መጽሐፈ መክብብ 1
1
1በኢየሩሳሌም የነገሠ የሰባኪው የዳዊት ልጅ ቃል።
2ሰባኪው፦ ከንቱ፥ ከንቱ፥ የከንቱ ከንቱ፥ ሁሉ ከንቱ ነው ይላል። 3ከፀሐይ በታች በሚደክምበት ድካም ሁሉ የሰው ትርፉ ምንድር ነው? 4ትውልድ ይሄዳል፥ ትውልድም ይመጣል፥ ምድር ግን ለዘላለም ነው። 5ፀሐይ ትወጣለች፥ ፀሐይም ትገባለች፥ ወደምትወጣበትም ስፍራ ትቸኵላለች። 6ነፋስ ወደ ደቡብ ይሄዳል፥ ወደ ሰሜንም ይዞራል፥ ዘወትር በዙረቱ ይዞራል፥ ነፋስም በዙረቱ ደግሞ ይመለሳል። 7ፈሳሾች ሁሉ ወደ ባሕር ይሄዳሉ፥ ባሕሩ ግን አይሞላም፥ ፈሳሾች ወደሚሄዱበት ስፍራ እንደ ገና ወደዚያ ይመለሳሉ። 8ነገር ሁሉ ያደክማል፥ ሰው ይናገረው ዘንድ አይችልም፥ ዓይን ከማየት አይጠግብም፥ ጆሮም ከመስማት አይሞላም።
9የሆነው ነገር እርሱ የሚሆን ነው፥ የተደረገውም ነገር እርሱ የሚደረግ ነው፥ ከፀሐይም በታች አዲስ ነገር የለም። 10ማንም፦ እነሆ፥ ይህ ነገር አዲስ ነው ይል ዘንድ ይችላልን? እርሱ ከእኛ በፊት በነበሩት ዘመናት ተደርጎአል። 11ለፊተኞቹም ነገሮች መታሰቢያ የላቸውም፥ ለኋለኖቹም ነገሮች ከእነርሱ በኋላ በሚነሡት ሰዎች ዘንድ መታሰቢያ አይገኝላቸውም።
12እኔ ሰባኪው በእስራኤል ላይ በኢየሩሳሌም ንጉሥ ነበርሁ። 13ከሰማይም በታች የተደረገውን ሁሉ በጥበብ እፈልግና እመረምር ዘንድ ልቤን አተጋሁ፥ እግዚአብሔር ይደክሙባት ዘንድ ይህችን ለሰው ልጆች የሰጠ ክፉ ጥረት ናት። 14ከፀሐይ በታች የተሠራውን ሥራ ሁሉ አየሁ፥ እነሆም፥ ሁሉ ከንቱ ነው፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። 15ጠማማ ይቀና ዘንድ አይችልም፥ ጐደሎም ይቈጠር ዘንድ አይችልም።
16እኔ በልቤ፦ እነሆ፥ ከእኔ አስቀድመው በኢየሩሳሌም ላይ ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ጥበብን አብዝቼ ጨመርሁ፥ ልቤም ብዙ ጥበብንና እውቀትን ተመለከተ ብዬ ተናገርሁ። 17ጥበብንና ዕብደትን ሞኝነትንም አውቅ ዘንድ ልቤን ሰጠሁ፥ ይህም ደግሞ ነፋስን እንደ መከተል እንደ ሆነ አስተዋልሁ። 18በጥበብ መብዛት ትካዜ ይበዛልና፥ እውቀትንም የሚጨምር ኀዘንን ይጨምራልና።
Currently Selected:
መጽሐፈ መክብብ 1: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ