መጽሐፈ ኢዮብ 42
42
1ኢዮብም መለሰ፥ እግዚአብሔርንም እንዲህ አለው፦ 2“ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደ ሆንህ፥ የሚሳንህም እንደሌለ ዐወቅሁ። 3ምክርን ከአንተ የሚሰውር፥ ቃሉንም ከአንተ የሚሸልግና የሚሸሽግ የሚመስለው ማን ነው? የማላስተውለውንና የማላውቀውንም ታላቅና ድንቅ ነገር የሚነግረኝ ማን ነው?
4“ጌታ ሆይ፥ እባክህ፥ ስማኝ፥ እኔም ልናገር፤ እጠይቅህማለሁ፥ አንተም አስተምረኝ። 5መስማትንስ ስለ አንተ ቀድሞ በጆሮዬ ሰምቼ ነበር፤ አሁን ግን ዐይኔ አየችህ፤ 6ስለዚህ ራሴን እንቃለሁ፤ ሰውነቴም ቀለጠ። እኔ አፈርና አመድ እንደ ሆንሁ አውቃለሁ።”
የኢዮብ ወዳጆች እንደ ተወቀሱ
7እግዚአብሔርም ይህን ቃል ለኢዮብ ከተናገረ በኋላ እግዚአብሔር ቴማናዊውን ኤልፋዝን እንዲህ አለው፥ “እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ አንዲት ቅን ነገርን በፊቴ አልተናገራችሁምና አንተና ሁለቱ ባልንጀሮችህ በድላችኋል። 8አሁን እንግዲህ ሰባት ወይፈኖችንና ሰባት አውራ በጎችን ይዛችሁ ወደ ባሪያዬ ወደ ኢዮብ ዘንድ ሂዱ፥ እርሱም የሚቃጠልን መሥዋዕት ስለ ራሳችሁ ያሳርግላችሁ። ባሪያዬም ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልይ፥ እኔም ፊቱን እቀበላለሁ። ስለ እርሱ ባይሆን ባጠፋኋችሁ ነበር። በባሪያዬ በኢዮብ ላይ ቅን ነገርን በፊቴ አልተናገራችሁምና።”
9ቴማናዊውም ኤልፋዝ፥ አውኬናዊው በልዳዶስና፥ አሜናዊው ሶፋር ሄደው እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ ስለ ኢዮብም ሲል ኀጢአታቸውን ይቅር አላቸው።
የኢዮብ ጤናና ሀብት እንደ ተመለሰ
10እግዚአብሔርም ኢዮብን አዳነው።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “አበለጠገው” ይላል። ኢዮብም ስለ ወዳጆቹ ጸለየ፥ እግዚአብሔርም ኀጢአታቸውን ተወላቸው፤ እግዚአብሔርም ቀድሞ በነበረው ገንዘቡ ሁሉ ፋንታ ሁለት እጥፍ ከዚያም በላይ አድርጎ ለኢዮብ ሰጠው። 11ወንድሞቹና እኅቶቹ ቀድሞም ያውቁት የነበሩት ሁሉ የሆነውን ሁሉ በሰሙ ጊዜ ወደ እርሱ መጡ፥ በቤቱም ከእርሱ ጋር እንጀራ በሉ፥ ጠጡም፤ አጽናኑትም፤ እግዚአብሔርም ባመጣበት ክፉ ነገር ሁሉ አደነቁ፤ እያንዳንዳቸውም ጥማድ በሬ፥#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የበግ ጠቦት” ይላል። አራት ድራህማ የሚመዝን ወርቅና ብር ሰጡት።
12እግዚአብሔርም ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን ለኢዮብ ባረከ፤ መንጋዎቹም ዐሥራ አራት ሺህ በጎች፥ ስድስት ሺህም ግመሎች፥ አንድ ሺህም ጥማድ በሬዎች፥ አንድ ሺህም እንስት አህዮች ነበሩ። 13ደግሞም ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆች ተወለዱለት። 14የመጀመሪያይቱን ስም ዕለት፥ የሁለተኛይቱንም ስም ቃስያ፥ የሦስተኛይቱንም ስም አማልትያስቂራስ ብሎ ሰየማቸው። 15ከሰማይ በታች እንደ ኢዮብ ሴቶች ልጆች ያሉ የተዋቡ ሴቶች በሀገሩ ሁሉ አልተገኙም፤ አባታቸውም ከወንድሞቻቸው ጋር ርስት ሰጣቸው።
16ኢዮብም ከደዌው ከዳነ በኋላ መቶ ሰባ#ዕብ. “መቶ አርባ” ይላል። ዓመት ኖረ፥ ኢዮብም የኖረበት ዘመን ሁሉ ሁለት መቶ አርባ#ዕብ. “ሁለት መቶ አርባ ስምንት” ይላል። ነው። ልጆቹንና የልጅ ልጆቹንም እስከ አራት ትውልድ ድረስ አየ። 17ኢዮብም ሸምግሎ ዕድሜም ጠግቦ ሞተ። 18#ምዕ. 42 ከቍ. 18 እስከ 25 በዕብ. የለም። እግዚአብሔር ከሚያነሣቸው ሰዎች ጋር ዳግመኛ እንደሚነሣ የተጻፈ ነው።
19ይህ ሰው በሶርያው መጽሐፍ እንደዚህ ተገልጦአል። የኖረበትም ሀገሩ በኤዶምያስና በዐረብ አውራጃ ያለ አውስጢድ ነው። 20ስሙም ቀድሞ ኢዮባብ ነበረ፥ ዐረባዊት ሴትንም አገባ። ስሙ ሄኖን የሚባል ልጅንም ወለደችለት። እርሱም የኤሳው የልጅ ልጅ የዛራ ልጅ ነው። እናቱም ባሱራስ ትባል ነበር። 21እርሱም ከአብርሃም አምስተኛ ነው። እርሱም በገዛት ሀገር በኤዶምያስ የነገሡ ነገሥታት እነዚህ ነበሩ። 22አስቀድሞ የነገሠ የቢዖር ልጅ ባላቅ ነው። የከተማዋም ስም ዲናባ ነበር። 23ከባላቅም በኋላ ስሙ ኢዮብ ይባል የነበረው ኢዮባብ ነገሠ። ከእርሱም በኋላ በቴማን ሀገር የነገሠ አሶም ነበር። 24ከእርሱም በኋላ በሞዓብ ምድረ በዳ የምድያምን ሰዎች የገደላቸው የበራድ ልጅ አዳድ ነበር፥ የከተማውም ስም ጌቴም ነበር። 25ወደ እርሱ የመጡ ወዳጆቹም አንዱ ከዔሳው ልጆች የተወለደ በቴማኖን የነገሠው ኤልፋዝ፥ በአውኪኒዮን የተሾመው በልዳዶስና የአሜኔዎን ንጉሥ ሶፋር ነበሩ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 42: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ