የዮሐንስ ወንጌል 21
21
ኢየሱስ በጥብርያዶስ ለደቀ መዛሙርቱ እንደ ተገለጠ
1ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በጥብርያዶስ ባሕር አጠገብ ለደቀ መዛሙርቱ እንደገና ተገለጠላቸው፤ እንዲህም ተገለጠ። 2ስምዖን ጴጥሮስና ዲዲሞስ የሚባለው ቶማስ፥ ከገሊላ ቃና የሆነው ናትናኤልም፥ የዘብዴዎስ ልጆችና ከደቀ መዛሙርቱም ሌሎች ሁለት በአንድነት ነበሩ። 3#ሉቃ. 5፥5።ስምዖን ጴጥሮስ “ዓሣ ላጠምድ እሄዳለሁ” አላቸው። እነርሱም “እኛም ከአንተ ጋር እንመጣለን” አሉት። ወጥተውም ወደ ታንኳይቱ ገቡ፤ ነገር ግን በዚያች ሌሊት ምንም አላጠመዱም።
4በነጋም ጊዜ ኢየሱስ በባሕር ዳር ቆመ፤ ደቀመዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም። 5ኢየሱስም “ልጆች ሆይ! አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?” አላቸው። “የለንም” ብለው መለሱለት። 6#ሉቃ. 5፥6።እርሱም “መረቡን በታንኳዪቱ በስተ ቀኝ ጣሉትና ታገኛላችሁ” አላቸው። ስለዚህም ጣሉት፤ በዚህም ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ መረቡን መጎተት አቃታቸው። 7ኢየሱስ ይወደው የነበረውም ደቀመዝሙር ጴጥሮስን “ጌታ እኮ ነው” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም ጌታ መሆኑን በሰማ ጊዜ ዕራቁቱን ነበረና ልብሱን ታጥቆ ወደ ባሕር ዘለለ። 8ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ግን ከምድር የራቁት ሁለት መቶ ክንድ ያህል ብቻ ስለ ነበር ዓሣ የሞላውን መረብ እየሳቡ በጀልባ መጡ።
9ወደ የብስ በወጡ ጊዜ ዓሣ በላዩ የተቀመጠበት ፍምና እንጀራ አዩ። 10ኢየሱስም “አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ አምጡ” አላቸው። 11ስምዖን ጴጥሮስም ወደ ጀልባይቱ ገብቶ መቶ አምሳ ሦስት ታላላቅ ዓሦች ሞልቶ የነበረውን መረብ ወደ ምድር ጐተተ፤ ይህንንም ያህል ብዙ ዓሣ ይዞ መረቡ አልተቀደደም። 12ኢየሱስም “ኑ፤ ብሉ” አላቸው። ከደቀ መዛሙርቱ አንድ እንኳን “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ሊጠይቀው የደፈረ አልነበረም፤ ጌታ መሆኑን አውቀው ነበርና። 13ኢየሱስም መጣና እንጀራ አንሥቶ ሰጣቸው፤ እንዲሁም ዓሣውን። 14ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲገለጥላቸው ይህ ሦስተኛው ጊዜ ነበረ።
ኢየሱስና ጴጥሮስ
15ከበሉ በኋላም ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! ከእነዚህ ይበልጥ ትወደኛለህን?” አለው። “አዎን ጌታ ሆይ! እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ፤” አለው። ኢየሱስም “ግልገሎቼን አሰማራ፤” አለው። 16ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! ትወደኛለህን?” አለው። “አዎን ጌታ ሆይ! እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም “ጠቦቶቼን ጠብቅ፤” አለው። 17ለሦስተኛ ጊዜም “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! ትወደኛለህን?” አለው። ለሦስተኛ ጊዜ “ትወደኛለህን?” ስላለው ጴጥሮስ አዘነና “ጌታ ሆይ! አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም “በጎቼን አሰማራ። 18እውነት እውነት እልሃለሁ፤ አንተ ጎልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ቦታ ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ፤ ሌላ ሰውም ያስታጥቅሃል፤ ወደማትወደውም ይወስድሃል” አለው። 19በምን ዓይነት ሞት እግዚአብሔርን እንደሚያከብር ሲያመለክት ይህንን ተናገረ። ከዚያም “ተከተለኝ፤” አለው።
ኢየሱስና የሚወደው ደቀመዝሙር
20 #
ዮሐ. 13፥25። ጴጥሮስም ዘወር ሲል ኢየሱስ ይወደው የነበረውን ደቀመዝሙር ከበስተኋላው አየ፤ እርሱም በእራት ጊዜ ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ “ጌታ ሆይ! አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ያለው ነበረ። 21ጴጥሮስም እርሱን አይቶ ኢየሱስን “ጌታ ሆይ! እርሱስ እንዴት ይሆናል?” አለው። 22ኢየሱስም “እስክመጣ ድረስ እንዲኖር ብፈቅድስ፥ ምን ግድ አለህ? አንተ ተከተለኝ” አለው። 23ስለዚህ “ያ ደቀመዝሙር አይሞትም” የሚል ወሬ በወንድሞች መካከል ተሰማ፤ ነገር ግን ኢየሱስ “እስክመጣ ድረስ እንዲኖር ብፈቅድ ምን ግድ አለህ?” አለው እንጂ “አይሞትም፤” አላለውም ነበር።
24ስለ እነዚህም ነገሮች የመሰከረው፥ ይህንንም የጻፈው ይህ ደቀመዝሙር ነው፤ ምስክሩም እውነት እንደሆነ እናውቃለን።
25ኢየሱስም ያደረገው ሌላ ብዙ ነገር አለ፤ ሁሉም አንድ በአንድ ቢጻፍ፥ እንደሚመስለኝ፥ ዓለም እራሱ የሚጻፉትን መጻሕፍት ለመያዝ ቦታ አይበቃውም ነበር።
Currently Selected:
የዮሐንስ ወንጌል 21: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ