ኢዮብ 5:1-27
ኢዮብ 5:1-27 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“አሁንም የሚመልስልህ ካለ ጥራ፥ ከቅዱሳን መላእክትም የምታየው ካለ? ሰነፉን ሰው ቍጣ ይገድለዋልና፥ ቅንዓትም ሰነፉን ያጠፋዋል። ሰነፎችን ሥር ሰድደው አየኋቸው፥ በድንገትም መኖሪያቸው ጠፋች። ልጆቻቸው ከደኅንነት ርቀዋል፥ በበርም ውስጥ ይቀጠቅጡአቸዋል፤ መከራም ያጸኑባቸዋል፥ የሚታደጋቸውም የለም። እነርሱ የሰበሰቡትንም ጻድቃን ይበሉታል። እነርሱን ግን ክፋት ቷጋቸዋለች፥ ኀይላቸውም ይደክማል። ችግር ከምድር አይወጣምና፥ መከራም ከተራሮች አይበቅልምና፤ የአሞራ ግልገሎች ግን ወደ ላይ እየበረሩ ከፍ እንዲሉ፥ ሰው እንዲሁ ለድካም ተወልዶአል። “እኔ ግን እግዚአብሔርን እለምነው ነበር፥ የሁሉ ጌታ እግዚአብሔርንም እጠራው ነበር። እርሱ የማይመረመረውን ታላቅ ነገርና የማይቈጠረውን የከበረና ድንቅ ነገር ያደርጋል። በምድር ላይ ዝናብን ይሰጣል፥ ከሰማይም በታች ውኃን ይልካል። የተዋረዱትን ከፍ ያደርጋቸዋል፥ የወደቁትንም ያነሣቸዋል። የተንኰለኞችን ምክር ይለውጣል፥ እጆቻቸውም ቅን አይሠሩም። ጠቢባንንም በተንኰላቸው ይይዛቸዋል፤ ምክርን የሚጐነጉኑ ሰዎችን አሳብ ያጠፋል። በቀን ጨለማ ያገኛቸዋል፥ በቀትርም ጊዜ በሌሊት እንዳሉ ይርመሰመሳሉ። በጦርነት ይጠፋሉ፤ ደካማውም ከኀያሉ እጅ ያመልጣል። ለምስኪኑ ተስፋ አለውና፤ የዐመጸኛም አፍ ይዘጋልና። “ነገር ግን እግዚአብሔር የሚገሥጸው ሰው ብፁዕ ነው፤ ስለዚህ ሁሉን የሚችለውን የአምላክን ተግሣጽ አትናቅ። እርሱ ይሰብራል፥ ዳግመኛም ይጠግናል፤ ይቀሥፋል፥ እጆቹም ይፈውሳሉ። ስድስት ጊዜ ከክፉ ነገር ያድንሃል፥ በሰባተኛውም ጊዜ ክፋት አትነካህም። በራብ ጊዜ ከሞት ያድንሃል፥ በጦርነትም ጊዜ ከሰይፍ እጅ ያድንሃል። ከምላስ ጅራፍ ይሰውርሃል፥ ከምትመጣብህም ክፋት አትፈራም። በኃጥኣንና በዐመጸኞች ላይ ትስቅባቸዋለህ፤ ከምድረ በዳ አራዊትም አትፈራም፤ የምድረ በዳ አራዊትም ከአንተ ጋር ይስማማሉ። ያንጊዜ ቤትህ በሰላም እንዲሆን ታውቃለህ፤ ከንብረትህም አንዳች አይጐድልም። ዘርህም ብዙ እንዲሆን፥ ልጆችህም እንደ አማረ መስክ ሣር እንዲሆኑ ታውቃለህ። በወራቱ የደረሰ አዝመራ እንዲሰበሰብ፥ የእህሉ ነዶም በወቅቱ ወደ አውድማ እንዲገባ፥ በረዥም ዕድሜ ወደ መቃብር ትገባለህ። እነሆ፥ ይህን ዐውቀን መረመርን፥ የሰማነውም ይህ ነው፤ አንተ ግን አንዳች ሠርተህ እንደ ሆነ ለራስህ ዕወቅ።”
ኢዮብ 5:1-27 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“እስኪ ተጣራ፤ የሚመልስልህ አለን? ከቅዱሳንስ ወደ ማንኛው ዘወር ትላለህ? ቂሉን ሰው ብስጭት ይገድለዋል፤ ቂሉንም ቅናት ያጠፋዋል። ቂል ሰው ሥር ሰድዶ አየሁት፤ ግን ድንገት ቤቱ ተረገመ። ልጆቹ የኑሮ ዋስትና የራቃቸው፤ በፍርድ አደባባይ ጥቃት የደረሰባቸው፣ ታዳጊ የሌላቸው ናቸው። ከእሾኽ መካከል እንኳ አውጥቶ፣ ራብተኛ ሰብሉን ይበላበታል፤ ጥማተኛም ሀብቱን ይመኝበታል። ችግር ከምድር አይፈልቅም፤ መከራም ከመሬት አይበቅልም። ፍንጣሪው ከእሳቱ ላይ ሽቅብ እንደሚወረወር፣ ሰውም ለመከራ ይወለዳል። “እኔ ብሆን ኖሮ፣ ወደ እግዚአብሔር በቀረብሁ፣ ጕዳዬንም በፊቱ በገለጽሁለት ነበር። እርሱ፣ የማይመረመሩ ድንቅ ነገሮች፣ የማይቈጠሩም ታምራት ያደርጋል። ምድሪቱን በዝናብ ያረሰርሳል፤ ሜዳውንም ውሃ ያጠጣል። የተዋረዱትን በከፍታ ቦታ ያስቀምጣል፤ ያዘኑትንም ወደ አስተማማኝ ስፍራ ያወጣቸዋል። እጃቸው ያሰቡትን እንዳይፈጽም፣ የተንኰለኞችን ዕቅድ ያከሽፋል። ጥበበኞችን በራሳቸው ተንኰል ይይዛቸዋል፤ የጠማሞችንም ሤራ ያጠፋል። ቀኑ ጨለማ ይሆንባቸዋል፤ በቀትርም ጊዜ በሌሊት እንዳለ ሰው በዳበሳ ይሄዳሉ። ድኻውን ከአፋቸው ሰይፍ፣ ከኀይለኛውም እጅ ያድነዋል። ስለዚህ ድኻ ተስፋ አለው፤ ዐመፅም አፏን ትዘጋለች። “እነሆ፤ እግዚአብሔር የሚገሥጸው ሰው ብፁዕ ነው፤ ስለዚህ ሁሉን ቻይ አምላክ ተግሣጽ አትናቅ። እርሱ ያቈስላል፤ ይፈውሳል፤ እርሱ ይሰብራል፤ በእጁም ይጠግናል፤ እርሱ ከስድስት መቅሠፍት ይታደግሃል፤ በሰባተኛውም ጕዳት አያገኝህም። በራብ ጊዜ ከሞት፣ በጦርነትም ከሰይፍ ያድንሃል። ከምላስ ጅራፍ ትሰወራለህ፤ ጥፋት ሲመጣም አትፈራም። በጥፋትና በራብ ላይ ትሥቃለህ፤ የምድርንም አራዊት አትፈራም። ከሜዳ ድንጋዮች ጋራ ትዋዋላለህና፤ የዱር አራዊትም ከአንተ ጋራ ይስማማሉ። ድንኳንህ በሚያስተማምን ሁኔታ እንዳለ ታውቃለህ፤ በረትህን ትቃኛለህ፤ አንዳችም አይጐድልብህም። ዘሮችህ አያሌ እንደሚሆኑ፣ የምትወልዳቸውም እንደ ሣር እንደሚበዙ ታውቃለህ። የእህል ነዶ ጐምርቶ በወቅቱ እንደሚሰበሰብ፣ ዕድሜ ጠግበህ ወደ መቃብር ትሄዳለህ። “እነሆ፤ ይህን ሁሉ መርምረናል፤ እውነት ሆኖ አግኝተነዋል፤ ስለዚህ ልብ በል፤ ተቀበለውም።”
ኢዮብ 5:1-27 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አሁንም ጥራ፥ የሚመልስልህ አለን? ከቅዱሳንስ ወደማናቸው ትዞራለህ? ሰነፉን ሰው ቍጣ ይገድለዋል፥ ሰነፉንም ቅንዓት ያጠፋዋል። ሰነፍ ሰው ሥር ሰድዶ አየሁት፥ ድንገትም መኖሪያውን ረገምሁ። ልጆቹም ከደኅንነት ርቀዋል፥ በበርም ውስጥ ተረግጠዋል፥ የሚታደጋቸውም የለም። የሰበሰበውንም ራብተኛ ይበላዋል፥ ከእሾህም ውስጥ እንኳ ያወጣዋል፥ የተጠማ ሀብታቸውን ዋጠ። ችግር ከትቢያ አይመጣም፥ መከራም ከመሬት አይበቅልም፥ የአሞራ ግልገሎች ግን ወደ ላይ እየበረሩ ከፍ እንዲሉ፥ ሰው እንዲሁ ለመከራ ተወልዶአል። እኔ ግን እግዚአብሔርን እለምን ነበር፥ ነገሬንም ወደ እግዚአብሔር አቀርብ ነበር። የማይመረመረውን ታላቅ ነገርና የማይቈጠረውን ተአምራት ያደርጋል። በምድር ላይ ዝናብን ይሰጣል፥ በእርሻም ላይ ውኃ ይልካል። የተዋረዱትን ወደ ላይ ያወጣል፥ ኀዘንተኞችንም ለደኅንነት ከፍ ከፍ ያደርጋቸዋል። እጃቸውም ምክራቸውን እንዳይፈጽም የተንኰለኞችን አሳብ ከንቱ ያደርገዋል። ጠቢባንን በተንኰላቸው ይይዛቸዋል፥ የጠማሞችንም ምክር ይዘረዝራል። በቀን ጨለማን ያገኛሉ፥ በቀትርም ጊዜ በሌሊት እንዳሉ ይርመሰመሳሉ። ድሀውንም ከአፋቸው ሰይፍ ከኃያሉም እጅ ያድነዋል። ለምስኪኑም ተስፋ አለው፥ ክፋት ግን አፍዋን ትዘጋለች። እነሆ፥ እግዚአብሔር የሚገሥጸው ሰው ምስጉን ነው፥ ስለዚህ ሁሉን የሚችለውን የአምላክን ተግሣጽ አትናቅ። እርሱ ይሰብራል፥ ይጠግንማል፥ ያቈስላል፥ እጆቹም ይፈውሳሉ። በስድስት ክፉ ነገር ውስጥ ያድንሃል፥ በሰባትም ውስጥ ክፋት አትነካህም። በራብ ጊዜ ከሞት፥ በሰልፍም ከሰይፍ እጅ ያድንሃል። ከምላስ ጅራፍ ትሰወራለህ፥ ጥፋትም ሲመጣ አትፈራም። በጥፋትና በራብ ላይ ትስቃለህ፥ ከምድረ በዳ አራዊትም አትፈራም፥ ቃል ኪዳንህ ከምድረ በዳ ድንጋይ ጋር ይሆናልና፥ የምድረ በዳም አራዊት ከአንተ ጋር ይስማማሉና። ድንኳንህም በሰላም እንዲሆን ታውቃለህ፥ በረትህን ትጐበኛለህ አንዳችም አይጐድልብህም። ዘርህም ታላቅ እንዲሆን፥ ትውልድህም እንደ ምድር ሣር እንዲሆን ታውቃለህ። በወራቱ የእህሉ ነዶ ወደ አውድማ እንዲገባ፥ በረጅም ዕድሜ ወደ መቃብር ትገባለህ። እነሆ፥ ይህችን መረመርን፥ የሰማነውም ይህ ነው፥ አንተ ግን አንዳች ሠርተህ እንደ ሆነ ለራስህ እወቀው።
ኢዮብ 5:1-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ኢዮብ ሆይ! መልስ የሚሰጥህ ሰው ብታገኝ እስቲ ተጣራ፤ ርዳታ ይሰጥህ ዘንድ ከመላእክቱ ወደ ማንኛው ትመለከታለህ? ቊጣ ሞኝን ይገድለዋል፤ ቅናትም ሰውን ያጠፋል። ሞኝ ደርጅቶ ሲኖር አየሁ፤ በእግዚአብሔር ቊጣ በድንገት መኖሪያው ፈራረሰ። ልጆቹም የኑሮ ዋስትና አያገኙም፤ በአደባባይም የሚከራከርላቸው ስለማያገኙ ጥቃት ይደርስባቸዋል። ሰብሉንም የተራቡ ሰዎች ይበሉታል፤ በእሾኽ መካከል የበቀለውን እንኳ አይተውለትም፤ የተጠሙ ሰዎችም ሀብቱን ለመውሰድ ይጐመዣሉ። ችግር ከዐፈር አይነሣም፤ መከራም ከመሬት አይበቅልም። የእሳት ፍንጣሪ ከፍም ላይ ተነሥቶ ወደ ዐየር እንደሚበር፥ እንደዚሁም ሰው ለመከራ ይወለዳል። “እኔ አንተን ብሆን ኖሮ ወደ እግዚአብሔር እማጠን ነበር፤ ችግሬን ሁሉ እገልጥለት ነበር። እርሱ የማይቈጠረውን ተአምራት፦ የማይመረመረውን ታላቅ ነገር ያደርጋል። በምድር ላይ ዝናብን ያዘንባል፤ እርሻዎችንም በውሃ ያረሰርሳል። የተዋረዱትን በክብር ከፍ ያደርጋቸዋል፤ ያዘኑትንም በማጽናናት ደስ ያሰኛቸዋል። ሥራቸው እንዳይሳካ የተንኰለኞችን ዕቅድ ከንቱ ያደርጋል። ጥበበኞችን የራሳቸው ተንኰል ወጥመድ ሆኖ እንዲይዛቸው ያደርጋል የተንኰለኞችም ዕቅድ በፍጥነት ይጠፋል። ቀኑ ጨለማ ይሆንባቸዋል፤ ገና በእኩለ ቀን፥ በሌሊት ጨለማ ውስጥ እንዳሉ ሆነው ይደናበሩ። ድኾችን ከጠላቶቻቸው ሰይፍ ያድናቸዋል፤ ችግረኞችንም ከጨቋኞች እጅ ነጻ ያወጣቸዋል። ለድኾች ተስፋ ይሰጣል፤ ዐመፅንም ከምድረ ገጽ ያጠፋል። “እግዚአብሔር የሚገሥጸው ሰው የተባረከ ነው! ስለዚህ የልዑል እግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ። እግዚአብሔር ቢያቈስልህም መልሶ ይጠግንሃል፤ በአንድ እጁ ቢጐዳህ በሌላ እጁ ይፈውስሃል። ከስድስት ዐይነት የመቅሠፍት አደጋዎች ይታደግሃል፤ በሰባተኛውም ምንም ጒዳት አይደርስብህም። በራብ ዘመን በሕይወት ያኖርሃል። በጦርነትም ጊዜ ከሞት ያድንሃል። እግዚአብሔር ከክፉ ምላስ ይጠብቅሃል፤ ጥፋት ቢመጣብህም አትፈራም። የኀያላን አጥቂነትና ራብ አያስደነግጡህም፤ የምድርንም አራዊት አትፈራም። በምታርሰው መሬት ላይ ድንጋይ አያውክህም፤ ከአራዊትም ጋር በሰላም ትኖራለህ። በድንኳንህ ሰላም እንደሚሰፍን ታረጋግጣለህ፤ የበጎችህንም በረት ስትጐበኝ ሁሉን በደኅና ታገኛቸዋለህ። ትውልድህ እንደሚበዛ ታውቃለህ፤ ዘርህም እንደ መስክ ሣር ይበዛል። የስንዴ እሸት እስኪጐመራ በማሳ ላይ እንደሚቈይ አንተም በዕድሜ እስከምትሸመግል ትኖራለህ። እኛ ይህን ሁሉ መርምረን እውነት መሆኑን ዐውቀናል አንተም አስተውለህ ተግባራዊ አድርገው።”
ኢዮብ 5:1-27 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“አሁንም ተጣራ፥ የሚመልስልህ አለን? ከቅዱሳንስ ወደማናቸው ትዞራለህ? አላዋቂውን ሰው ቁጣ ይገድለዋል፥ ሞኙንም ቅንዓት ያጠፋዋል። አላዋቂውን ሰው ሥር ሰድዶ አየሁት፥ ድንገትም መኖሪያውን ረገምሁ። ልጆቹም ከደኅንነት ርቀዋል፥ በበርም ውስጥ ተረግጠዋል፥ የሚደርስላቸውም የለም። የሰበሰበውንም የተራበ ይበላዋል፥ ከእሾህም ውስጥ እንኳ ያወጣዋል፥ የተጠማ ሀብታቸውን ዋጠ። ችግር ከትቢያ አይመጣም፥ መከራም ከመሬት አይበቅልም፥ ሰው ለመከራ ተወልዶአል የአሞራ ግልገሎች ወደ ላይ እየበረሩ ከፍ እንደሚሉ። እኔ ግን እግዚአብሔርን እለምን ነበር፥ ነገሬንም ወደ እግዚአብሔር አቀርብ ነበር። የማይመረመረውን ታላቅ ነገርና የማይቈጠረውን ተአምራት ያደርጋል። በምድር ላይ ዝናብን ይሰጣል፥ በእርሻም ላይ ውኃ ይልካል። የተዋረዱትን ወደ ላይ ያወጣል፥ ያዘኑትን ለደኅንነት ከፍ ያደርጋቸዋል። የተንኰለኞችን አሳብ ከንቱ ያደርገዋል፥ እጃቸውም ደባቸውን ከግብ እንዳያደርስ። ጠቢባንን በተንኰላቸው ይይዛቸዋል፥ የጠማሞችንም ምክር ያጠፋል። በቀን ጨለማን ያገኛሉ፥ በቀትርም ጊዜ በሌሊት እንዳሉ ይርመሰመሳሉ። ድሀውን ከአፋቸው ሰይፍ አንዲሁም ከኃያላን እጅ ያድነዋል። ለምስኪኑም ተስፋ አለው፥ ግፍ ግን አፍዋን ትዘጋለች። እነሆ፥ እግዚአብሔር የሚገሥጸው ሰው ብፁዕ ነው፥ ስለዚህ ሁሉን የሚችለውን የአምላክን ተግሣጽ አትናቅ። እርሱ ቢያቈስልም ይጠግናልና፥ ቢሰብርም፥ እጆቹ ይፈውሳሉና። ከስድስት ችግሮች ያድንሃል፥ በሰባተኛውም ውስጥ ክፋት አትነካህም። በራብ ጊዜ ከሞት፥ በሰልፍም ጊዜ ከሰይፍ እጅ ያድንሃል። ከምላስ ጅራፍ ትሰወራለህ፥ የጥፋት አደጋ ሲመጣም አትፈራም። በጥፋት አደጋና በራብ ላይ ትስቃለህ፥ የምድረ በዳ አራዊትንም አትፈራም፥ ቃል ኪዳንህ ከምድረበዳ ድንጋይ ጋር ይሆናልና፥ የምድረ በዳም አራዊት ከአንተ ጋር ይስማማሉና። ድንኳንህ ሰላምን እንደሚያገኝም ታውቃለህ፥ በረትህን ትጐበኛለህ፥ አንዳችም አይጐድልብህም። ዘርህም እንደሚበዛ፥ ትውልድህም እንደ ምድር ሣር ብዙ እንደሚሆን ታውቃለህ። የእህሉ ነዶ ወራቱ ሲደርስ ወደ አውድማ እንደሚገባ፥ ዕድሜ ጠግበህ ወደ መቃብር ትገባለህ። እነሆ፥ ይህችን መረመርን፥ የሰማነውም ይህ ነው፥ አንተም ለራስህ እወቀው።”