መጽሐፈ ኢዮብ 22
22
የሦስተኛው ዙር ንግግር
1ቴማናዊውም ኤልፋዝ መለሰ፥ እንዲህም አለ፦
2“በውኑ ማስተዋልንና ዕውቀትን የሚያስተምር፥
እግዚአብሔር አይደለምን?
3አንተ በሥራህ ንጹሕ ከሆንህ እግዚአብሔርን ምን ያገደዋል?#ዕብ. “ጻድቅ መሆንህ ሁሉን ቻይ አምላክን ደስ ያሰኘዋልን” ይላል።
መንገድህንስ ብታቀና ምን ይጠቅመዋል?
4አንተንስ ተቈጣጥሮ ይዘልፍሃልን?
ወደ ፍርድስ ከአንተ ጋር ይገባልን?
5“ክፋትህስ የበዛ አይደለምን?
ኀጢአትህስ ቍጥር የሌለው አይደለምን?
6የወንድሞችህን መያዣ በከንቱ ወስደሃል፥
የታረዘውንም ልብሱን ገፍፈሃል።
7ለተጠማ ውኃ አላጠጣህም፥
የራብተኛውንም ጕርሻ ነጥቀሃል፥
ምድርን የሚዘራ ሰውም በውስጧ ድንበርን ያኖራል።
8ፊታቸውን አይተህ ያደነቅሃቸው አሉ፥
በምድርም ላይ ድሆችን በዐመፅ ጠላህ#ከዕብራይስጥ ልዩነት አለው።
9መበለቶችን ባዶአቸውን ሰድደሃቸዋል፥
ድሃአደጎችንም አስጨንቀሃቸዋል።
10ስለዚህ አሽክላ ከብቦሃል፥
ከባድ ጦርነትም አናውጦሃል።
11ብርሃኑም ጨለማ ሆነብህ፥
ተኝተህም ሳለህ ውኃው አሰጠመህ።
12“ልዑል የወደደውን ያደርግ ዘንድ የሚገባው አይደለምን?#በዕብራይስጥ ልዩነት አለው።
ትዕቢተኞችንስ አያዋርዳቸውምን?
13አንተም እንዲህ ብለሃል፦ ኀያል እርሱ ምን ያውቃል?
በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆኖ ሊፈርድ ይችላልን?
14የጠቈረ ደመና ጋርዶታል አያይምም፤
በሰማይ ክበብ ላይ ይራመዳል።
15በውኑ ጻድቃን#ዕብ. “ኃጥኣን” ይላል። ሰዎች የረገጡአትን
የዱሮይቱን መንገድ ትጠብቃለህን?
16ጊዜያቸው ሳይደርስ ተነጠቁ፤
መሠረታቸውም እንደ ፈሳሽ ውኃ ፈሰሰ።
17እግዚአብሔር ምን ያደርገናል?
ሁሉን የሚችል አምላክስ ምን ያመጣብናል? ይላሉ።
18ነገር ግን ቤታቸውን በመልካም ነገር ሞላ፤
የኃጥኣን ምክር ከእርሱ የራቀች ናት።
19ጻድቃንም አይተው ሳቁ፤
ንጹሓንም በንቀት ይዘባበቱባቸዋል።
20በእውነት ሀብታቸው ጠፋ፥
የቀረውንም እሳት በላች።
21“አሁንም መታገሥ ትችል እንደ ሆነ፥
ፍሬህም ይበጅ እንደ ሆነ እስኪ ጽኑ#ግእዝ “ኩን እኩየ” ይላል። ሁን።
22ከአፉም ሕጉን ተቀበል፥
በልብህም ቃሉን አኑር፤
23ብትመለስ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ራስህን ብታዋርድ፥
ኀጢአትንም ከልብህ ብታርቅ፥
24በዓለቱ ቋጥኝ ላይ ለራስህ መዝገብን ታኖራለህ።
የሶፎርም ወርቅ እንደ ጅረት ድንጋይ ይሆንልሃል።#በዕብራይስጥ ልዩነት አለው።
25ሁሉን የሚችል አምላክም ከጠላቶችህ ይረዳሃል።
ንጽሕናንም በእሳት እንደ ተፈተነ ብር አድርጎ ይመልስልሃል።
26በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ታገኛለህ።
ወደ ሰማይም በደስታ ትመለከታለህ።
27ወደ እርሱም ትጸልያለህ፥ እርሱም ይሰማሃል፤
ስእለትህንም ይሰጠሃል።
28የጽድቅህንም ብድራት ይሰጥሃል።
ብርሃንም በመንገድህ ላይ ይበራል።
29ራስህን ብታዋርድ ሰውም ኰራብኝ ብትል፥
ራሱን የሚያዋርደውን ሰው ያድነዋል።
30ንጹሕን ሰው ያድነዋል፤
በእጅህም ንጽሕና ትድናለህ።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 22: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ