መጽሐፈ ኢዮብ 41
41
1እነሆ፥ ተስፋው ከንቱ ነው፥
ያየው ሁሉ ስንኳ በፊቱ ይዋረዳል።
2ያንቀሳቅሰውም ዘንድ የሚደፍር የለም፥
እንግዲህ በፊቴ መቆም የሚችል ማን ነው?
3እመልስለትስ ዘንድ መጀመሪያ የሰጠኝ ማን ነው?
ከሰማይ ሁሉ በታች ያለው ገንዘቤ ነው።
4ስለ አካላቱና ስለ ብርቱ ኃይሉ፥
ስለ መልካም ሰውነቱ ዝም አልልም።
5የውጪ ልብሱን ማን ይገፋል?
በጥንድ መንጋጋውስ ውስጥ ማን ይገባል?
6የፊቱንስ ደጆች የሚከፍት ማን ነው?
በጥርሶቹ ዙሪያ ግርማ አለ።
7ቅርፊቶቹ ጠንካራ ስለ ሆኑ እርሱ ትዕቢተኛ ነው፥
በጠባብ ማተሚያ እንደ ታተሙ ናቸው።
8እርስ በርሳቸው የተቀራረቡ ናቸውና
ነፋስ በመካከላቸው መግባት አይችልም።
9እርስ በርሳቸው የተገጣጠሙ ናቸው፥
እስከማይለያዩም ድረስ ተያይዘዋል።
10እንጥሽታው ብልጭታ ያወጣል፥
ዓይኖቹም እንደ ወገግታ ናቸው።
11ከአፉ ፋናዎች ይወጣሉ፥
የእሳትም ፍንጣሪ ይረጫል።
12እንደ ፈላ ድስትና እንደሚቃጠል ሸምበቆ
ከአንፍንጫው ጢስ ይወጣል።
13እስትንፋሱ ከሰልን ታቃጥላለች፥
ነበልባልም ከአፉ ይወጣል።
14በአንገቱ ኃይል ታድራለች፥
ግርማ በፊቱ ይዘፍናል።
15የሥጋውም ቅርፊት የተጣበቀ ነው፥
እስከማይንቀሳቀሱም ድረስ በእርሱ ላይ ጸንተዋል።
16ልቡ እንደ ድንጋይ የደነደነ ነው፥
እንደ ወፍጮ ድንጋይ የጸና ነው።
17በተነሣ ጊዜ ኃያላን ይፈራሉ፥
ከድንጋጤም የተነሣ ያብዳሉ።
18ሰይፍና ጦር፥ ፍላጻና መውጊያም ቢያገኙት አያሸንፉትም።
19ብረትን እንደ ገለባ፥
ናስንም እንደ ነቀዝ እንጨት ይቈጥራቸዋል።
20ፍላጻ ሊያባርረው አይችልም፥
የወንጭፍም ድንጋዮች እንደ ገለባ ይሆኑለታል።
21በሎታውን እንደ ገለባ ይቈጥረዋል፥
ሰላጢኑም ሲሰበቅ ይስቃል።
22ታቹ እንደ ስለታም ገል ነው፥
እንደ መዳመጫም በጭቃ ላይ ያልፋል።
23ቀላዩን እንደ ድስት ያፈላዋል፥
ባሕሩንም እንደ ሽቱ ምንቸት ያደርገዋል።
24በስተ ኋላው ብሩህ መንገድን ያበራል፥
ቀላዩም ሽበት ይመስላል።
25ያለ ፍርሃት የተፈጠረ፥
እንደ እርሱ ያለ በምድር ላይ የለም።
26ከፍ ያለውን ሁሉ ይመለከታል፥
በትዕቢተኞችም ሁሉ ላይ ንጉሥ ነው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 41: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ