን፥
ንስርም ወደ ንጥቂያው እንደሚበርር ያልፋል።
27እኔ፦ የኀዘን እንጕርጕሮዬን እረሳለሁ፥
ፊቴን መልሼ እጽናናለሁ ብል፥
28ንጹሕ እንደማታደርገኝ እኔ አውቃለሁና
ከመከራዬ ሁሉ እፈራለሁ።
29በደለኛ እንደሚሆን ሰው እሆናለሁ፥
ስለ ምንስ በከንቱ እደክማለሁ?
30በአመዳይ ውስጥ ብታጠብ፥
እጆቼንም እጅግ ባነጻ፥
31በአዘቅት ውስጥ ታሰጥመኛለህ፥
ልብሴም ይጸየፈኛል።
32እንድመልስለት አብረን ወደ ፍርድ እንገባ ዘንድ፥
እርሱ እንደ እኔ ሰው አይደለም።
33እጁን በሁለታችን ላይ የሚያኖር ዳኛ
በመካከላችን ምነው በተገኘ!
34በትሩን ከእኔ ላይ ያርቅ፥
ግርማውም አያስፈራኝ፥
35እናገርም ነበር፥ አልፈራውምም ነበር፥
በራሴ እንዲህ አይደለሁምና።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 9: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ