የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢዮብ 39

39
1የበረሃ ፍየል የምትወልድበትን ጊዜ ታውቃለህን?
ዋላይቱስ የምታምጥበትን ጊዜ ትመለከታለህን?
2እርስዋ የምትፈጽመውንስ ወራት ትቈጥራለህን?
የምትወልድበትንስ ጊዜ ታውቃለህን?
3ይንበረከካሉ፥ ልጆቻቸውንም ይወልዳሉ፥
ከምጣቸውም ያርፋሉ።
4ልጆቻቸው ይጠነክራሉ፥
በሜዳም ያድጋሉ፥
ይወጣሉ፥ ወደ እነርሱም አይመለሱም።
5የሜዳውስ አህያ አርነት ማን አወጣው?
የበረሃውንስ አህያ ከእስራቱ ማን ፈታው?
6በረሃውን ለእርሱ ቤት አድርጌ ሰጠሁት፥
መኖሪያውም በጨው ምድር ነው።
7በከተማ ውካታ ይዘብታል፥
የነጂውን ጩኸት አይሰማም።
8ተራራውን እንደ መሰምርያው ይመለከተዋል፥
ለምለሙንም ሁሉ ይፈልጋል።
9ጐሽ ያገለግልህ ዘንድ ይታዘዛልን?
ወይስ በግርግምህ አጠገብ ያድራልን?
10ጐሽ ይተልምልህ ዘንድ ትጠምደዋለህን?
ወይስ ከአንተ በኋላ በእርሻ ላይ ይጐለጕላልን?
11ጕልበቱስ ብርቱ ስለ ሆነ ትታመነዋለህን?
ተግባርህንስ ለእርሱ ትተዋለህን?
12ዘርህንስ ይመልስልህ ዘንድ፥
በአውድማህስ ያከማችልህ ዘንድ ትታመነዋለህን?
13የሰጐን ክንፍ በደስታ ይንቀሳቀሳል፥
ነገር ግን ክንፉና ላባው ጭምተኛ ነውን?
14እንቍላልዋን በመሬት ላይ ትተዋለች፥
በአፈርም ውስጥ ታሞቀዋለች፥
15እግር ይሰብረው ዘንድ፥
የምድረ በዳም አውሬ ይረግጠው ዘንድ ትረሳለች።
16የእርስዋ እንዳልሆኑ በልጆችዋ ትጨክናለች፥
በከንቱም ብትሠራ አትፈራም፥
17እግዚአብሔር ጥበብን ከእርስዋ ከልክሎአልና፥
ማስተዋልንም አልሰጣትምና።
18ወደ ላይ ከፍ ከፍ ስትል
በፈረስና በፈረሰኛው ትሳለቃለች።
19ለፈረስ ጕልበቱን ሰጥተኸዋልን?
አንገቱንስ ጋማ አልብሰኸዋልን?
20እንደ አንበጣስ አፈናጠርኸውን?
የማንኰራፋቱ ክብር የሚያስፈራ ነው።
21በኮቴው በሸለቆው ውስጥ ይጐደፍራል፥
በጉልበቱም ደስ ይለዋል፥
ሰይፍም የታጠቁትን ለመገናኘት ይወጣል።
22በፍርሃት ላይ ይስቃል፥
እርሱም አይደነግጥም፥
ከሰይፍም ፊት አይመለስም።
23በእርሱ ላይ የፍላጻ ኮረጆና ብልጭልጭ የሚል ጦር
ሰላጢንም ያንኳኳሉ።
24በጭካኔና በቍጣ መሬትን ይውጣል፥
የመለከትም ድምፅ ቢሰማ አይቆምም።
25የመለከትም ድምፅ ሲሰማ፦ እሰይ! ይላል፥
ከሩቅ ሆኖ ሰልፍንና የአለቆቹን ጩኸት፥
የሠራዊቱንም ውካታ ያሸታል።
26በውኑ ከጥበብህ የተነሣ ጭልፊት ያንዣብባልን?
ወይስ ክንፎቹን ወደ ደቡብ ይዘረጋልን?
27በአፍህ ትእዛዝ ንስር ከፍ ከፍ ይላልን?
ቤቱንስ በአርያም ላይ ያደርጋልን?
28በገደል ላይ ይኖራል፥
በገደሉ ገመገምና በጥጉ ያድራል።
29በዚያም ሆኖ የሚነጥቀውን ይጐበኛል፥
ዓይኑም በሩቅ ትመለከታለች።
30ጫጩቶቹም ደም ይጠጣሉ፥
በድን ባለባትም ስፍራ እርሱ በዚያ አለ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ