መጽሐፈ ኢዮብ 23
23
1ኢዮብም መለሰ፥ እንዲህም አለ፦
2“ዛሬም ዘለፋዬ ከእጄ እንደ ሆነ ዐወቅሁ።#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. ልዩነት አለው።
እጁንም በእኔ ላይ አከበደ፥ አስለቀሰኝም።
3እርሱን ወዴት እንደማገኘው ምነው ባወቅሁ!
ወደ ነገሩ ፍጻሜም ምነው በደረስሁ!
4የሠራሁት ቢኖር ይነግረኝ ነበረ፥
ስከራከርም አፌ ዝም አይልም ነበር።
5የሚሰጠኝንም ፈውስ#ዕብ. “የሚመልስልኝን ቃል” ይላል። አውቅ ነበር፥
የሚለኝንም አስተውል ነበር።
6በኀይሉ ብዛት ቢመጣብኝም እንኳ
በቍጣው አያስፈራራኝም ነበር።
7እውነትና ቅንነት ከእርሱ ዘንድ ናቸውና።
ከፍርዴም ለዘለዓለም ያሳርፈኝ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ፍርዴን ያመጣዋል” ይላል። ነበር።
8እነሆ፥ ወደ ፊት እሄዳለሁ፥ እንግዲህም አልኖርም፤
ስለ ፍጻሜውም አላውቅም፤
9ወደሚሠራበትም ወደ ግራ ብሄድ አልመለከተውም፤
ቀኝ እጁ ይከብበኛል፤ ነገር ግን አላየውም።
10መንገዴን ፈጽሞ ዐወቀ፥
እንደ ወርቅም ፈተነኝ
11እንደ ትእዛዙ እወጣለሁ፥
መንገዱንም ጠብቄአለሁ፥ ፈቀቅም አላልሁም።
12ከትእዛዙም አላለፍሁም፤
ቃሉን በልቤ ሰውሬአለሁ።
13“ስለ ፍርድ የሚከራከር ማን ነው?
እርሱ የወደደውን ያደርጋልና።
14ስለዚህም እኔ ስለ እርሱ ቸኰልሁ፤
በተገሠጽሁም ጊዜ አሰብሁት።
15ስለዚህ በፊቱ ደነገጥሁ፤
አስበዋለሁ፤ ከእርሱም የተነሣ እፈራለሁ።
16እግዚአብሔር ግን ልቤን አቀለጠው፥
ሁሉን የሚችል አምላክም አስጨንቆኛል።
17ጨለማም እንደሚመጣብኝ፥
ድቅድቁም ጨለማ ፊቴን እንደሚከድን አላወቅሁም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 23: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ