መጽሐፈ ኢዮብ 40
40
1እግዚአብሔርም መለሰ ኢዮብንም እንዲህ አለው፦
2በውኑ የሚከራከር ሰው ሁሉን ከሚችል አምላክ ጋር ይከራከራልን?
ከእግዚአብሔር ጋር የሚዋቀስ እርሱ ይመልስለት።
3ኢዮብም መለሰ እግዚአብሔርንም እንዲህ አለው፦
4እነሆ፥ እኔ ወራዳ ሰው ነኝ፥ የምመልስልህ ምንድር ነው?
እጄን በአፌ ላይ እጭናለሁ።
5አንድ ጊዜ ተናገርሁ፥ አልመልስምም፥
ሁለተኛ ጊዜም፥ ከእንግዲህ ወዲህ አልናገርም።
6እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰ እንዲህም አለ፦
7እንግዲህ እንደ ወንድ ወገብህን ታጠቅ፥
እጠይቅሃለሁ፥ አንተም ተናገረኝ።
8በውኑ ፍርዴን ታፈርሳለህን?
አንተስ ጻድቅ ትሆን ዘንድ በእኔ ትፈርዳለህን?
9እንደ እግዚአብሔር ክንድ ያለ ክንድ አለህን?
ወይስ እንደ እርሱ ባለ ድምፅ ታንጐደጕዳለህን?
10በታላቅነትና በልዕልና ተላበስ፥
በክብርና በግርማም ተጐናጸፍ።
11የቍጣህን ፈሳሽ አፍስስ፥
ትዕቢተኛውንም ሁሉ ተመልክተህ አዋርደው።
12ትዕቢተኛውንም ሁሉ ተመልከት፥ ዝቅ ዝቅም አድርገው፥
በደለኞችንም ወዲያውኑ እርገጣቸው።
13በአፈር ውስጥ በአንድነት ሰውራቸው፥
በተሸሸገም ስፍራ ፊታቸውን ሸፍን።
14በዚያን ጊዜም ቀኝ እጅህ ታድንህ ዘንድ እንድትችል
እኔ ደግሞ እመሰክርልሃለሁ።
15ከአንተ ጋር የሠራሁትን ጉማሬ፥ እስኪ፥ ተመልከት፥
እንደ በሬ ሣር ይበላል።
16እነሆ፥ ብርታቱ በወገቡ ውስጥ ነው፥
ኃይሉም በሆዱ ጅማት ውስጥ ነው።
17ጅራቱን እንደ ጥድ ዛፍ ያወዛውዛል፥
የወርቹ ጅማት የተጐነጐነ ነው።
18አጥንቱ እንደ ናስ አገዳ ነው፥
አካላቱ እንደ ብረት ዘንጎች ናቸው።
19እርሱ የእግዚአብሔር ፍጥረት አውራ ነው፥
ሠሪውም ሰይፉን ሰጠው።
20የሜዳ እንስሶች ሁሉ የሚጫወቱበት ተራራ
ምግብን ያበቅልለታል።
21ጥላ ካለው ዛፍ በታች፥
በደንገልና በረግረግ ውስጥ ይተኛል።
22ጥላ ያለው ዛፍ በጥላው ይሰውረዋል፥
የወንዝ አኻያ ዛፎች ይከብቡታል።
23እነሆ፥ ወንዙ ቢጐርፍ አይደነግጥም፥
ዮርዳኖስም እስከ አፉ ድረስ ቢፈስስ እርሱ ይተማመናል።
24ዓይኖቹ እያዩ ይያዛልን?
አፍንጫውስ በወጥመድ ይበሳልን?
25በውኑ አዞውን በመቃጥን ታወጣለህን?
ምላሱንስ በገመድ ታስረዋለህን?
26ወይስ ስናጋ በአፍንጫው ታደርጋለህን?
ወይስ በችንካር ጕንጩን ትበሳለህን?
27በውኑ ወደ አንተ እጅግ ይለምናልን?
በጣፈጠስ ቃል ይናገርሃልን?
28በውኑ ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን ይገባልን?
ወይስ ለዘላለም ባሪያ ታደርገዋለህን?
29ከወፍ ጋር እንደምትጫወት ከእርሱ ጋር ትጫወታለህን?
ወይስ ለሴት ባሪያዎችህ ታስረዋለህን?
30አጥማጆች በእርሱ ይከራከራሉን?
ወይስ ነጋዴዎች ያካፍሉታልን?
31በውኑ ቁርበቱን በጭሬ፥
ራሱንስ በዓሣ ጦር ትሞላዋለህን?
32እጅህን በላዩ ጫን፥
ሰልፉን አስብ፥ እንግዲህም አትድገም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 40: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ