ኢዮብ 22:21-27
ኢዮብ 22:21-27 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ለእግዚአብሔር ተገዛ፤ ከእርሱም ጋር ሰላም ይኑርህ፤ በረከትም ታገኛለህ። ምክርን ከአፉ ተቀበል፤ ቃሉንም በልብህ አኑር። ሁሉን ወደሚችል አምላክ ብትመለስ ትጠገናለህ፤ ክፋትን ከድንኳንህ ብታርቅ፣ የወርቅህን አንኳር ትቢያ ላይ፣ የኦፊር ወርቅህንም ጥልቅ ሸለቆ ውስጥ ብትጥለው፣ ሁሉን ቻዩ አምላክ ወርቅ ይሆንልሃል፤ ምርጥ ብር ይሆንልሃል። በዚያ ጊዜ ሁሉን በሚችል አምላክ ደስ ይልሃል፤ ፊትህንም ወደ እግዚአብሔር ታቀናለህ። ወደ እርሱ ትጸልያለህ፤ እርሱም ይሰማሃል፤ አንተም ስእለትህን ትሰጣለህ።
ኢዮብ 22:21-27 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አሁንም ከእርሱ ጋር ተስማማ፥ ሰላምም ይኑርህ፥ በዚያም በጎነት ታገኛለህ። ከአፉም ሕጉን ተቀበል፥ በልብህም ቃሉን አኑር፥ ሁሉን ወደሚችል አምላክ ብትመለስ፥ ብትዋረድም፥ ኃጢአትንም ከድንኳንህ ብታርቅ፥ የወርቅን ዕቃ በአፈር ውስጥ፥ የኦፊርንም ወርቅ በጅረት ድንጋይ መካከል ብትጥል፥ ሁሉን የሚችል አምላክ ወርቅና የሚብለጨለጭ ብር ይሆንልሃል። የዚያን ጊዜ ሁሉን በሚችል አምላክ ደስ ይልሃል፥ ፊትህንም ወደ እግዚአብሔር ታነሣለህ። ወደ እርሱም ትጸልያለህ፥ እርሱም ይሰማሃል፥ ስእለትህንም ትሰጣለህ።
ኢዮብ 22:21-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ስለዚህ ኢዮብ ሆይ፥ ራስህን ለእግዚአብሔር አስገዛ፤ ከእርሱም ጋር ሰላም ይኑርህ፤ ይህን ብታደርግ መልካም ነገርን ታገኛለህ። እግዚአብሔር የሚሰጥህን ትምህርት ተቀበል፤ ቃሉንም በልብህ አኑር። ራስህን ሁሉን ወደሚችል አምላክ ብትመልስ እንደ ቀድሞህ ትሆናለህ። ከቤትህ የክፋትን ሥራ አስወግድ ወርቅን ወደ ትቢያ ጣለው፤ የኦፊርንም ወርቅ እንደ ጅረት ድንጋይ ወርውረው፤ በዚያን ጊዜ ሁሉን ቻይ አምላክ ለአንተ ወርቅና ንጹሕ ብር ይሆንልሃል። በዚያን ጊዜ ሁሉን በሚችል አምላክ ደስ ይልሃል፤ በእርሱም ተማምነህ ትኖራለህ። ወደ እርሱም በምትጸልይበት ጊዜ የለመንከውን ሁሉ ስለሚፈጽምልህ፥ ስለትህን ትከፍላለህ።
ኢዮብ 22:21-27 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“አሁንም መታገሥ ትችል እንደ ሆነ፥ ፍሬህም ይበጅ እንደ ሆነ እስኪ ጽኑ ሁን። ከአፉም ሕጉን ተቀበል፥ በልብህም ቃሉን አኑር፤ ብትመለስ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ራስህን ብታዋርድ፥ ኀጢአትንም ከልብህ ብታርቅ፥ በዓለቱ ቋጥኝ ላይ ለራስህ መዝገብን ታኖራለህ። የሶፎርም ወርቅ እንደ ጅረት ድንጋይ ይሆንልሃል። ሁሉን የሚችል አምላክም ከጠላቶችህ ይረዳሃል። ንጽሕናንም በእሳት እንደ ተፈተነ ብር አድርጎ ይመልስልሃል። በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ታገኛለህ። ወደ ሰማይም በደስታ ትመለከታለህ። ወደ እርሱም ትጸልያለህ፥ እርሱም ይሰማሃል፤ ስእለትህንም ይሰጠሃል።
ኢዮብ 22:21-27 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“እንግዲህ አሁንም ከእርሱ ጋር ተስማማ፥ ሰላምም ይኑርህ፥ በዚያም መልካምን ታገኛለህ። ከአፉም ትምህርቱን ተቀበል፥ በልብህም ቃሉን አኑር፥ ሁሉን ወደሚችል አምላክ ብትመለስ፥ ትደረጃለህ፥ ክፋትንም ከድንኳንህ ብታርቅ፥ ወርቅን በአፈር ውስጥ፥ የኦፊርንም ወርቅ በጅረት ድንጋይ መካከል ብትጥል፥ ሁሉን የሚችል አምላክ ወርቅና የሚብለጨለጭ ብር ይሆንልሃል። የዚያን ጊዜ ሁሉን በሚችል አምላክ ደስ ይልሃል፥ ፊትህንም ወደ እግዚአብሔር ታነሣለህ። ወደ እርሱም ትጸልያለህ፥ እርሱም ይሰማሃል፥ ስእለትህንም ትሰጣለህ።