ዮሐንስ 21:15-22
ዮሐንስ 21:15-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በልተው ካበቁ በኋላ፣ ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን፣ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፤ ከእነዚህ አብልጠህ ትወድደኛለህን?” አለው። እርሱም፣ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤ እንደምወድድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም፣ “ጠቦቶቼን መግብ” አለው። ኢየሱስም ለሁለተኛ ጊዜ፣ “የዮና ልጅ፣ ስምዖን ሆይ፤ በእውነት ትወድደኛለህን?” አለው። እርሱም፣ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤ እንደምወድድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም፣ “በጎቼን ጠብቅ” አለው። ሦስተኛም ጊዜ፣ “የዮና ልጅ፣ ስምዖን ሆይ፤ ትወድደኛለህን?” አለው። ጴጥሮስም ሦስተኛ ጊዜ ኢየሱስ፣ “ትወድደኛለህን?” ብሎ ስለ ጠየቀው ዐዝኖ፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንደምወድድህም ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “በጎቼን መግብ። እውነት እልሃለሁ፤ ወጣት ሳለህ ልብስህን ራስህ ለብሰህ ወደ ፈለግህበት ትሄድ ነበር፤ ስትሸመግል ግን እጅህን ትዘረጋለህ፤ ሌላም ሰው ልብስህን አስታጥቆህ ልትሄድ ወደማትፈልግበት ይወስድሃል።” ኢየሱስ ይህን ያለው ጴጥሮስ በምን ዐይነት ሞት እግዚአብሔርን እንደሚያከብረው ለማመልከት ነው። ከዚህ በኋላም፣ “ተከተለኝ” አለው። ጴጥሮስ ወደ ኋላው ዘወር ሲል፣ ኢየሱስ ይወድደው የነበረ ደቀ መዝሙር ሲከተላቸው አየ፤ ይህም ደቀ መዝሙር ያን ጊዜ እራት ሲበሉ ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ፣ “ጌታ ሆይ፤ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ያለው ነበር። ጴጥሮስም ባየው ጊዜ፣ “ጌታ ሆይ፤ እርሱስ?” ብሎ ጠየቀ። ኢየሱስም፣ “እስክመለስ ድረስ በሕይወት እንዲኖር ብፈልግ እንኳ አንተን ምን ቸገረህ? አንተ ራስህ ተከተለኝ” አለው።
ዮሐንስ 21:15-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ምሳም ከበሉ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ፦ ስምዖን ጴጥሮስን፥ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን?” አለው፤ እርሱም፥ “አዎን፥ ጌታዬ ሆይ፥ እኔ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “በጎችን ጠብቅ” አለው። ዳግመኛም፥ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን?” አለው፤ እርሱም፥ “አዎን፥ ጌታዬ ሆይ፥ እኔ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው፤ “ጠቦቶችን አሰማራ” አለው። ሦስተኛ ጊዜም፥ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን?” አለው፤ ጴጥሮስም ሦስት ጊዜ ትወደኛለህን? ስላለው ተከዘ፤ “ጌታዬ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እኔም እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው፤ “እንኪያስ ግልገሎችን ጠብቅ” አለው። “እውነት እውነት እልሃለሁ፤ አንተ ጐልማሳ ሳለህ በገዛ እጅህ ወገብህን ታጥቀህ ወደ ወደድኸው ትሄድ ነበር፤ በሸመገልህ ጊዜ ግን እጆችህን ትዘረጋለህ፤ ወገብህንም ሌላ ያስታጥቅሃል፤ ወደማትወደውም ይወስድሃል።” በምን ሞት እግዚአብሔርን ያከብር ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት ይህን ተናገረ፤ ይህንም ብሎ ተከተለኝ አለው። ጴጥሮስም መለስ ብሎ ጌታችን ኢየሱስ ይወደው የነበረውን ያን ደቀ መዝሙር ሲከተለው አየ፤ እርሱም ራት ሲበሉ በጌታችን በኢየሱስ አጠገብ የነበረውና “ጌታ ሆይ፥ አሳልፎ የሚሰጥህ ማነው?” ያለው ነው። ጴጥሮስም እርሱን አይቶ፥ “ጌታ ሆይ፥ ይህስ እንዴት ይሆናል?” አለው። ጌታችን ኢየሱስም፥ “እስክመጣ ይኖር ዘንድ ብወድድስ አንተን ምን አግዶህ፤ አንተ ግን ተከተለኝ” አለው።
ዮሐንስ 21:15-22 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ምሳ ከበሉ በኋላም ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን፦ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን?” አለው። “አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። “ግልገሎቼን አሰማራ” አለው። ደግሞ ሁለተኛ፦ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን?” አለው። “አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። “ጠቦቶቼን ጠብቅ” አለው። ሦስተኛ ጊዜ፦ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን?” አለው። ሦስተኛ፦ “ትወደኛለህን?” ስላለው ጴጥሮስ አዘነና፦ “ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም፦ “በጎቼን አሰማራ። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ አንተ ጕልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ፥ ሌላውም ያስታጥቅሃል ወደማትወደውም ይወስድሃል” አለው። በምን ዓይነት ሞት እግዚአብሔርን ያከብር ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት ይህን አለ። ይህንም ብሎ፦ “ተከተለኝ” አለው። ጴጥሮስም ዘወር ብሎ ኢየሱስ ይወደው የነበረውን ደቀ መዝሙር ሲከተለው አየ፤ እርሱም ደግሞ በእራት ጊዜ በደረቱ ተጠግቶ፦ “ጌታ ሆይ፥ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ያለው ነበረ። ጴጥሮስም ይህን አይቶ ኢየሱስን፦ “ጌታ ሆይ፥ ይህስ እንዴት ይሆናል?” አለው። ሲየሱስም፦ “እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ፥ ምን አግዶህ? አንተ ተከተለኝ” አለው።
ዮሐንስ 21:15-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ቊርስ ከበሉ በኋላ ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን፥ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! እነዚህ ከሚወዱኝ ይበልጥ ትወደኛለህን?” አለው። እርሱም “አዎ፥ ጌታዬ ሆይ! እኔ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም “ግልገሎቼን መግብ” አለው። ሁለተኛ ጊዜም “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! ትወደኛለህን?” አለው። እርሱም “አዎ፥ ጌታዬ ሆይ! እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም “ጠቦቶቼን ጠብቅ” አለው። ሦስተኛ ጊዜም “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! ትወደኛለህን?” አለው። ሦስተኛ ጊዜ “ትወደኛለህን?” ስላለው ጴጥሮስ አዘነና “ጌታ ሆይ! አንተ ሁሉን ታውቃለህ፥ እኔ እንደምወድህም ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “በጎቼን አሰማራ፤ እውነት፥ እውነት እልሃለሁ፤ አንተ ጐልማሳ ሳለህ ቀበቶህን በገዛ እጅህ ታጥቀህ ወደ ፈለግኽበት ትሄድ ነበር፤ በሸመገልክ ጊዜ ግን አንተ እጆችህን ትዘረጋና ሌላ ሰው ያስታጥቅሃል፤ ወደማትፈልግበትም ይወስድሃል።” ይህንንም ያለው ጴጥሮስ በምን ዐይነት ሞት እግዚአብሔርን ማክበር እንዳለበት ሲያመለክት ነው፤ ከዚህ በኋላ ጴጥሮስን “ተከተለኝ!” አለው። ጴጥሮስ ዘወር ብሎ ኢየሱስ የሚወድደው ደቀ መዝሙር ሲከተለው አየ፤ ይህ ደቀ መዝሙር በእራት ጊዜ ወደ ኢየሱስ ተጠግቶ፥ “ጌታ ሆይ፥ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ብሎ የጠየቀው ነው። ጴጥሮስ እርሱን አየና “ጌታ ሆይ! ይህስ ሰው ምን ይሆናል?” ሲል ኢየሱስን ጠየቀ። ኢየሱስም “እኔ እስክመጣ ድረስ እንዲኖር ብፈቅድ አንተን ምን አገባህ? አንተ ተከተለኝ!” አለው።
ዮሐንስ 21:15-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከበሉ በኋላም ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! ከእነዚህ ይበልጥ ትወደኛለህን?” አለው። “አዎን ጌታ ሆይ! እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ፤” አለው። ኢየሱስም “ግልገሎቼን አሰማራ፤” አለው። ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! ትወደኛለህን?” አለው። “አዎን ጌታ ሆይ! እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም “ጠቦቶቼን ጠብቅ፤” አለው። ለሦስተኛ ጊዜም “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! ትወደኛለህን?” አለው። ለሦስተኛ ጊዜ “ትወደኛለህን?” ስላለው ጴጥሮስ አዘነና “ጌታ ሆይ! አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም “በጎቼን አሰማራ። እውነት እውነት እልሃለሁ፤ አንተ ጎልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ቦታ ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ፤ ሌላ ሰውም ያስታጥቅሃል፤ ወደማትወደውም ይወስድሃል” አለው። በምን ዓይነት ሞት እግዚአብሔርን እንደሚያከብር ሲያመለክት ይህንን ተናገረ። ከዚያም “ተከተለኝ፤” አለው። ጴጥሮስም ዘወር ሲል ኢየሱስ ይወደው የነበረውን ደቀመዝሙር ከበስተኋላው አየ፤ እርሱም በእራት ጊዜ ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ “ጌታ ሆይ! አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ያለው ነበረ። ጴጥሮስም እርሱን አይቶ ኢየሱስን “ጌታ ሆይ! እርሱስ እንዴት ይሆናል?” አለው። ኢየሱስም “እስክመጣ ድረስ እንዲኖር ብፈቅድስ፥ ምን ግድ አለህ? አንተ ተከተለኝ” አለው።