ኢዮብ 42:1-8
ኢዮብ 42:1-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኢዮብም መለሰ፥ እግዚአብሔርንም እንዲህ አለው፦ “ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደ ሆንህ፥ የሚሳንህም እንደሌለ ዐወቅሁ። ምክርን ከአንተ የሚሰውር፥ ቃሉንም ከአንተ የሚሸልግና የሚሸሽግ የሚመስለው ማን ነው? የማላስተውለውንና የማላውቀውንም ታላቅና ድንቅ ነገር የሚነግረኝ ማን ነው? “ጌታ ሆይ፥ እባክህ፥ ስማኝ፥ እኔም ልናገር፤ እጠይቅህማለሁ፥ አንተም አስተምረኝ። መስማትንስ ስለ አንተ ቀድሞ በጆሮዬ ሰምቼ ነበር፤ አሁን ግን ዐይኔ አየችህ፤ ስለዚህ ራሴን እንቃለሁ፤ ሰውነቴም ቀለጠ። እኔ አፈርና አመድ እንደ ሆንሁ አውቃለሁ።” እግዚአብሔርም ይህን ቃል ለኢዮብ ከተናገረ በኋላ እግዚአብሔር ቴማናዊውን ኤልፋዝን እንዲህ አለው፥ “እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ አንዲት ቅን ነገርን በፊቴ አልተናገራችሁምና አንተና ሁለቱ ባልንጀሮችህ በድላችኋል። አሁን እንግዲህ ሰባት ወይፈኖችንና ሰባት አውራ በጎችን ይዛችሁ ወደ ባሪያዬ ወደ ኢዮብ ዘንድ ሂዱ፥ እርሱም የሚቃጠልን መሥዋዕት ስለ ራሳችሁ ያሳርግላችሁ። ባሪያዬም ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልይ፥ እኔም ፊቱን እቀበላለሁ። ስለ እርሱ ባይሆን ባጠፋኋችሁ ነበር። በባሪያዬ በኢዮብ ላይ ቅን ነገርን በፊቴ አልተናገራችሁምና።”
ኢዮብ 42:1-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢዮብም እንዲህ ሲል ለእግዚአብሔር መለሰ፤ “አንተ ሁሉን ማድረግ እንደምትችል፣ ዕቅድህም ከቶ እንደማይሰናከል ዐወቅሁ። አንተ፣ ‘ያለ ዕውቀት ዕቅዴን የሚያደበዝዝ ይህ ማን ነው?’ አልኸኝ፤ በርግጥ ያልገባኝን ነገር፣ የማላውቀውንና ላስተውለው የማልችለውን ጕዳይ ተናገርሁ። “ ‘ስማኝ፣ ልናገር እኔ እጠይቃለሁ፤ አንተ ትመልስልኛለህ’ አልኸኝ። ጆሮዬ ስለ አንተ ሰምታ ነበር፤ አሁን ግን ዐይኔ አየችህ። ስለዚህ ራሴን እንቃለሁ፤ በትቢያና በዐመድ ላይ ተቀምጬ ንስሓ እገባለሁ።” እግዚአብሔር ይህን ለኢዮብ ከተናገረ በኋላ፣ ቴማናዊውን ኤልፋዝን እንዲህ አለው፤ “እንደ አገልጋዬ እንደ ኢዮብ ስለ እኔ ቅን ነገር ስላልተናገራችሁ፣ ቍጣዬ በአንተና በሁለቱ ባልንጀሮችህ ላይ ነድዷል። አሁን እንግዲህ ሰባት ወይፈኖችና ሰባት አውራ በጎች ይዛችሁ ወደ አገልጋዬ ወደ ኢዮብ ሂዱ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትም ስለ ራሳችሁ አቅርቡ። እንደ አሳፋሪ ተግባራችሁ እንዳላደርግባችሁ አገልጋዬ ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል፤ እኔም ጸሎቱን እቀበላለሁ፤ እንደ አገልጋዬ እንደ ኢዮብ ስለ እኔ ቅን ነገር አልተናገራችሁምና።”
ኢዮብ 42:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢዮብም መለሰ እግዚአብሔርንም እንዲህ አለው፦ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደ ሆንህ፥ አሳብህም ይከለከል ዘንድ ከቶ እንደማይቻል አወቅሁ። ያለ እውቀት ምክርን የሚሰውር ማን ነው? ስለዚህ እኔ የማላስተውለውን፥ የማላውቀውንም ድንቅ ነገር ተናግሬአለሁ። እባክህ፥ ስማኝ፥ እኔም ልናገር፥ እጠይቅህማለሁ፥ አንተም ተናገረኝ። መስማትንስ በጆሮ በመስማት ሰምቼ ነበር፥ አሁን ግን ዓይኔ አየችህ፥ ስለዚህ ራሴን እንቃለሁ፥ በአፈርና በአመድ ላይ ተቀምጬ እጸጸታለሁ። እግዚአብሔርም ይህን ቃል ለኢዮብ ከተናገረ በኋላ እግዚአብሔር ቴማናዊውን ኤልፋዝን፦ እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ ቅንን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና ቍጣዬ በአንተና በሁለቱ ባልንጀሮችህ ላይ ነድዶአል። አሁን እንግዲህ ሰባት ወይፈኖችና ሰባት አውራ በጎች ይዛችሁ ወደ ባሪያዬ ወደ ኢዮብ ዘንድ ሂዱ፥ የሚቃጠልንም መሥዋዕት ስለ ራሳችሁ አሳርጉ፥ ባሪያዬም ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል፥ እኔም እንደ ስንፍናችሁ እንዳላደርግባችሁ ፊቱን እቀበላለሁ፥ እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ ቅን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና።
ኢዮብ 42:1-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ ኢዮብ ለእግዚአብሔር እንዲህ ሲል መለሰ፦ “አምላክ ሆይ! አንተ ሁሉን ነገር ማድረግ እንደምትችል ዐውቃለሁ፤ የአንተንም ዕቅድ ማሰናከል የሚችል የለም። እኔ የማውቀው በጣም ትንሽ ሆኖ ሳለ ብዙ የምናገረው ለምን እንደ ሆነ ጠይቀሃል። በእርግጥ እኔ ስለማላውቃቸውና እጅግ ድንቅ ስለ ሆነ ነገር ተናግሬአለሁ። ‘አድምጥና ለጥያቄዬ መልስ ስጥ’ ብለኸኛል፤ እኔ እስከ አሁን ስለ አንተ የማውቀው፥ ሰዎች የነገሩኝን በመስማት ብቻ ነበር፤ አሁን ግን በዐይኖቼ አየሁህ። ከዚህም የተነሣ የተናገርኩት ነገር ስላሳፈረኝ በዐመድና በትቢያ ላይ ተቀምጬ ንስሓ እገባለሁ።” እግዚአብሔር ከኢዮብ ጋር እነዚህን ነገሮች ከተነጋገረ በኋላ ቴማናዊውን ኤሊፋዝን እንዲህ አለው፦ “እናንተ ስለ እኔ እንደ አገልጋዬ እንደ ኢዮብ ትክክለኛውን ነገር ስላልተናገራችሁ እኔ በአንተና በሁለቱ ጓደኞችህ ላይ ተቈጥቼአለሁ። ስለዚህ አሁን ሰባት ኰርማዎችንና ሰባት አውራ በጎችን ይዛችሁ ወደ አገልጋዬ ወደ ኢዮብ ሂዱ፤ እዚያም ስለ ራሳችሁ ኃጢአት የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ፤ አገልጋዬ ኢዮብ ይጸልይላችኋል፤ እኔም ጸሎቱን ሰምቼ በበደላችሁ መጠን አልቀጣችሁም፤ እናንተ እንደ ኢዮብ ስለ እኔ ትክክል የሆነውን ነገር አልተናገራችሁም።”
ኢዮብ 42:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢዮብም መለሰ፤ ጌታንም እንዲህ አለው፦ “ሁሉንም ማድረግ እንድምትችል፥ ሐሳብህም ሊከለከል ከቶ እንደማይቻል አወቅሁ። ያለ እውቀት ምክርን የሚሰውር ማን ነው? ስለዚህ እኔ የማላስተውለውን፥ የማላውቀውንም ድንቅ ነገር ተናግሬአለሁ። እባክህ፥ ስማኝ፥ እኔም ልናገር፥ እጠይቅህማለሁ፥ አንተም አሳውቀኝ። መስማትንስ በጆሮ በመስማት ሰምቼ ነበር፥ አሁን ግን ዓይኔ አየችህ፥ ስለዚህ ራሴን እንቃለሁ፥ በአፈርና በአመድ ላይ ተቀምጬ እጸጸታለሁ።” ጌታም ይህንን ለኢዮብ ከተናገረ በኋላ፥ ቴማናዊውን ኤልፋዝን እንዲህ አለው፦ “እንደ አገልጋዬ እንደ ኢዮብ ቅንን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና ቁጣዬ በአንተና በሁለቱ ባልንጀሮችህ ላይ ነድዶአል። አሁን እንግዲህ ሰባት ወይፈኖችና ሰባት አውራ በጎች ይዛችሁ ወደ አገልጋዬ ወደ ኢዮብ ሂዱ፥ የሚቃጠልንም መሥዋዕት ስለ ራሳችሁ አሳርጉ፥ አገልጋዬም ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል፥ እኔም እንደ ጥፋታችሁ እንዳላደርግባችሁ ጸሎቱን እሰማለሁ፥ እንደ አገልጋዬ እንደ ኢዮብ ቅን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና።”