መጽሐፈ ኢዮብ 42
42
1ኢዮብም መለሰ እግዚአብሔርንም እንዲህ አለው፦
2ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደ ሆንህ፥
አሳብህም ይከለከል ዘንድ ከቶ እንደማይቻል አወቅሁ።
3ያለ እውቀት ምክርን የሚሰውር ማን ነው?
ስለዚህ እኔ የማላስተውለውን፥
የማላውቀውንም ድንቅ ነገር ተናግሬአለሁ።
4እባክህ፥ ስማኝ፥ እኔም ልናገር፥
እጠይቅህማለሁ፥ አንተም ተናገረኝ።
5መስማትንስ በጆሮ በመስማት ሰምቼ ነበር፥
አሁን ግን ዓይኔ አየችህ፥
6ስለዚህ ራሴን እንቃለሁ፥
በአፈርና በአመድ ላይ ተቀምጬ እጸጸታለሁ።
7እግዚአብሔርም ይህን ቃል ለኢዮብ ከተናገረ በኋላ እግዚአብሔር ቴማናዊውን ኤልፋዝን፦ እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ ቅንን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና ቍጣዬ በአንተና በሁለቱ ባልንጀሮችህ ላይ ነድዶአል። 8አሁን እንግዲህ ሰባት ወይፈኖችና ሰባት አውራ በጎች ይዛችሁ ወደ ባሪያዬ ወደ ኢዮብ ዘንድ ሂዱ፥ የሚቃጠልንም መሥዋዕት ስለ ራሳችሁ አሳርጉ፥ ባሪያዬም ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል፥ እኔም እንደ ስንፍናችሁ እንዳላደርግባችሁ ፊቱን እቀበላለሁ፥ እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ ቅን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና። 9ቴማናዊውም ኤልፋዝ ሹሐዊውም በልዳዶስ ናዕማታዊውም ሶፋር ሄደው እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው አደረጉ፥ እግዚአብሔርም የኢዮብን ፊት ተቀበለ።
10ኢዮብም ስለ ወዳጆቹ በጸለየ ጊዜ እግዚአብሔርም ምርኮውን መለሰለት፥ እግዚአብሔር ቀድሞ በነበረው ፋንታ ሁለት እጥፍ አድርጎ ለኢዮብ ሰጠው። 11ወንድሞቹና እኅቶቹ ቀድሞም ያውቁት የነበሩት ሁሉ ወደ እርሱ መጡ፥ በቤቱም ከእርሱ ጋር እንጀራ በሉ፥ ስለ እርሱም አዘኑለት፥ እግዚአብሔርም ካመጣበት ክፉ ነገር ሁሉ አጽናኑት፥ እያንዳንዳቸውም ብርና የወርቅ ቀለበት ሰጡት። 12እግዚአብሔርም ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን ለኢዮብ ባረከ፥ አሥራ አራት ሺህም በጎች፥ ስድስት ሺህም ግመሎች፥ አንድ ሺህም ጥማድ በሬዎች፥ አንድ ሺህም እንስት አህዮች ነበሩት። 13ደግሞም ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆች ሆኑለት። 14የመጀመሪያይቱንም ስም ይሚማ፥ የሁለተኛይቱንም ስም ቃስያ፥ የሦስተኛይቱንም ስም አማልቶያስ ቂራስ ብሎ ሰየማቸው። 15እንደ ኢዮብ ሴቶች ልጆችም ያሉ የተዋቡ ሴቶች በአገሩ ሁሉ አልተገኙም፥ አባታቸውም ከወንድሞቻቸው ጋር ርስት ሰጣቸው። 16ከዚህም በኋላ ኢዮብ መቶ አርባ ዓመት ኖረ፥ ልጆቹንና የልጅ ልጆቹንም እስከ አራት ትውልድ ድረስ አየ። 17ኢዮብም ሸምግሎ ዕድሜም ጠግቦ ሞተ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 42: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ