የዮሐንስ ወንጌል 21
21
የኢየሱስ ለሰባቱ ደቀ መዛሙርት መገለጥ
1ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በጥብርያዶስ ባሕር አጠገብ፥ ለደቀ መዛሙርቱ እንደገና ተገለጠ፤ የተገለጠውም እንደሚከተለው ነው፤ 2ስምዖን ጴጥሮስ፥ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ፥ የቃና ዘገሊላው ናትናኤል፥ የዘብዴዎስ ልጆችና ሌሎች ሁለት ደቀ መዛሙርት አብረው ነበሩ። 3ስምዖን ጴጥሮስ “ዓሣ ለማጥመድ መሄዴ ነው” አላቸው። #ሉቃ. 5፥5።
እነርሱም “ከአንተ ጋር እንሄዳለን” አሉት፤ ወጥተውም ሄዱና ወደ ጀልባ ገቡ፤ ነገር ግን በዚያች ሌሊት አንድ ዓሣ እንኳ አልያዙም። 4ሲነጋ ኢየሱስ በባሕሩ ዳር ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም። 5ኢየሱስም “ልጆች ሆይ! አንዳች ዓሣ አላችሁን?” አላቸው።
እነርሱም “ምንም የለንም” አሉት።
6እርሱም “መረቡን ከጀልባው በስተቀኝ በኩል ጣሉና ታገኛላችሁ” አላቸው። ስለዚህ መረቡን በባሕሩ ውስጥ ጣሉት፤ ብዙ ዓሣም ከመያዛቸው የተነሣ መረቡን መጐተት አቃታቸው። #ሉቃ. 5፥6።
7በዚህ ጊዜ ኢየሱስ የሚወድደው ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን “ጌታ ነው እኮ!” አለው። ስምዖን ጴጥሮስ “ጌታ ነው” ማለትን በሰማ ጊዜ ለሥራ ብሎ ልብሱን አውልቆ ስለ ነበረ ወዲያው ልብሱን ለበሰና ወደ ባሕሩ ዘሎ ገባ። 8ሌሎች ደቀ መዛሙርት ግን ከምድር የራቁት መቶ ሜትር ያኽል ብቻ ስለ ነበረ ዓሣ የሞላበትን መረብ እየሳቡ በጀልባ መጡ። 9ከጀልባው በወረዱ ጊዜ ዓሣ በላዩ የነበረበት የከሰል ፍምና እንጀራ አዩ። 10ኢየሱስም “አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ አምጡ” አላቸው።
11ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ወደ ጀልባው ገብቶ መቶ ኀምሳ ሦስት ትልልቅ ዓሣዎች የሞሉበትን መረብ ወደ ምድር ጐተተ፤ ይህን ያኽል ብዙ ዓሣ ቢይዝም መረቡ አልተቀደደም። 12ከዚህ በኋላ ኢየሱስ፦ “ኑ ብሉ” አላቸው። ጌታ ኢየሱስ መሆኑን ሁሉም ዐውቀው ስለ ነበር፥ ከደቀ መዛሙርቱ አንድ እንኳ፥ “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ሊጠይቀው የደፈረ አልነበረም። 13ከዚያም ኢየሱስ መጣና፤ እንጀራውንና ዓሣውን አንሥቶ ሰጣቸው።
14ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ ወዲህ ደቀ መዛሙርቱ ሲያዩት ይህ ሦስተኛ ጊዜ ነበር።
ኢየሱስ ለጴጥሮስ ያቀረበው ጥያቄ
15ቊርስ ከበሉ በኋላ ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን፥ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! እነዚህ ከሚወዱኝ ይበልጥ ትወደኛለህን?” አለው። እርሱም “አዎ፥ ጌታዬ ሆይ! እኔ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” ሲል መለሰለት። 16ኢየሱስም “ግልገሎቼን መግብ” አለው። ሁለተኛ ጊዜም “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! ትወደኛለህን?” አለው። እርሱም “አዎ፥ ጌታዬ ሆይ! እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም “ጠቦቶቼን ጠብቅ” አለው። 17ሦስተኛ ጊዜም “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! ትወደኛለህን?” አለው። ሦስተኛ ጊዜ “ትወደኛለህን?” ስላለው ጴጥሮስ አዘነና “ጌታ ሆይ! አንተ ሁሉን ታውቃለህ፥ እኔ እንደምወድህም ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “በጎቼን አሰማራ፤ 18እውነት፥ እውነት እልሃለሁ፤ አንተ ጐልማሳ ሳለህ ቀበቶህን በገዛ እጅህ ታጥቀህ ወደ ፈለግኽበት ትሄድ ነበር፤ በሸመገልክ ጊዜ ግን አንተ እጆችህን ትዘረጋና ሌላ ሰው ያስታጥቅሃል፤ ወደማትፈልግበትም ይወስድሃል።” 19ይህንንም ያለው ጴጥሮስ በምን ዐይነት ሞት እግዚአብሔርን ማክበር እንዳለበት ሲያመለክት ነው፤ ከዚህ በኋላ ጴጥሮስን “ተከተለኝ!” አለው።
ኢየሱስና ሌላው ደቀ መዝሙር
20ጴጥሮስ ዘወር ብሎ ኢየሱስ የሚወድደው ደቀ መዝሙር ሲከተለው አየ፤ ይህ ደቀ መዝሙር በእራት ጊዜ ወደ ኢየሱስ ተጠግቶ፥ “ጌታ ሆይ፥ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ብሎ የጠየቀው ነው። 21ጴጥሮስ እርሱን አየና “ጌታ ሆይ! ይህስ ሰው ምን ይሆናል?” ሲል ኢየሱስን ጠየቀ።
22ኢየሱስም “እኔ እስክመጣ ድረስ እንዲኖር ብፈቅድ አንተን ምን አገባህ? አንተ ተከተለኝ!” አለው።
23በዚህ ምክንያት በወንድሞች መካከል፥ “ይህ ደቀ መዝሙር አይሞትም” የሚል ወሬ ተሰራጨ፤ ነገር ግን ኢየሱስ፥ “እኔ እስክመጣ ድረስ እንዲኖር ብፈቅድ አንተ ምን አገባህ” አለ እንጂ፥ “አይሞትም” አላለም። 24ስለ እነዚህ ነገሮች ሁሉ የመሰከረና እነዚህንም ነገሮች የጻፈ ይህ ደቀ መዝሙር ነው፤ የእርሱም ምስክርነት እውነት እንደ ሆነ እናውቃለን።
25ኢየሱስ ያደረጋቸው ሌሎች ብዙ ነገሮች ደግሞ አሉ። እኔ እንደሚመስለኝ እርሱ ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉ አንድ በአንድ ቢጻፉ ኖሮ የሚጻፉትን መጻሕፍት ዓለም ራሱ መሸከም ባልቻለም ነበር።
Currently Selected:
የዮሐንስ ወንጌል 21: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997