የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ወንጌል 20

20
የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ
(ማቴ. 28፥1-8፤ ማር. 16፥1-8፤ ሉቃ. 24፥1-14)
1ከሳምንቱም በመጀመሪያው ቀን መግደላዊት ማርያም ገና ጨለሞ ሳለ በማለዳ ወደ መቃብር መጣች፤ ድንጋዩም ከመቃብሩ ተፈንቅሎ አየች። 2እየሮጠችም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደነበረው ወደ ሌላው ደቀመዝሙር መጥታ “ጌታን ከመቃብር ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አናውቅም” አለቻቸው። 3ስለዚህ ጴጥሮስና ሌላው ደቀመዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። 4ሁለቱም አብረው ሮጡ፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ከጴጥሮስ ይልቅ ፈጥኖ ወደ ፊት ሮጠና ቀድሞ ወደ መቃብሩ ደረሰ፤ 5ዝቅም ብሎ ሲመለከት የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፤ ነገር ግን አልገባም። 6ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት መጣ፤ ወደ መቃብሩም ገባ፤ የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፤ 7እንዲሁም በራሱ ላይ የነበረውን ጨርቅ ለብቻው በአንድ ስፍራ ተጠምጥሞ እንደ ነበረ እንጂ ከተልባ እግሩ ልብስ ጋር ተቀምጦ እንዳልነበረ አየ። 8በዚያን ጊዜ አስቀድሞ ወደ መቃብር የመጣውም ሌላው ደቀመዝሙር ገባ፤ አየም፤ አመነም፤ 9“ከሙታን መነሣት ይገባዋል” የሚለውን የመጽሐፉን ቃል ገና አላወቁም ነበርና። 10ደቀ መዛሙርቱም ወደ ቤታቸው ሄዱ።
ኢየሱስ ለመግደላዊት ማርያም ታየ
(ማቴ. 28፥9-10ማር. 16፥9-11)
11ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር። እያለቀሰችም ወደ መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤ 12ሁለት ነጭ ልብስ የለበሱ መላእክትም፥ የኢየሱስን ሥጋ አስተኝተውበት በነበረበት ስፍራ፥ አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች። 13እነርሱም “አንቺ ሴት! ስለምን ታለቅሻለሽ?” አሉአት። እርሷም “ጌታዬን ወስደውታል፤ ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም፤” አለቻቸው። 14ይህንም ብላ ወደ ኋላ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ነገር ግን ኢየሱስ እንደሆነ አላወቀችም። 15ኢየሱስም “አንቺ ሴት! ስለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ?” አላት። እርሷም የአትክልት ጠባቂ መስሎአት “ጌታ ሆይ! አንተ ወስደኸው እንደሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ፤ እኔም እወስደዋለሁ፤” አለችው። 16ኢየሱስም “ማርያም!” አላት። እርሷ ዘወር ብላ በዕብራይስጥ “ረቡኒ!” አለችው፤ ትርጓሜውም “መምህር ሆይ!” ማለት ነው። 17ኢየሱስም “ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ ‘እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ፤’ ብለሽ ንገሪአቸው፤” አላት። 18መግደላዊት ማርያም ሄደችና ጌታን እንዳየችው፥ ይህንንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረች።
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ታየ
(ማቴ. 28፥16-20ማር. 16፥14-18ሉቃ. 24፥36-49)
19በዚያው ከሳምንቱ የመጀመሪያው በሆነው ቀን፥ በመሸ ጊዜ፥ ደቀመዛሙርቱ ተሰብስበው በነበሩበት፥ አይሁድን ስለ ፈሩ ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ፥ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። 20ይህንንም ብሎ እጆቹንም ጎኑንም አሳያቸው። ደቀ መዛሙርቱም ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው። 21ኢየሱስም ዳግመኛ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ፤” አላቸው። 22ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። 23#ማቴ. 16፥19፤ 18፥18።ኀጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል፤” አላቸው።
ኢየሱስና ቶማስ
24ነገር ግን ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ከእነርሱ ጋር አልነበረም። 25ሌሎቹም ደቀመዛሙርቱ “ጌታን አይተነዋል፤” አሉት። እርሱ ግን “የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ላይ ካላየሁ፥ ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ውስጥ ካላስገባሁ፥ እጄንም በጎኑ ቊስል ውስጥ ካላስገባሁ አላምንም፤” አላቸው።
26ከስምንት ቀን በኋላም ደቀመዛሙርቱ ደግመው በቤት ውስጥ ነበሩ፤ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበረ። ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። 27ከዚያም በኋላ ቶማስን “ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ ውስጥ አስገባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን፤” አለው። 28ቶማስም “ጌታዬና አምላኬ!” ብሎ መለሰለት። 29ኢየሱስም “ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው” አለው።
የዚህ መጽሐፍ ዐላማ
30ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፉ ሌላ ብዙ ምልክቶችን በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ፤ 31ነገር ግን ኢየሱስ መሢሕ፥ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ