ኢዮብ 42:8-10
ኢዮብ 42:8-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አሁን እንግዲህ ሰባት ወይፈኖችንና ሰባት አውራ በጎችን ይዛችሁ ወደ ባሪያዬ ወደ ኢዮብ ዘንድ ሂዱ፥ እርሱም የሚቃጠልን መሥዋዕት ስለ ራሳችሁ ያሳርግላችሁ። ባሪያዬም ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልይ፥ እኔም ፊቱን እቀበላለሁ። ስለ እርሱ ባይሆን ባጠፋኋችሁ ነበር። በባሪያዬ በኢዮብ ላይ ቅን ነገርን በፊቴ አልተናገራችሁምና።” ቴማናዊውም ኤልፋዝ፥ አውኬናዊው በልዳዶስና፥ አሜናዊው ሶፋር ሄደው እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ ስለ ኢዮብም ሲል ኀጢአታቸውን ይቅር አላቸው። እግዚአብሔርም ኢዮብን አዳነው። ኢዮብም ስለ ወዳጆቹ ጸለየ፥ እግዚአብሔርም ኀጢአታቸውን ተወላቸው፤ እግዚአብሔርም ቀድሞ በነበረው ገንዘቡ ሁሉ ፋንታ ሁለት እጥፍ ከዚያም በላይ አድርጎ ለኢዮብ ሰጠው።
ኢዮብ 42:8-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አሁን እንግዲህ ሰባት ወይፈኖችና ሰባት አውራ በጎች ይዛችሁ ወደ አገልጋዬ ወደ ኢዮብ ሂዱ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትም ስለ ራሳችሁ አቅርቡ። እንደ አሳፋሪ ተግባራችሁ እንዳላደርግባችሁ አገልጋዬ ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል፤ እኔም ጸሎቱን እቀበላለሁ፤ እንደ አገልጋዬ እንደ ኢዮብ ስለ እኔ ቅን ነገር አልተናገራችሁምና።” ቴማናዊው ኤልፋዝ፣ ሹሐዊው በልዳዶስና ናዕማታዊው ሶፋር እግዚአብሔር እንደ ተናገራቸው አደረጉ፤ እግዚአብሔርም የኢዮብን ጸሎት ተቀበለ። ኢዮብ ለወዳጆቹ ከጸለየ በኋላ፣ እግዚአብሔር እንደ ገና አበለጸገው፤ ቀድሞ በነበረው ፈንታ ዕጥፍ አድርጎ ሰጠው።
ኢዮብ 42:8-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አሁን እንግዲህ ሰባት ወይፈኖችና ሰባት አውራ በጎች ይዛችሁ ወደ ባሪያዬ ወደ ኢዮብ ዘንድ ሂዱ፥ የሚቃጠልንም መሥዋዕት ስለ ራሳችሁ አሳርጉ፥ ባሪያዬም ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል፥ እኔም እንደ ስንፍናችሁ እንዳላደርግባችሁ ፊቱን እቀበላለሁ፥ እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ ቅን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና። ቴማናዊውም ኤልፋዝ ሹሐዊውም በልዳዶስ ናዕማታዊውም ሶፋር ሄደው እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው አደረጉ፥ እግዚአብሔርም የኢዮብን ፊት ተቀበለ። ኢዮብም ስለ ወዳጆቹ በጸለየ ጊዜ እግዚአብሔርም ምርኮውን መለሰለት፥ እግዚአብሔር ቀድሞ በነበረው ፋንታ ሁለት እጥፍ አድርጎ ለኢዮብ ሰጠው።
ኢዮብ 42:8-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህ አሁን ሰባት ኰርማዎችንና ሰባት አውራ በጎችን ይዛችሁ ወደ አገልጋዬ ወደ ኢዮብ ሂዱ፤ እዚያም ስለ ራሳችሁ ኃጢአት የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ፤ አገልጋዬ ኢዮብ ይጸልይላችኋል፤ እኔም ጸሎቱን ሰምቼ በበደላችሁ መጠን አልቀጣችሁም፤ እናንተ እንደ ኢዮብ ስለ እኔ ትክክል የሆነውን ነገር አልተናገራችሁም።” ከዚህ በኋላ ቴማናዊው ኤሊፋዝ፥ ሹሐዊውም ቢልዳድና ናዕማታዊውም ጾፋር ሄደው እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ እግዚአብሔርም የኢዮብን ጸሎት ሰማ። ኢዮብ ለሦስቱ ወዳጆቹ ከጸለየ በኋላ እግዚአብሔር እንደገና እንዲበለጽግ አደረገው፤ ዱሮ ከነበረውም ይበልጥ እጥፍ አድርጎ ሰጠው።
ኢዮብ 42:8-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አሁን እንግዲህ ሰባት ወይፈኖችና ሰባት አውራ በጎች ይዛችሁ ወደ አገልጋዬ ወደ ኢዮብ ሂዱ፥ የሚቃጠልንም መሥዋዕት ስለ ራሳችሁ አሳርጉ፥ አገልጋዬም ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል፥ እኔም እንደ ጥፋታችሁ እንዳላደርግባችሁ ጸሎቱን እሰማለሁ፥ እንደ አገልጋዬ እንደ ኢዮብ ቅን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና።” ቴማናዊውም ኤልፋዝ ሹሐዊውም በልዳዶስ ናዕማታዊውም ሶፋር ሄደው ጌታ እንዳዘዛቸው አደረጉ፥ ጌታም የኢዮብን ጸሎት ሰማ። ኢዮብም ስለ ወዳጆቹ ሲጸልይ ጌታ ምርኮውን መለሰለት፥ ጌታ ቀድሞ በነበረው ፋንታ በሁለት እጥፍ አሳድጎ ለኢዮብ ሰጠው።